lunedì

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆን ከአጭበርባሪዎች ተጠንቀቅ


“EPISODIO DI SCIACALLAGGIO”

ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ
ጉዳዩ በቂ የመኖሪይ ፈቃድ ወረቀት ሳይኖራቸዉ በጣሊያን ምድር ላይ ከዛሬ ነገ ኑሮ ያልፍልኛል ብለዉ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙትን የዉጭ ሀገር ዜጎች በተለይም የአማርኛ ቛንቛን አንብበዉ መረዳት የሚችሉትን ሁሉ የሚመለክት ነዉ::
በጣሊያን ሀገር እንደማንኛቸዉም ሌሎች ሀገሮች ሁሉ አንዳንድ አታላዮችና አጭበርባሪ ግለሰቦች ህገወጥ በሆነ መንገድ ገንዘብ ማግኘትን ብቻ ሙያዬ ብለው ተያይዘዉታል:: “ዬትም ፍጪዉ ዱቄቱን አምጪዉ” እንደሚሉት የአያቶቻችን ተረት ይሆንና ልባቸዉ ድንጋይ ከመሆኑ የተነሳ የሌላዉን ሰዉ ችግር ከምንም አይቆጥሩትም፣ ርህራሄ የሚባል በዉስጣቸዉ አልተፈጠረም፣ ማንንም ለይተዉ አያዩም::
ይህችንም ማስጠንቀቂያ ለመጫር ያስገደደኝ ነገር ቢኖር ሰሞኑን እዚሁ በጣሊያን ሀገር በፖርደኖኔ ከተማ (Pordenone) የመኖሪይ ፈቃድ ወረቀት በሌላቸዉ የዉጭ ሀገር ዜጎች ላይ የተከሰተዉ ይህ ነዉ የማይባል የበደል በደል ነዉ:: ፖርደኖኔ (Pordenone) ከተማ ላይ ሰሞኑን የመኖሪይ ፈቃድ ወረቀት ያለገደብ በፖርደኖኔ ፖስታ ቤት በኩል እየተሰጠ ነዉ ብሎ በማስወራት ያለአግባብ ገንዘብ በመቀበልና በማታለል አንዳንድ በጣሊያን ሀገር የሚገኙትን የመኖሪይ ፈቃድ ወረቀት የሌላቸዉን የዉጭ ሀገር ዜጎች ከፍተኛ ችግር ላይ ጥለዋቸዋል፣ የጣሊያን ፖሊስም አገሪቱን ለቀዉ እንዲወጡ አስፈላጊዉን እርምጃ ለመዉሰድ ተገዷል:: መጠንቀቅ የሚገባዉ ነገር ቢኖር ባሁኑ ወቅት የጣሊያን መንግስት ምንም አይነት የመኖሪይ ፈቃድ ወረቀት ሊያስገኝ የሚችል ህግ አልደነገገምና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል::
ይህንን መልእክት ሰምቶ ላልሰማ ማሰማት መልካም ስነምግባር መሆኑን መዘንጋት የለብንምና ተግባራዊ ለማድረግ እንሞክር እላለሁ::
መልካም ወቅት ለአንባቢያን
zeleke_eresso@yahoo.it


የተጓዥ የውጪ ዜጋዎች መመሪያ ላይ ማሻሻያ ተደረገ


12 08 07
.
ለእረፍት ወደ ትውልድ ሀገር ደርሶ ለመመለስ የሚያስችለው መመሪያ ነጥቦች ላይ እርማትና ማሻሻያ ተደረገበት።
.
ይህ ከሚመለከታቸው የውጪ ዜጋዎች መሐከል ለመጀመሪያ ጊዜ ሶጆርኖ ለማውጣት ፎርም ሞልተው ማመልከቻ ያስገቡትንም ይጨምራል። አዎ እነሱም ሳይቀሩ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ለእረፍት ሄደው መመለስ ይችላሉ። ይህ የታረመው የመመሪያ ነጥብ የሚጠቅሰው አንቀጽ እንዲህ ይላል…..
« አንድ የውጪ ሀገር ዜጋ ሶጆርኖ ለማውጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ማመልከቻ ያስገባ ከሆነና ለዚህም ደግሞ የፖስታቤት ደረሰኝ (cedolino delle Poste) የተሰጠው ከሆነ ለእረፍት ወደ ትውልድ ሀገሩ ሄዶ መመለስ ይችላል።»

