lunedì

ለፈገግታ (ክፍል 2)

በኢሜልና በኮሜንት ከደረሱን ውስጥ



ክዚህ በታች ያለው ፅሁፍ በየጊዜው በኢሜል እና በኮሜንት የደረሱንን አሰባስበን እና መርጠን ያወጣናቸው ቀልዶች ናቸው። ለገፁ ቅንብብር እንዲያመቸን በማለት በፅሁፋችሁ ላይ የነበሩትን ተጨማሪ መልዕክቶችና ሰላምታችሁን ከውስጡ በመለያየት ቀልዶቹን ብቻ እንዲወጡ አድርገናል። ለወደፊትም አስፈላጊውን ብቻ ከጽሁፉ ውስጥ በመምረጥ ከስማችሁ ጋር እንዲወጣ ይሆናል።





አገር ቤት ውስጥ የፈረንችና የሀበሻ ዶሮ ይጣላሉ። ጥላቸው የተጀመረው ከፈረንጇ ዶሮ ነው። የፈረንጇ ዶሮ የእኔ እንቁላል ትልቅ ስለሆነ በ 50ሳ ይሸጣል ያንቺ ግን ትንሽ ስለሆነ በ 40ሣ ይሸጣል እያሉ ሲከራረሩ ሀበሻዋ ዶሮ ትናደድና
"እኔ ለ 10ሣንቲም ብዬ ቂጤን አላሰፋም?" አለች ይባላል
ዮናስ (ቦሎኛ)


አንዱ አበሻ ልጅ ዋና ለመማር piscina ይሄድና ሲዋኝ ይሰምጥና መውጣት ያቅተዋል። ከዚያ እዚያው ውሀ ውስጥ እየተንፈራገጠ በአጠገቡ ሰው እንዳለ ሲመለከት አንድ ጠና ያሉ ሰውዬ በpiscinaው አጠገብ ሲያልፉ ያያል። የሰጠመውም ልጅ "አባባ aiutare! ... Io morire! ... እያለ ሲጮህ ሰውዬው ደግሞ ዞር አሉና እንዲህ አሉት " ጣሊያንኛ ከመማርህ በፊት ዋና አትማርም ነበር?" አሉት።
Endale T/Mariam (Roma)


3 ሆነው ባጠፉት ከባድ ወንጀል መሰረት ሶስቱም የሞት ፍርድ ይፈረድባቸዋል አሉ:: እናም በምን መንገድ እንደሚሞቱ የመምረጥ እድሉ ይሰጣቸዋል:: በመርዝ፣ በጋዝ ታፍኖ፣ በስቅላት፣ በጥይት፣ በኤድስ ቫይረስ መወጋት፣
1ኛው "በስቅላት" አለ።
2ኛው "በጥይት" አለ።
3ኛው "በኤድስ ቫይረስ መወጋት" አለ።
ታዲያ ፍርዱ አልቆ ከተከናወነ በኋላ ይሄው 3ኛው ቫይረሱ የተወጋበትን ቂጡን እያሻሸ ምን አለ መሰላቹ ...
"ሸወድኩዋቸው እኮ!" አለ።
እንዴት? ሲሉት ጊዜ
"ኮንደም አድርጌያለሁ"
አብራሃም (ቦሎኛ)


በሽተኛው ዓይን ዶክተር ጋ ይሄዳል:: ዶክተሩ ከመረመረው በሁዋላ ዓይኑ መቀየር እንዳለበት አምኖ ለጊዜው የተገኘው የድመት ዓይን ስለነበረ በዚሁ ይቀይርለታል::
ዶክተር :- "እህ አሁንስ በደንብ ታያለህ ? ንገረኝ ..." ማለት
በሽተኛ :- "በሚገባ ዶክተር:: አያለሁ ብሎ መመለስ"
ዶክተር :- "ምን ይታይሃል?" ሌላ ጥያቄ
በሽተኛ :- "ዓይጥ ነዋ::" ብሎ ዕርፍ
ከቤ


