venerdì

አውሮፓና ስደተኞች


ሜዴትራኒያን ውቂያኖስን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመዝለቅ የሚጥሩት ስደተኞች ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ ነው የመጣው። የሜዴትራኒያን ባሕር ተዋሳኝ ከሆኑት የማግሬብ አገሮች፤ ከሊቢያ፣ ሞሮኮ፣ አልጄሪያና ቱኒዚያ ተነስተው ውቂያኖሱን በጀልባ በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመዝለቅ የሚሞክሩት አፍሪቃውያንና የመካከለኛው ምሥራቅ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ከድህነት ለማምለጥና የተሻለ ኑሮ ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግ አገራቸውን ለቀው ከሚሰደዱት ብዙዎቹም ባሕር ውስጥ እየሰጠሙ ማለቃቸውም አሁንም ቢሆን የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። ለዚያውም ጉዞው ቢሳካላቸው እንኳ የሰደተኛን ጎርፍ ለመግታት ደምባቸውን እያጠበቁና ብዙዎችን ለማስወጣት ጥረታቸውን እያጠናከሩ በሄዱት የአውሮፓው ሕብረት አገሮች ተገን ለማግኘት ያላቸው ዕድል የመነመነ ሆኖ ነው የሚገኘው። በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ አገሮች የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት አጥቶ ዛሬ ነገ ልንባረር ነው ሲሉ ኑሯቸውን በሰቀቀን የሚገፉት ስደተኞች ጥቂቶች አይደሉም።
ኢጣሊያ ክ2004 ዓም ጀምሮ ወደ ደቡባዊ ጠረፏ ወደ ላምፔዱዛ ደሴት ከዘለቁት ስደተኞች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትን መልሳ ወደ ሊቢያ ልካለች። በአውሮፓው ሕብረት አገሮችም በሰሜናዊው አፍሪቃ መሸጋገሪያ አገሮች ስደተኞቹን ገትቶ ለመያዝ የሚያስችል ማከማቻ ሰፈር እንዲቆም በጀርመን የአገር ግዛት ሚኒስትር አቶ ቺሌይ የቀረበው ሃሣብ በዚያን ዓመት ብዙዎችን ሲያከራክር ነበር። የስደተኛውን ጎርፍ ለመግታት በሰሜናዊው አፍሪቃ መከማቻ ሰፈር ማቆም ይቻላል ተብሎ የቀረበው ሃሣብ የአውሮፓውን ሕብረት ያነጋገረና ማከራከሩን ይታወስ ነበር። ሃሣቡ በኢጣሊያና በአውስትሪያ ተደግፍ ነበር። ነገርግን በተቀሩት የሕብረቱ ዓባል ሃገራት ለምሳሌ በፈረንሣይ ... ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም ነበር።
ስደተኞቹን በሰሜናዊው አፍሪቃ አገሮች በማከማቸት ዓለም አቀፉ ደምብ ያስቀመጠውን የደህንነት መስፈርት ማስከበር ይቻላል ወይ?
የተጠቀሱት ሃገራት የሰብዓዊ መብት ይዞታስ እስከምን ድረስ ነው?