ማስገንዘቢያ
ይህ ለመጀመሪያ ተጓዦች ለሚሆኑት የውጪ ዜጋዎችን የሚመለከት የመመሪያ ማሻሻያ ድንጋጌ ከሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ውስጥ በ 6 08 2007 የታረመ ነው። ጽህፈትቤቱም ይህንን መመሪያ ለውጪ ሀገር ዜጋዎች ጉዳይ አስፈጻሚ (immigrazione) ቢሮዎች በደብዳቤ እንዲተላለፍላቸው እንዲሁም በመገናኛዎች እንዲወጡ ያደርጋሉ። ይህም እስከሚደረግ ጊዜ መጠባበቅ ይኖርበታል። በአስቸኳይ እንድሚያስተላልፉትና በቅርቡም በስራ ላይ እንዲያውሉት የሁላንም ምኞት ነው።
እስከዛሬ ድረስም በጣሊያን ለመኖርና ለመስራት ፍቃድ (ሶጆርኖ) ያልነበራቸው ፍቃዱን ለማግኘት ያገቡት ማመልከቻ የመጀመሪያቸው ስልሆነ በተሰጣቸው ደረሰኝ ወረቀት የትውልድ ሀገራቸው ደርሰው መመለስ የማይቻል ነበረ። ይኸውም በመጀመሪያው የደረሰኝ ወረቀት ብቻ ሄዶ ለመመለስ ከፍተኛ ጥርጣሬና ስጋት በመኖሩ ማንም የሚሞክር እንኳን እንዳልነበረ ይታወቃል። አሁን ግን የመጀመሪያውን የመኖሪያው ፍቃድ ለማግኝት በመጠባበቅ ላይ ያሉትም በcedolino ብቻ ሄደው መመለስ ይችላሉ። ሶጆርኖ በእጃቸው እስከሚሰጣቸው ድረስ ለሚጠብቁት ሀገራቸው ለመሄድ ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል ማለት ነው።
.
እነዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶጆርኖ አውጪዎች ያላቸው መብት በኪሳቸው ሶጆርኖውን ከያዙት ወይም እስከሚታደስላቸው ድረስ በመጠባበቅ ላይ ካሉት ጋር እኩል ነው ማለት አይቻልም። በመጀመሪያው ሶጆርኖ አውጪ ላይ አንዳንድ መብቶች ላይ ወሰን በማድረግ የተለያዩ ፈቃዶችን ይነፍጋቸዋል። ነገርግን መብቱ እኩል ባይሆላቸውም የዚህ መመሪያ ማሻሻያ የሚያስከፋ አይደለም። መብታቸውን እኩል እንዳይሆን የሚያደርጉት ልዩነቶች ከዚህ በታች ሰፍረዋል።