3ት እብዶች ከአማኑኤል ሆስፒታል ሸውደው ለማምለጥ ወስነው መውጫው በር ሲደርሱ በአጋጣሚ ዘበኞቹ የሉም ነበር። በቃ ዘበኞቹ የሉም ማንን እንሸውዳለን? ብለው ወደ ውስጥ ተመለሱ::
Ted 85


ተማሪ :- ባልሰራሁት ስራ ይቀጡኛል ይገርፉኛል?"
ቲቸር :- "እረ እኔቴ እንዴት ሰው ባልሰራው ስራ ይቀጣል? … ይህማ የማይሆን ነገር ነው አልገርፍህም!"
ተማሪ :- "ይምሉልኛል?"
ቲቸር :- "ሙ ት ልጄ! አልመታህም! መድሀኒያለምን! ባልሰራኸው ስራ በፍፁም አትመታም! እንዴ!!!"
ተማሪ :- "እንግዲያውስ ቲቸር አመሰግናለው ዛሬ homework አልሰራሁም"
ከቤ


ሁለት እብዶች ናቸው እየሄዱ ይጨዋወታሉ። አንዱ እብድ አንድ በጣም ትልቅ ተራራ አየና ያንን ተራራ እንግፋው አለው። ለሌላኛው እሱም እሺ ብሎ ላት ላት እስኪላቸው ድረስ ጃኬታቸውን አውልቀው ይገፋሉ። እንደአጋጣሚ አንዱ ሞጭላፋ አይቶቸው በልቡ እየሳቀባቸው ጃኬታቸውን ሞጨለፈው። ትንሽ ቆይተው አንዱ እብድ ዞር ሲል ጃኬታቸው የለም።
"አንተ ጃኬታችንስ?" ቢለው
ያኛው ደሞ ትንሽ የባሰበት ስለነበር "እንዴ አንተ ደሞ በጣም ብዙ እየገፋን በጣም ርቀን ሰለሄድንኮ ነው ማየት ያልቻልነው" አለው ይባላል
ከቤ


ባል ሊሞት ሲያጣጥር ሚስቱን ይጠራና እኔ ስሞት ብዙ ማዘን የለብሽም:: ያለባልም መቅረት የለብሽም:: እንዲያውም ጎረቤታችንን ዘነበን አግቢ:: አደራ ይላታል:: ሚስትም መለስ አድርጋ እንዴት እንዲህ ትለኛለህ? እኔ ፍቅር እንጂ የወንድ ቃር የያዘኝ መስሎሀል? ደግሞ ባገባስ እንዴት ዘነበን አገባለሁ እሱ ስንት ዘመን ሊገልህ የሚፈልግ ጠላትህ አይደል? ብላ ታፈጥበታለች:: ባልም እያቃሰተ ጥላቴማ መሆኑን መች አጣሁት እንደኔው ጥብስ እድርግርሽ እንድትገይልኝ ነበር እንጂ ብሏት እርፍ::
ቅጣው ሀ/ማሪያም (German)


ሁለት እብዶች ተገናኝተው በመንገድ እየተጫወቱ ሲሄዱ አንድ ነገር ተቆልሎ ይመለከታሉ:: እነሱም ሁኔታው ገርሟቸው አጎንብሰው ሲመራመሩ ሁኔታውን ለመረዳት ስላልቻሉ ሁለቱም በጣታቸው ደንቁለው ቀመሱት። ወደ አፍንጫቸው ጠጋ አድርገው ሲያሸቱት አር መሆኑን ሲያውቁ ጊዜ "እፍ እፍ እፍ እፍ እንኳን በእግራችን ያልረገጥነው" አሉ ይባላል።
ዝናሽ


