domenica

የዘርና የቀለም ልዩነት በምዕራብ ሀገሮች


የዘርና የቀለም ልዩነት መስፋፋት በምዕራብ ሀገሮች እንደ ሰደድ እሳት እየቀጠለ የሚሄድና አሳሳቢነቱም እየጎላ መምጣቱ ታውቋል። ከምን ተነስቶ ከምን እንደደረሰ ግምገማ ተደርጎበታል።
በተባበሩት መንግሥታት ማኅበር በኩል የተደረገው ጥናት በተለይም በዲሞክራሲ መርሆ እንደሚመራ የሚነገርለት የምዕራባውያኑ ማኅበራዊ ኑሮ ለዘርና ለቀለም ልዩነት የተጋለጠ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም ለሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑ ድርጅቶችና ጥናቶች አሳሳቢነቱን በግልጽ አስምረውበታል። ይሁንና የምዕራቡ ሀገር ፖለቲከኞች ሁኔታው አልፎ አልፎ የሚከሰት የቀለምና የዘር ልዩነት እንዳለ ቢናገሩም ይህን ያህል አሳሳቢ ነው ብለው ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት መከበር ተጠሪ የሆኑት የሴኒጋሉ ተወላጅ አፍሪቃዊው ዱኦዶ ዴኔ ስለ ጉዳዩ ብዙ የሚሉት አላቸው። በቅርቡ ከተከሠተው ከፈረንሣዩ ሁኔታ በመጀመር፥ በእስፓኝ የተደረገውን ያስታውሳሉ። በእስፓኝ አገር “እንዳሉሲን” በተባለው ክፍለ ሀገር አንድ የሞሮኮ ተወላጅ አንዲት ሴት በመግደሉ ወዲያው የሞሮኮ ተወላጅ የሆኑ አረቦች ሁሉ እንደ ዱር አውሬ ታድነው ተያዙ አንዳንዶችም ተገደሉ። በሆላንድ አገር በአምስተርዳም ከተማ የተፈጸመው ከዚህ የተለየ አይደለም። ቫን ጎኅ የተባለው ፊልም አዘጋጅ በመገደሉ ብዙ የሞሮኮ ተወላጆችና አረቦች ተንገላተዋል። ይህ የሚያመለክተው ችግሩ እንደ ሰደድ እሳት እየተያያዘ በመሄድ በተለያየ ቦታ እየተዳረሰ መሆኑን ነው። የሚገርመው ግን ይላሉ ዱኦዶ ዴኔ አንድ እራስ በተቆረጠ ቁጥር ሌላ እራስ እያቆጠቆጠ መሄዱ ነው።
እንደዚህ ያለውን መሠረታዊ ግጭት የሚፈጥሩት ሶስት ጉዳዮች እንደሆኑ ተመራማሪዎች በጥናት ደርሰውበታል። አንደኛ የዘርና የቀለም፥ ሁለተኛው የባሕል፥ ሦስተኛው የሃይማኖት ልዩነት ነው። እነዚህ ሁኔታዎች በአንድ አገር ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። ከሁሉም የሚከፋው ግን የዘርና የቀለም ልዩነት መሆኑን የሴኒጋሉ ተወላጅ ዱኦዶ ዴኔ ይናገራሉ።
የዓለም ማኅበረሰብ በዘርና በቀለም ልዩነት የሚመጣውን አሳሳቢ ግጭት ቀደም ብሎ ስለተረዳው የቀለምና የዘር ልዩነት የሚወገድበትን መንገድ ለመቀየስ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ጉዳዩን በኃላፊነት ወስዶ እየተከታተለ የዘርና የቀለም ልዩነትን የሚያስወግድ ድርጅት እስከማቋቋም ደርሷል። ይሁንና ድርጅቱ ተቋቁሞ፥ መመሪያውም ተዘጋጅቶ በሥራ እንዲተረጎም ጥረት በሚደረግበት ጊዜ አንዳንድ ውጤቶች ቢመዘገቡም ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ውሏል ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም።
በአሁኑ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ማኅበር አስተያየት በምዕራባውያን አገሮች ዘንድ የሰብአዊ መብት የተከበረበት ዲሞክራሲ ሰፍኗል እየተባለ ቢለፈፍም በአንዳንድ አገሮች በሚታየው የዘርና የቀለም ልዩነት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ከሌሎች አገሮች እየፈለሱ ወደ ምዕራባውያን አገሮች የሚገቡ ስደተኞችም ሆኑ ሠራተኞች የራሳቸውን ባሕልና ልማድ ይዘው ስለሚገቡ ሌላ አዲስ መዋቅር መጣል ይኖርበታል። ... ይቀጥላል ...