የመጀመሪያ ሶጆርኖ አውጪ ከሆነ
1ኛ* ከጣሊያን በወጣበት በር ተመልሶ መግባት ይኖርበታል።
2ኛ* ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገር መጓዝ አይቻልም። በፊትም በነበረው ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌ መሠረት የarea schengen አካባቢ መዟዟር አይቻልም።
እነዚህ ሰነዶች በመውጪያም ሆነ በመግቢያ ጊዜ የድንበር ፖሊሶች ማህተም የሚያደረጉባቸው በመሆናቸው በጉዞ ላይ ምንግዜም በእጅ የሚያዙ ናቸው። ከጣሊያን በሚወጡበትም ሆነ በሚገቡበት ጊዜ ዶኩሜንታቸው ላይ (የፖስታቤት ደረሰኙ፣ ፓስፖርቱ፣ ቪዛው እንዲሁም ሶጆርኖ አሳዳሽ ከሆነ ጊዜው የወደቀበትን የሶጆርኖ ኮፒውን (ግልባጭ) ወዘተ… ወዘተ… ማሳየት ይገባቸዋል። በሁሉም መዝገቦች ላይ የድንበር ፖሊሶች ማህተም ወይም ቁጥጥር ስለሚያደርጉበት ነው። በአጠቃላይ ይህ የፖስታ ቤት ደረሰኝ ወረቀት እንደመጓጓዣ ሰነድ ቢያገለግልም ጉዞው (መነሻውና መድረሻው) የተወሰነ ነው።
3ኛ* (ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ...)
የእኛ አስተያየት
የመመሪያ ማሻሻያዎች በሚደረጉበት ጊዜ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሥራ ላይ እንዲውል በየቦታው ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ስራውን የሚያስፈጽሙት የኢሚግሬሽን ጽህፈት ቤቶችና ቢሮዎች ሳያዘገዩ ጊዜው በስራ ላይ እንዲያውሉት ማድረግና በተለይም ለሰሞኑ የእረፍት ተጓዦች እንዳይተጓጎሉ ጥረት ቢደረግ አይከፋም። በተለይም ሀገራችንን የሚመለከተው የሚሊኒየም በዓል አከባበር ላይ ብዙ ተጓዦች የሆኑ ወገኖቻችን ስለአሉበትና የኦች የመመለሻ ቀን ገደብ አስከ 30 10 07 በመሆኑ.......

.
በፖስታ ቤት ደረሰኝ ወረቀት ወደ ውጪ የሚሄዱና የሄዱ በሙሉ እስከ … 30 10 2007 ድረስ መመለስ ይኖርባቸዋል
.
ሶጆርኖ ለማሳደስ የፖስታ ቤት ደረሰኝ ያላቸው ለእረፍት ከጣሊያን ለሚወጡና ለወጡ በሙሉ የመመለሻቸው ቀን ላይ የመጨረሻ የጊዜ ገደብ ቀን ተደረገበት። ይኸውም የገደብ ቀን የሚመጣው October 30 2007 እንደሆነ በሀገር ውስጥ የአስተዳደር ሚኒስትር በወጣው የመመሪያ ማሻሻያዎች ላይ ባለፈው ሳምንት ተደነገገ።

የእኛ አስተያየት
ይህ እየተጓተተ ያለው የሶጆርኖ እድሳት ለሚያስከትለው የውጪ ዜጋዎች ችግር ለማቀለል በሂደቱ ላይ በየጊዜው የመመሪያ ለውጦች በማድረግ ማሻሻያ እያደረጉ ቢሆንም የሚወጡትን መመሪያዎች በጊዜው ለማስፈጸም ቢሮክራሲው በሚያስከትለው ችግር ምክንያት ሌሎች ችግሮች እየተፈጠሩ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ የመኖሪያ ፈቃድ ለማሳደስ ማመልከቻ በፖስታቤት አቅርበው እስከሚሰጣቸው ድረስ የሚጠባበቁ የውጪ ሀገር ዜጎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በመሆናቸውና ችግሮችን ለማቃለል እየተጓተተ ያለው የሶጆርኖ እድሳት ቢሮክራሲ ወደ የሀገራቸው ለእረፍት ለሚሄዱት ተጓዦች ችግር ከብዙ በጥቂቱ እንዲቃለልላቸው ቢያደርግም በዚሁ ቢሮክራሲ የተነሳ ብዙዎች የዉጭ ሀገር ዜጎች ሰራተኞች ከነበራቸዉ የስራ መስክ ሊባረሩ ተዳርገዋል። ሌላ ስራ የሚቀጥር ድርጅት ፈልገዉም ቢያገኙም እንኳን የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀታቸው በመዉደቁ ከመቀጠር እየተጓጎሉ ይገኛሉ። እናም መዘዙና ውጣ ውረዱ እየበዛ መጥቶ በብዙዎቹ ዉጭ ዜጋዎች ላይ ስቃይ ጨምሯል። ለዚህ ደግሞ መፍትሄ ይሆናል በማለት በአለፈው ሳምንት ላይ በዚሁ አምዳችን ላይ በዶክተር ዘለቀ ጥቆማዎች ተደርገው እንደነበር ይታወሳል። ይኸንንም በድጋሜ ለማስታወስ "ይህ ችግር የገጠማቸው የውጪ ዜጋዎች በሙሉ የፖስታ ቤት ደረሰኝ ወረቀታቸውን ይዘው በመሄድ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የስራ አጦች ሊስት ላይ መመዝገብ መቻል ይሆናል። በቁጥር 19/2007 የጣሊያን የሀገር ዉስጥ ሚንስቴር ድንጋጌ ላይ የወጣ በመሆኑ በሚኖሩበት ሀገር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ቢሮ በመቅረብ መመዝገብ ይችላሉ" የሚል ነበር። ...