ሁለት ጓደኛማቾች ቁጭ ብለው ጫት እየቃሙ ብው ብለው መርቅነዋል::
አንደኛው በድንገት ብድግ አለና "በዓለም ላይ ያለውን ወርቅ በሙሉ ልገዛው ነው" ሲል
ቀበል አድርጎ "አይ አልሸጥም" አለው::
አብራሃም (ቦሎኛ)

venerdì

ከጣሊያን መንግስት የተሰጠ የነፃ እድል ትምህርት

15/04/2008
ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ
የጣሊያን መንግስት መጪዉን የትምህርት ዘመን ማለትም ከሰፕቴምበር 2008 እስከ ኦክቶበር 2009 ያለዉን የትምህርት አመት አስመልክቶ የዉጭ ሀገር ዜጎችን አወዳድሮ ለአሸናፊዎቹ የነፃ እድል ትምህርት ማለትም እስኮላርሺፕ ለመስጠት አቅዶ በነበረዉ ፕላን መሰረት ሰሞኑን በአገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የነፃ እድል ትምህርት ማስታወቂያ ማዉጣቱ ታዉቆአል::
ለጊዜዉ የነፃ እድል ትምህርቱ ለስንት ተማሪዎች ሊሰጥ እንደታቀደና የእስኮላርሺፑ ትክክለኛ ቁጥር ስንት እንደሆነ በግልፅ የተሰጠ ዝርዝር መግለጫ ባይኖርም እድሉ ሁሉንም የትምህርት ዘርፎች እንደሚያጠቃልል ከወጣዉ ማስታወቂያ መረዳት ተችሏል::
መወዳደር የሚፈልግ ሁሉ በቀጥታ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ወይንም በየአቅራቢያዉ ያሉትን የጣሊያን አምባሲ ጽ/ቤት በቀጥታ በመጠየቅ አስፈላጊዉን መልስ ማግኘት ይችላል::

ለመወዳደር ምን ያስፈልጋል?
- የትምህርት ደረጃን የሚገልፅ ማስረጃ;
- እድሜዉ ከ 35 አመት በላይ ያልሆነ

የትምህርት ዘርፎች
- የአጭር ጊዜ የጣሊያንኛ ቋንቋ ትምህርት;
- የተለያዩ የዩኒቨርስቲ አጫጭር የሙያ ነክ ኮርሶች;
- የተለያዩ መካከለኛ የሙያ ማሻሻያ ኮርሶች;
- በተለያዩ መስኮች የዲግሪ ትምህርት;
- በተለያዩ መስኮች ከመጀመሪያ ዲግሪ ቀጥሎ ያሉትን ትምህርቶች ማለትም የፖስት ግራጁዌት እስከ ዶክትሬት ድረስ;
- ባህላዊና ሙዚቃዊ አጫጭርና የረጅም ጊዜ ትምህርቶች;
- እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል::
መልካም እድል ለሁላችሁ

giovedì

“ሐሰትና ስንቅ እያደር ይቀላል”

ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ 18.02.08

በአንድ በዴሞክራሲ በበለፀገና ባደገ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት የወደፊት ፕሮግራም ዝግጅት መሰረት በአገሪቱ በሚደረገዉ የፖለቲካ ምርጫ ለመካፈል ቅስቀሳ የማካሄድና አላማቸዉም ጭምር ምን እንደሆነ በትክክል ለመራጩ ሕዝብ የማሳወቅና የማስረዳት ግዴታ ሲኖርባቸዉ በአንፃሩ መብታቸዉም የተጠበቀ እንደሆነ ይታወቃል:: ይህንንም ስርአትና ደንብ የዴሞክራሲ ጨዋታ (il gioco delle regole della democrazia) በማለት ይጠሩታል::
በዚህ በጣሊያን አገርም እንደ አዉሮፓዉያን አቆጣጠር የፊታችን 13 እና 14 አፕሪል 2008 በሚደረገዉ የፖለቲካ ምርጫ ላይ ለመካፈል የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የዉጭ ሀገር ዜጋዉን በተመለከተ የማስፈራራት ዘመቻ፣ ቅስቀሳ፣ ፕሮፖጋንዳና ሽብርም ጭምር በመንዛት ላይ እንደሆኑ በገሃድ ይታያል::
ከዚህ ቀጥሎ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ዝርዝርና ፕሮግራማቸዉን በተለይም በጣሊያን አገር ነዋሪ ለሆኑት አንባቢያን ሊጠቅም ይችላል በማለት ባጭሩ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፣
ስኒስትራ አርኮባሌኖ (Sinistra Arcobaleno):
ባጠቃላይ በተግባር መተርጎም ቢችል የዉጭ አገር ዜጋዉን መብት ሙሉ በሙሉ ሊያስከብር የሚችል ፕሮግራም መስሎ ይታያል;
የዴሞክራትክ ፓርቲ (Partito Democratico):
እምግሬሽንን መቆጣጠር፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት የጊዜ ገደብ ይራዘም፣ መብትና ግዴታን ማሳወቅ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት ማስከበር፣ ጣሊያን አገር ለሚወለዱት ሁሉ የዜግነት መብት ማስከበር፣ ሕገወጥ ወይንም ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጎችን ማባረር;
እታሊያ ደይ ቫሎሪ (Italia dei Valori):
ወንጀልን ማጥፋት፣ ሕገወጥ ወይንም ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጎችን ወዲያዉኑ ማባረር; ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጋ ወደ አገሩ ተልኮ እስር ቤት ይቆያል;
ዩኒዮኔ ዲ ቸንትሮ (Unione di Centro); ወንጀልን ማጥፋት፣ የጣሊያን ዜጎችን ህይወት መንከባከብ፣ ለቁጥጥር ይሆን ዘንድ ለፖሊስ ተገቢዉን መሳሪያ ማቅረብ፣ እምግሬሽንን መቆጣጠር፣ ስራና መኖሪያ ቤት ያለዉ ታክስ በአግባቡ የከፈለ የዉጭ አገር ዜጋ የመኖር መብቱ ይከበራል;
ፖፖሎ ደላ ሊበርታ (Popolo della Libertà)
ወንጀልን ማጥፋት፣ ሕገወጥ ወይንም ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጎችን ወዲያዉኑ ማባረር; እንተርናሽናል ወንጀልን መቆጣጠር፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ለሌላቸዉ እንዳይሰጥ፣ ጊዜያዊ እስር ቤቶችን ቁጥር መጨመር፣ ስራና የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ተለያይተዉ አይታዩም በመሆኑም ስራ የሌለዉ የዉጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀቱ አይታደስም;
ላ ዴስትራ (La destra)
በጣሊያን አገር የሚገኝ ማንኛዉም የዉጭ አገር ዜጋ ወደ መጣበት ትዉልድ አገሩ ይመለስ፣ ወንጀልን ማጥፋት፣ ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጋ ወደ አገሩ ተልኮ እስር ቤት ይቆያል፣ በደንብ መቆጣጠር ይቻል ዘንድ የዉጭ አገር ዜጋ ሁሉ አሻራ የመነሳት ግዴታ አለበት፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ለሌላቸዉ እንዳይሰጥ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳይፈቀድ;
ሌጋ ኖርድ (Lega Nord)
ስራና የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ተለያይተዉ አይታዩም፣ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ገንዘብ ማሳየት ያስፈልጋል ገንዘቡም እንዴት እንደተገኘ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፣ በዉጭ አገር ዜጋዉ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር መደረግ ይኖርበታል፣ በመንግስት የመኖሪያ ቤቶች ዉስጥ በሚኖሩት ቤቱ በትክክለኛ ህጋዊ መንገድ እንደተሰጣቸዉ አትብቆ መቆጣጠር፣ ማንኛዉም መንግስታዊ እርዳታ ለዉጭ አገር ዜጋ እንዳይፈቀድ እና የመሳሰሉትን ይጠቅሳል::
እንግዲህ ባጠቃላይ የፓርቲዎቹን ፕሮግራም ስንመለከት ከመጀመሪያዉ በስተቀር ሁሉም የጋራ ቀመራቸዉ የዉጭ አገር ዜጋዉ ሁሉ አደገኛ እንደሆነ በማስመሰል በህብረተሰቡ ላይ ፍርሃትን መዝራት ሆኖአል::
ዉሸትና ስንቅ እያደር ይቀላል እንደተባለዉ ከምርጫዉ በኋላ ሁሉም ይረሳና እንደነበረዉ ይቀጥላል ብቻ ለማየት ያብቃን::

