martedì

ከኩዌስቱራ ወደ ፖስታ ቤት


ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም
ዶ/ር ዘለቀ እሬሶ
Bologna (Italy) 28/11/2006

በእጣሊያን አገር ለመኖር የሚያስችለዉን የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት (permesso di soggiorno e carta soggiorno) አዲሱን ለማዉጣትም ሆነ አሮጌዉን ለማሳደስን በተመለከተ ሰሞኑን አዲስ መመሪያ ተላለፈ::
ካሁን ቀደም በፖሊስ - በኩዌስቱራ - ሲሰጥም ሆነ ሲታደስ የነበረዉ የመኖሪያ የፈቃድ ወረቀት ከሚቀጥለዉ ሰኞ 04/12/2006 ጀምሮ በፖስታ ቤት እንዲከናወን የእጣሊያን የሀገር ዉስጥ ሚንስትሩ በአለፈው ጊዜ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጡ:: በመሆኑም ፖስታ ቤቶች ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ተጨማሪ ማስተናገጃዎችን ለማዘጋጀት በመሮጥ ላይ ይገኛሉ:: ለዚህም ዉሳኔ ሊደረስ የተቻለዉ ከ 06/11/2006 ጀምሮ በፕራቶ፣ በአንኮና፣ በፍሮስኖኔ፣ በብርንድሲ እና በመሳሰሉት ጥቂት የእጣሊያን ትናንሽ ከተሞች የተካሄደዉ ጊዜያዊ ሙከራ ባስገኘዉ ጥሩ ዉጤት መሰረት ነዉ ይባላል::
.
ለማሳደስም ሆነ አዲስ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ለማግኘት:-
1) በአቅራቢያ በሚገኘዉ ማንኛዉም ፖስታ ቤት በመሄድ ፎርም መቀበል;
2) ፎርሙ አዲስ መጠየቂያ፣ ማሳደሻ፣ መቀየሪያ፣ ማስተካከያ፣ ወዘተ ለመሳሰሉት ይጠቀማል;
3) የመኖሪያዉ ፈቃድ ለስራ (ቅጥረኛ ወይም የግል)፣ ለቤተሰብ፣ ለትምህርት፣ ለቱሪዝም፣ ለሃይማኖት እና ለመሳሰሉት ሁሉ ይጠቅማል;
4) የሰራተኛ ማህበር ተወካዮችም (patronati) አስፈላጊዉን አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተዋል;
5) ፎርሙ ተሞልቶ ፖስታ ቤት መረከብ አለበት;
6) ፖስታ ቤቱ ለአስረካቢዉ ደረሰኝ ይሰጣል;
7) ፖስታ ቤቱ የተረከበዉን ጥያቄ ወደ ኩዌስቱራ ይልከዋል;
8) ኩዌስቱራም መዝገቡን አጣርቶ የመጀመሪያ ጥያቄ ከሆነ ግለሰቡን ለአሻራ ይጠራዋል ነገር ግን ለማሳደስ ከሆነ ቀርቦ እንዲወስድ ይጠራዋል::

.

ይህ ቀላል ለዉጥ አይደለም ቀደም ተብሎ በየዜና ማሰራጫዎች በሰፊዉ መነገር የነበረበት ጉዳይ ነዉ:: እንደሚታወቀዉ የእጣሊያን መንግስት የዉጭ አገር ዜጋ ጉዳይ ሲሆን ሁሌ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አይደል? ይህን ለዉጥ ስንቶቹ የዉጭ አገር ዜጎች ሰምተዉታል? ምን ያህልስ ተግባራዊ ይሆናል? ዉጤቱን ለማየት ያብቃን::

.

የክፍያ ጉዳይ ማንኛዉም ጠያቂ እያንዳንዱ € 30,00 ለፖስታ ቤት የአገልግሎት ዋጋ ይከፍላል:: ለቴምብር € 14,62; € 27,50 ደግሞ ለፎርም የመክፈል ግዴታ አለበት:: መመሪያዉ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀዉ ከሰኞ 11/12/2006 መሆኑን በዚህ አጋጣሚ በጣሊያን ለሚኖሩ አንባቢያን መግለጥ እወዳለሁ::