በፖስታ ቤት የደረሰኝ ወረቀት ነፍስህን አድን



የጣሊያን ቢሮክራሲና ማለቅያ የሌለዉ የዉጭ ሀገር ዜጋዉ ስቃይ
20 07 07
ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ
ሰሞኑን ከተለያዩ ሰዎች “የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀቴን ለማሳደስ ፖስታ ቤት ካስገባሁ ሁለት፣ ስድስት፣ ዘጠኝ፣ አስራ ሁለት ወራት ወዘተ ሞላኝ ዳሩ ግን እንዃንስ ወረቀቱ ታድሶ ሊላክልኝ ቀርቶ ፎቶግራፍ እንዳቀርብ እንኳን የጠየቀኝ ሰዉ የለም” በማለት ብሶታቸዉን ሲገልጹ እሰማለሁ:: ከዚሁ የቢሮክራሲ ዉጣ ዉረድ የተነሳ በብዙ የሚቆጠሩ የዉጭ ሀገር ዜጎች ሰራተኞች ቀደም ሲል ከነበራቸዉ የስራ መስክ ሊባረሩ ተዳርገዋል፣ ፈልግዉም ሌላ ስራ ቢያገኙ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀቱ በመዉደቁ የሚቀጥራቸዉ ድርጅት አይኖርም:: ይህ ብቻ ሳይሆን መዘዙ እየበዛ ይመጣና የዉጭ ሀገር ዜጋዉ ስቃይ ይጨምራል፣ መፍትሄዉ የፖስታ ቤት ደረሰኝን በማሳየት በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የስራ አጦች ሊስት ላይ መመዝገብ መቻል ይሆናል:: የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀቱን ለማሳደስ ፖስታ ቤት አስገብቶ የፖስታ ቤት ደረሰኝ ተሰጥቶት በመጠባበቅ ላይ ያለ ግለሰብ ሁሉ በየክፍለ ሀገሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ቢሮ በመቅረብ መመዝገብ እንደሚችል በቁጥር 19/2007 የጣሊያን የሀገር ዉስጥ ሚንስቴር ሰሞኑን ደንግጓል::