venerdì

በእርሻና ቱሪዝም የስራ መስክ ሰማኒያ ሺህ የዉጭ አገር ዜጎች ጣሊያን እንዲገቡ ተፈቀደ


ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ እንዳይሆን
Decreto flussi 80.000 ingressi stagionali anno 2008
ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ
Bologna, 03 gennaio 2008
በመጀመሪያ ደረጃ እንኳን ለ2008 በሰላም አደረሳችሁ በማለት የያዝነዉ የሥራ አመት የጤና; የሰላም; የደስታና የብልጽግና ይሆን ዘንድ መልካምና ዘላለማዊ ምኞቴን በዚህ አጋጣሚ ለአንባቢያን ለመግለጽ እወዳለሁ::
“ያለማወቅ ከምንም አያድንም” ከሚል ርእስ በመነሳት በተለያዩ ወቅቶች ከዚህ ዌብ ሳይት አዘጋጅ ጋር ባደረግኩት የስራ ትብብር ከተለያዩ አገሮች ከጣሊያንም ሆነ በተለይም ከጣሊያን አገር ዉጪ ከብዙዎቻችሁ ለተላኩልኝ የምስጋና መግለጫና የማበረታቻ መልእክቶች ለያንዳንዳችሁ በግል መመለስ ቢያዳግተኝም ሁላችሁንም ይህንን ጽሑፍ ምክንያት በማድረግ በሰፊዉ አመሰግናለሁ እላለሁ::
ወደ አርእስቴ ልመለስና በእርሻና ቱሪዝም የስራ መስክ ሰማኒያ ሺህ ለሚሆኑ የዉጭ አገር ዜጎች ጊዜያዊ የስራ እድል ይከፍታል ተብሎ የሚጠበቀዉ የጣሊያን መንግስት የኢምግሬሽን ሕግ በዛሬዉ እለት በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ይወጣል ተብሎ በጉጉት ይጠበቃል::
የዉጭ አገር ዜጋዉን ሰራተኛ ለመቅጠር ማንኛዉም ቀጣሪ ግለሰብም ሆነ ድርጅት የቅጥር ፎርሙን ቅጽ ከመሙላቱ በፊት የአገር ዉስጥ ምንስቴር በሚቀጥለዉ ወር (ፌብርዋሪ) መጀመሪያ አካባቢ ያወጣል ተብሎ የሚጠበቀዉን መመሪያና ሰፊ መግለጫ መጠበቅ ይኖርበታል::
የሚመጡትም ሰራተኞች ከተለያዩ አገሮች ሲሆን በተለይም ክሰርቢያ; ከሞንተኔግሮ; ከቦዝኒያ; ከማቼዶኒያ; ከክሮዋዝያ; ከሕንድ; ከፓክስታን; ከባንግላደሽ; ከስሪላንካ; ከኡክራይና; ከቱኒዚያ; ከአልባኒያ; ከሞሮኮ; ከሞልዳቪያና ከግብጽ በብዛት ሊመጡ እንደሚችሉ ተጠቅሷል::
ካሁን ቀደም ማለትም ባለፉት አመታት እ.አ.አ. በ2005; በ2006 እና በ2007 ለተመሳሳይ ስራ ጣሊያን አገር እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዉ ሰርተዉ ወደያገራቸዉ ተመልሰዉ የነበሩት ሁሉ ለመምጣት ቅድሚያ ሊሰጣቸዉ እንደሚችልም ጭምር በሕጉ ላይ ተጠቅሷል::
በዚህም አመት እንዳለፈዉ ጊዜ የማመልከቻዉ ቅጽ የሚሞላዉ በእንተርኔት መሆኑም ጭምር ተገልጿል::
“ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” እንዳይሆን ጉዳዩን መከታተል የሚፈልግ ካለ ስር ደርሶ ከመራወጥና ከመንገላተት ይድናል ብዬ በማለት ይህቺን መልእክት አስተላልፋለሁ::
በሚቀጥለዉ እስክንገናኝ መልካም ወቅት
አድራሻ: Dr. Zeleke Eresso
P.O.Box 839
40100 – Bologna
ITALY
Zeleke_eresso@yahoo.it
Tel. 3395764139





giovedì

የጣሊያን ምንስትሮች ምክር ቤት ለ 80.000 ሺህ የዉጭ አገር ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ፈቃድ ሕግ አፀደቀ