እነዚህ ጥያቄዎች በቀላሉ ምላሽ ለማግኘት የሚችሉ ሆነው አይገኙም። በወቅቱ ጎልቶ የሚታየው ስደተኛውን በማከማቸት አጠቃላዩን የስደተኛ ጎርፍ ሊገታ መቻሉ አጠያያቂ መሆኑን ነው። የስደቱን ችግርና መንስዔ ከመሠረቱ ሊያስወግድ መብቃቱም ሲበዛ ያጠራጥራል። እርግጥ በመስከረም 2001 ዓ.ም. አሜሪካ ውስጥ የሽብርተኞች ጥቃት ደርሶ የዓለምን ገጽታ በሰፊው ከለወጠ ወዲህ በአውሮፓም የጸጥታ ጥበቃውና የሕብረቱን የውጭ ድንበር አስተማማኝ የማድረጉ ግፊት እየጠነከረ ነው የመጣው። ሆኖም ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች እንደሚያደርጉት የስደተኛውን ጉዳይ ሽብርን ከመቋቋሙ ጥረት ጋር ማዛመዱ ተገቢነት አይኖረውም።
ይህን መሰሉን አስተሳሰብ ከሚያራምዱት ፖለቲከኞች መካከል ለአውሮፓ ሕብረት ኮሚሢዮን በፍርድ ኮሜሣርነት የታጩት ኢጣሊያዊው ክርስቲያን ዴሞክራት ሮኮ ቡቲልዮኔ ይገኙበት ነበር። ቡቲልዮኔ የኮሚሢዮኑ ሥልጣን ጸድቆ ብራስልስ ውስጥ መቀመጫ ከያዙ ወደፊት የአውሮፓው ሕብረት የጸጥታና የድንበር ጥበቃ ጉዳይ ሃላፊም ሊሆኑ ይችሉ ነበር። ቀደምታቸው የፖርቱጋሉ ተወላጅ አንቶኒዮ ቪቶሪኖ በአንጻሩ እነዚህን ዘርፎች የጠቀለለ ሰፊ ሥልጣን አልነበራቸውም። የኢጣሊያው ወግ አጥባቂ ባለሥልጣን ሕገ-ወጡ የስደተኞች እንቅስቃሴ ሊገታ ይገባዋል ባይ እንደመሆናቸው መጠን በሕብረቱ ኮሚሢዮን ውስጥ ይህንኑ ዓላማቸውን ካራመዱ ክርክሩ ይበልጥ መጠናከሩ የማይቀር ነው። አውሮፓ ቢቀር በሃሣብ በጉዳዩ ለሁለት የመከፈል አዝማሚያ ነው የሚታይባት። ብራስልስ ውስጥ የሕብረቱ ዓባል ሃገራት የግራ ክንፍ ፖለቲካ ወገን የኢጣሊያው ዕጩ ኮሜሣርና የመሰሎቻቸው አመለካከት ገና ከጅምሩ እንዳልተዋጠለት ሰሞኑን በግልጽ አሣይቷል።
በጀርመኑ አገር ግዛት ሚኒስትር ኦቶ ቺሊይ የተቀሰቀሰው በሰሜናዊው አፍሪቃ ስደተኞችን ማከማቻ መፍጠርና በዚያው የመገደብ ሃሣብ ለነገሩ ላይ ላዩን ቀላል ነገር ቢመስልም ተቀባይነት ቢያገኝ በአውሮፓ ጸንቶ የቆየውን የስደተኞች ተገን መብት ከመሠረቱ ሊለውጥ የሚችል ነው። ራሳቸው ኦቶ ቺሊይ ያሰቡት ገቢር ቢሆን በዚህ በጀርመን የፖለቲካ ተገን የመጠየቁ መሠረታዊ መብት አስፈላጊ አይሆንም ሲሉ ነው የተናገሩት። ይህ ሃሣብ የጀኔቫውን የስደተኛ መብት ጥበቃ ውል የሚጻረር በመሆኑ በዚህ በጀርመን በብዙዎች ሲነቀፍ የአውሮፓው ሕብረት ኮሚሢዮንም ተቃውሞታል። ለዚህም ነበር የሕብረቱ አገር ግዛት ሚኒስትሮች በቅርቡ ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ጉዳዩን ከማንሳት ይልቅ በስተጀርባ መተዉ የተመረጠው።