ሶጆርኖ እስከሚሰጡኝ ጊዜ ቢፈጅም የራሱ ጉዳይ


መምሪያ

28 07 2007

ምንም እንኳን ይህ መምሪያ ለዚህ የውጪ ዜጎች ለእረፍት ጉዞዋቸው እንዲጠቀሙበት ዘግየት ብሎ የወጣ ቢሆንም ሰሞኑን በሀገር አስተዳደር ሚኒስትር ጁሊያኖ አማቶ የተፈረመበት መምሪያ በመሆኑና ለሁላችንም መልካም ዜና ስለሆነ መልዕክቱን እንዲያነቡት ስናደርግ ከደስታ ጋር ነው።
"ማንኛውም የውጪ ዜጋ የመኖሪያ ፈቃዱን ለማሳደስ ማመልከቻ ያስገባ ከሆነና ለዚህም ደግሞ የፖስታቤት ደረሰኝ የተሰጠው ከሆነ መብቱ በሙሉ ሙሉ ሶጆርኖ በኪሱ ከያዘው እኩልና የማያንስ ነው" የሚል ነው። ስለዚህም ሥራ መቀየር፣ አዲስ የቤት ኪራይም ሆነ የሥራ ኮንትራት መውሰድ፣ የመኪና መንጂያ ፈቃድ ማውጣት፣ የትውልድ ሀገሩ ደርሶ መመለስ፣ ወዘተ...ወዘተ...ወዘተ...ወዘተ...
በአጠቃላይ የፖሊስ ጽህፈትቤቱ (ኩዌስቱራ) ሶጆርኖ እስከሚታደስላቸው ድረስ በመጠበቅ ላይ ያሉትን የሚነፍጋቸውን መብቶች አሁን ነጻ ያደርጋቸዋል። ሶጆርኖ በኪሱ ካለው ጋር እኩል መብት እንዲኖረው ያደርጋል ማለት ነው።
መምሪያውን ከዚህ ያውርዱ

ማስገንዘቢያዎች
* የትውልድ ሀገሩ ደርሶ መመለስ ለሚፈልግ ለፋሲካ፣ ለገና፣ እንዲሁም ለበጋው እርፍት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ትውልድ ሀገር ደርሶ ለመመለስ ይችላል። ነገር ግን ወደ ከጣሊያን በወጣበት በር ተመልሶ መግባት ይኖርበታል። ምክንያቱም ሲወጣ ፓስፖርቱ ላይ ማሕተም የሚያደረግበት የድንበር ፖሊስ ሲገባም ማሕተም ስለሚያደርግበትና መመለሱ የሚመዘገብበ ስለሆነ ነው። ከዚህም በላይ የፖስታቤቱ ደረሰኝ ወይም ጊዜው የወደቀብት ሶጆርኖ ላይም ቁጥጥር ሊኖር ይችላል።
* ሌላው ደግሞ ይህ የፖስታ ቤት ደረሰኘ ወረቀት እንደመጓጓዣ ሰነድ ቢያገለግልም ጉዞው (መነሻውና መድረሻው) የተወሰነ በመሆኑ ከደርሶ መመለሱ ሌላ ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገር መጓዝ አይቻልም። በፊትም በነበረው ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌ መሠረት የ (area schengen) አካባቢ መዟዟር አይቻልም።

ምንም እንኳን ይህ የተፈረመበት ዋና መመሪያ በሥራ ላይ እንዲውል በየቦታው የተላለፈ ቢሆንም ከፖሊስ ጽህፈት ቤቱ ሌላ በየቢሮዎች ሙሉ በሙሉ መሪያውን እንዲጠቀሙበትና በአስቸኳይ ለዚህ የእረፍት ጊዜ ተጓዦች እንዳይተጓጎሉና በቶሎ እንዲፈጸምላቸው የሁላችንም ምኞት ነው። ከዚህም በላይ ይህ መምሪያ በዚህ ዓመት ያለውን ጊዜያዊ የውጪ ዜጋዎችን ችግርና ይህንን እየተጓተተ ያለውን የሶጆርኖ እድሳት ቢሮክራሲ ለማቀለል ተብሎ የተደረገ ሊሆን ስለሚችል በሂደቱ ላይ ለውጦች ሊኖሩት ይችላሉ:: ስለዚህም ወደፊት ለተሻለ ሁኔታ ተስፋ እናደርጋለን።

አብራሃም ዘ. 28 07 2007