አ.አ.አ. በ 8/11/2007 የጣሊያን ምንስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ባደረገዉ ስብሰባ ሰማኒያ ሺህ ያህል ለሚሆኑ የዉጭ አገር ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ፈቃድ ማግኘት እንዲችሉ አዲስ ሕግ አፀደቀ::
ይህ አዲስ ሕግ ተግባራዊ የሚሆነዉ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣ በኋላ ስለሆነ ትንሽ ጊዜ መጠበቅ ያስፈልጋል::
የሚመጡትም የዉጭ አገር ዜጎች የስራ ክፍል በእርሻና በቱሪዝም ሲሆን በብዛት የሚመጡትም ከሚከተሉት አገሮች ይሆናል:-
- ሰርቢያ;
- ቦዝኒያ፣
- የቀድሞዉ ይዩጎዝላቪያ ረፑብሊክ ማቸዶኒያ;
- ክሮዋዝያ;
- ህንድ;
- ፓክስታን;
- ባንግላደሽ;
- ስሪላንካ;
- ዩክራይና;
- ቱኒዝያ;
- አልባኒያ;
- ሞሮኮ;
- ሞልዳቪያ;
- ግብፅ ወዘተ ናቸዉ:
በ 2005፣ 2006፣ 2007 የስራ አመት በጊዜያዊ ሰራተኛነት ጣሊያን አገር የመጡ ግለሰቦች ሁሉ ማመልከቻቸዉን ማቅረብ ይችላሉ::
የማመልከቻ ማቅረቢያዉ ሁኔታ ካሁን ቀደም እንደጠቀስኩት በእንተርኔት ይሆናል::

ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ


mercoledì

የጣሊያን የምንስትሮች ምክር ቤት 170.000 የዉጭ ሀገር ስራ ፈላጊዎች ጣሊያን አገር መግባት ይችሉ ዘንድ ሰሞኑን አዲስ ህግ አረቀቀ


ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ
14 11 2007

ካሁን በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለፅኩት ሁሉ የጣሊያን መንግስት በየአመቱ ምን ያህል የዉጭ ሀገር ዜጎች ሰራተኞች ለሀገሪቱ ለስራ እንደሚያስፈልጉ በመተመን ጣሊያን እንዲገቡ በየጊዜዉ የአመቱን ህግ ይደነግጋል:: በመሆኑም በዚህ በያዝነዉ የአመት በጀት ፕሮግራም መሰረት በአንቀፅ 2 እንደተመለከተዉ የጣሊያን መንግስት 170.000 ለሚሆኑ የዉጭ ሀገር ዜጎች ማለትም የአዉሮፓ ህብረት አባል አገር ዜጎችን ሳይጨምር በስራ ምክንያት ጣሊያን አገር መግባት የሚያስችል አዲስ ህግ አዉጥቶአል::

የህጉንም ይዘት አጠር ባለ መልኩ ለአንባቢያን ለማስቀመጥ ያህል:-
በመጀመሪያ ደረጃ በህጉ አንቀፅ 2 ላይ እንደተጠቀሰዉ ሁሉ ቁጥራቸዉ 47.100 ያህል ሰራተኞች ከተለያዩ አገሮች ማለትም ክጣሊያን ጋር የቅርብ የጋራ ስምምነት ተፈራርመዉ ከነበሩት ከሚከተሉት አገሮች የሚመጡ እንደሆኑ ተጠቅሷል:-
- ከአልባንያ 4.500;
- ከአልጀሪያ 1.000;
- ከባንግላደሽ 3.000;
- ከግብፅ 8.000;
- ከፍሊፒን 5.000;
- ከጋና 1.000;
- ከሞሮኮ 4.500;
- ከሞልዳቪያ 6.500;
- ከናይጄሪያ 1.500;
- ከፓክስታን 1.000;
- ከሴኔጋል 1.000;
- ከሶማሊያ 100;
- ከስሪላንካ 3.500;
- ከቱኒዚያ 4.000;
- ከተቀሩት አገሮች 2.500::