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መብት ጥበቃ ውል ከተፈረመ ሃምሣ ዓመታት አልፎታል። ከዚያን በፊት ተመሳሳይ ያልታየለት ውል ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለስደት ለዳረጋቸው አውሮፓውያን ዕርዳታና ተገን ለመስጠት በጊዜው የተደረገው ጥረት ውጤት ነበር። ጀኔቫ ላይ ተቀማጭ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኛ መርጃ ተቋም አፈ-ቀላጤ ሩፐርት ኮልቪል መለስ ብላው እንደሚያስታውሱት ውሉን የተለየ ትርጉም የሚሰጠው በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለስደተኞች መብት ጥበቃ ዓለምአቀፍ ጽናት ያለው ሕግ ለማስፈን መብቃቱ ነው። ይህ ደግሞ ወሣኝ ጉዳይ ነበር። የስደተኞች መብት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊከበር የሚችለው የዓለም መንግሥታትን ግዴታ ላይ የሚጥል የጥበቃ ዋስትና ሲኖር ብቻ በመሆኑ። ይህ ሃቅ ትናንት ጽናት ነበረው፤ ዛሬም ይኖረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኛ መብት ጥበቃ ውል በመጀመሪያ በአውሮፓ ብቻ ጸንቶ ከቆየ ከ16 ዓመታት በኋላ እ.ኢ.አ. በ1967 ነበር በዓለምአቀፍ ደረጃ ሊጸና የበቃው። እስከዛሬ 140 የዓለም መንግሥታት ሲያጸድቁት በጅምሩ ውሉ ላይ የሰፈሩት መሠረታዊ አንቀጾች፤ ለምሳሌ ያህል ስደተኛ የሚለው ቃል አተረጓጎም ራሱ ዛሬም ሳይቀየሩ እንደጸኑ ናቸው። በዚሁ ውል መሠረት ስደተኛ ተብሎ የሚቆጠረው በዘር፣ በሃይማኖት፣ በነገድ፣ በማሕበራዊና በፖለቲካ አሰላለፉ የመሳደድ ጭብጥ ፍርሃቻ ስላለው አገሩን መልቀቅ የተገደደ ማንኛውም ዜጋ ነው። የትኛውም ስደተኛ አደጋ እስካለበት ድረስ ያለውዴታው ወደ ትውልድ አገሩ መጋዝ የለበትም የሚለው አንቀጽም አንዱ እጅግ ጠቃሚና መሠረታዊ ዓላማ ሆኖ ይገኛል። ስደተኞች ተገን አግኝተው በሰፈሩበት አገር የመሥራት፣ ነጻ ሆኖ የመንቀሳቀስ፣ የትምሕርትና የሃይማኖት ነጻነት ያላቸው መሆኑም በማያሻማ ሁኔታ የተቀመጠ ጉዳይ ነው።
እንግዲህ በሰሜን አፍሪቃ መገደቢያ ሰፈር ለመትከል በአውሮፓ የተጸነሰው ሃሣብ ይህን ሁሉ መስፈርት ሳይጋፋ ሊያልፍ የሚችል አይሆንም። እርግጥ ዛሬ የስደቱ መንስዔ ምክንያትም ሆነ የፈለሣው ባሕርይ ከቀድሞው እጅግ እየተለወጠ መጥቷል። ከሃምሣ ዓመታት በፊት የጀኔቫው ውል ሲሰፍን በመሠረቱ ያተኮረው በፖለቲካ ምክንያት በሚሳደዱ ተገን ፈላጊዎች ላይ ነበር። ዛሬም በፖለቲካ አመለካከታቸው የሚሳደዱና ተገን የሚሹ የጭቆና ሰለቦች አይጥፉ እንጂ አብዛኛው ስደተኛ በኤኮኖሚ ችግር፤ ማለት በረሃብና በጦርነት የተነሣ አካባቢውን እየለቀቀ የሚፈልስ ሆኗል። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን የፖለቲካ ጭቆናና ፍትህ-አልባ የአገዛዝ ዘይቤ የፈጠረው ችግር ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ስደተኞችን መገደቢያና ማስፈሪያ ይታነጽባቸው በተባሉት ሊቢያን በመሳሰሰሉት አገሮችም ፍትሃዊ ሥርዓት አለ ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም።