የስራዉስ ምክንያትና መስክ ምን ምን ይሆናል?
- በቤት ሰራተኛነት 65.000;
- በህንፃ ስራ ሰራተኛነት 14.200;
- በከፍተኛ ትምህርት ተመርቀዉ የሙያ ሃላፊ የሆኑ 1.000;
- በሹፌርነት ልዩ የአዉሮፓ ሰርቲፊኬት ያላቸዉ 500;
- በአሳና ባህር ስራ ላይ 200;
- በተቀሩት የስራ መስኮች 30.000;
- ትምህርትን በስራ በመቀየር 3.000;
- በሙያ ኮርስ ስልጠና 1500;
- በትምህርት 2.500;
- እና በመሳሰሉት::

መቼ ማመልከት ይቻላል?
ይህ ህግ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በወጣ በአስራ አምስተኛዉ ቀኑ ማመልከት ይቻላል:: ማመልከቻዉን የሚያቀርበዉ ቀጣሪዉ ግለሰብ ፎርሙን እንተርኔት በመጠቀም መሙላት ይኖርበታል::
zeleke_eresso@yahoo.it
Tel. 3395764139

martedì

“የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል”


* ዶ/ር ዘለቀ እሬሶ*
... በአገራችን በኢትዮጵያ ገበያ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መተንተኑ በዚህ ወቅት አስፈላጊነቱ ጎልቶ ባይታየኝም እንዲያዉ ለማስታወስ ያህል ባጭሩ ገበያ ማለት ምርት አምራቹ ግለሰብ ወይንም ቡድን በተለይም የገጠሩ አርሶ አደር ክፍል ማንኛዉንም ያመረተዉን ጥሬ እቃ ለመሸጥ የሚያቀርብበት አማካይ ስፍራና ለኑሮዉ የሚያስፈልገዉን ለመግዛት የሚሄድበት ማእከላዊ ቦታ ነዉ:: ብቻ ባጠቃላይ እቃና ገንዘብ የመለዋወጫዉ ቦታ ገበያ በመባል ይጠራል:: በመሆኑም የተለያዩ የገበያ ስሞችን እንደነ ጉልት ገበያ፣ መርካቶ፣ እሁድ ገበያ፣ ቅዳሜ ገበያ፣ ሰኞ ገበያ፣ ማክሰኞ ገበያ ወዘተ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል::
... ከላይ እንደጀመርኩት ገበያ የእቃና የገንዘብ መለዋወጫ ቦታ ብቻ ሳይሆን የአገር ሽማግሌዎች የተጣሉ ግለሰቦችን በመጥራት የሚያስታርቁበት ስፍራም ነዉ:: በዚህ የገበያ ቀን ሌባዉንና አታላዩን ለመቆጣጠር ሲባል የጸጥታ አስከባሪዎች በገበያዉ ዉስጥ በመዞር አካባቢዉን ይቃኛሉ:: ይህም ለገበያዉ መልካም ፍጻሜ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል:: ህዝቡም በሰላም የሚፈልገዉን በመግዛትም ሆነ በመሸጥ የፈለገዉን አከናዉኖ ወደየቤቱ ይመለሳል::
... ማህበራዊ ኑሮን በተመለከተ ገበያ ጥቅሙ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ህብረተሰቡ ጥላቻን አስወግዶ ተፋቅሮ፣ ተሳስሮ፣ ተቻችሎ፣ ተረዳድቶና ተስማምቶ በአንድነት እንዲኖር በማድረግም ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል::