ለዚህም ነው ሁለቱን የስደት ምክንያቶች የሚለያያቸውንና አንድ የሚያደርጋቸንም ምክንያት በሚገባ በማጤን ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት መጣሩ ግድ የሚሆነው። ጉዳዩ የሚመለከተው የበላይ ባለሥልጣን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ተቋም በአንድ በኩል መሠረታዊ ዓላማው እንዳይዛባ መታገልና በሌላ በኩልም ለምሳሌ ከአውሮፓው ሕብረት ጋር የተለወጠውን ሁኔታ ያጤነ ትብብር በማራመድ ተልዕኮውን መወጣት ይጠበቅበታል። ጉዳዩ ውስብስብ ሊሆን ይችላል። የሆነው ሆኖ ግን የስደተኞች ሰብዓዊ መብት ዛሬም ነገም እንደትናንት ሁሉ ሊታጠፍ የማይገባው ጉዳይ ነው።
በአውሮፓ ለፖለቲካም ሆነ ዛሬ በተለይ ቁጥራቸው ለተበራከተው የኤኮኖሚ ስደተኞች ጎርፍ ማየል ምክንያቱ ጭቆና፣ ድህነት፣ የመብትና የልማት ዕጦት መሆኑ በማያሻማ ሁኔታ ይታወቃል። ለነገሩ የበለጸገው ዓለም በታዳጊ አገሮች ላይ የተጫነውን ዕዳ በማቃለል ለልማት አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር በተደጋጋሚ ቃል ገብቷል። የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድም ከፍ አድርጎ ያስቀመጠው የታዳጊ አገሮችን ልማት በማፋጠን ድህነትን በተወሰኑ ዓመታት በከፊል የመቀነሱን ዓላማ ነው። ይሁን እንጂ ቃልና ተግባር የሚጣጣሙ ሆነው አይገኙም። የዕዳ ምሕረቱን ጉዳይ ካነሣን አይቀር ይህ ከንቱ ውዳሴ መሆኑን ሰሞኑን ዋሺንግተን ላይ ተካሂዶ የነበረው የሰባቱ በኤኮኖሚ ልማት የበለጸጉ ቀደምት መንግሥታት የ G-7 መሪዎች ጉባዔ እንደገና አሣይቷል።
በአውሮፓ የኤኮኖሚ ስደተኞችን ጎርፍ ለመግታት ከተፈለገ እነዚሁ በሚመነጩባቸው አገሮች ጦርነትና የፖለቲካ ጭቆና እንዲወገድ፣ ፍትህና ፍትሃዊ የአስተዳደር ዘይቤ እንዲሰፍን፤ በአጠቃላይ ሰብዓዊ መብቶች በውል እንዲከበሩ የዓለም ሕብረተሰብ ለስሙ ከሚሰነዘር ሃዘኔታ አልፎ በተጨባጭ ድርሻውን ለመወጣት መነሣት ይኖርበታል። ሕብረተሰባዊ ሰላምና የኤኮኖሚ ዕድገት ገሃድ መሆን እስካልቻለ ድረስ ግን ስደተኛ ይኖራል፤ ወደ ምዕራቡ ዓለም የሚደረገውም ፈለሣ በየጊዜው መልኩን ይለዋውጥ እንደሆን እንጂ ቀጣይ ነው የሚሆነው። በሰሜን አፍሪቃም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች ማጎሪያ መሰል ሰፈር ማነጹ ስደተኞችን ከራስ ደጃፍ በማራቅ ጊዜያዊ የሕሊና ዕረፍት ለማግኘት ካልሆነ በስተቀር መፍትሄ ይሆናል ብሎ ማሰቡ ከንቱ ነው። ከምዕራቡ የዴሞክራሲ ሕብረተሰብ የሞራል መስፈርት የሚጣጣምም አይሆንም።