ታዲያ በዚህ በምንኖርበት አካባቢ ማለትም “በዉጭዉ አለም” የገበያ ሁኔታ መልኩና ይዘቱ በጣም ለየት ያለ ነዉ:: አንዳንድ እዚህ ነዋሪ የሆኑት የዉጭ ሀገር ዜጎችም የንግዱን አለም ተያይዘዉታል:: ቁጥራቸዉም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል:: የንግዱን ይዘትም በሁለት መልኩ ልናገናዝበዉ ይገባል:: በአንድ በኩል የሚያበረታታና እንደ ምሳሌ የሚወሰድ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ “የገበያ ግርግር ለሌባ ምቹ ነዉ” የሚለዉን የአያቶቻችንን አባባል የሚያስታዉሰን ይመስለኛል::
... እስቲ የመጀመሪያዉን ለመመልከት እንሞክር:: አንድ በዚህ አካባቢ ነዋሪ የሆነ የዉጭ ሀገር ዜጋ የሚኖርበትን ሀገር ቋንቋ፣ ባህልና የኑሮ ዘዴዉን ጠንቅቆ ከተረዳ ህጋዊ በሆነ መንገድ ሰርቶ ለመንግስት ደግሞ መክፈል የሚኖርበትን የስራ ግብር ከገበረና ከማንኛዉም ወንጀል ነጻ ከሆነ ግዴታዉን በሚገባ ተወጥቶአል ብሎ ማለት ይቻላል:: ይህም ከአንድ ጥሩ ነዉ ከሚባል ዜጋ የሚጠበቅ በጎ ስነምግባር ነዉ:: አብዛኛዉን ጊዜ የዉጭ ሀገር ዜጋ ይህን ግዴታዉን አጥብቆ መወጣት እንዳለበት ተደጋግሞ በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች እንደ ዉዳሴ ማሪያም ሲነገረዉ መብቱን በተመለከተ እንዲከበርለት በሚጠይቅበት ወቅት ግን መልሱ ሰምቶ እንዳልሰማ ይሆንና ግለሰቦችን ወደማይፈልጉት የወንጀል መንገድ ይመራቸዋል:: መብትና ግዴታ ተነጣጥለዉ የሚታዩ ሁለት ነገሮች መሆን የለባቸዉም::
... በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የግለሰቦች መብት አለመከበር ብዙ የሚያስከትላቸዉ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም:: የጸጥታ ችግር፣ የሌብነት፣ የማጭበርበር፣ የሽርሙጥና፣ የድራግ ሱስ ወዘተ ብቻ በአጠቃላይ “እንደምንም ገንዘብ ብቻ ላፍራ” የሚል መፈክር ተይዞ ይነሳና መጨረሻዉ ዉድቀት ከመሆንም ያልፍና ሰላማዊ ኑሮ ቀርቶ በምትኩ መፈራራትና ጥላቻ የመሳሰሉት ይነግሳሉ:: ብልጠትን፣ ማጭበርበርንና ዉሸትን መሰረት በማድረግ የሚሰራን ስራ እንደ ስራ ሊንቆጥረዉ አይገባም::
... በኢጣሊያን ሃገር ዉስጥ በግምት ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ የዉጭ ሐገር ዜጎች እንደሚኖሩ ይነገራል:: ይህ ቁጥር ብዙ መስሎ ቢታይም ከሌሎች የአዉሮፓ አገሮች ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ነዉ:: በተጨማሪ ለጊዜዉ ቁጥራቸዉ በትክክል የማይታወቅ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት የሌላቸዉ የድብቅ ስራ በመስራት ኑሮን ለመወጣት የሚታገሉም ጭምር እንዳሉ ነዉ::
... አንዳንድ የዜና ማሰራጫዎች አልፎ አልፎ የዉጭ ሃገር ዜጋን በተመለከተ ትክክለኛ ያልሆነ መልክት ያስተላልፋሉ:: የዉጭ ሃገር ዜጋንና ወንጀልን አጣምረዉ በማቅረብ የዉጭ ሃገር ዜጋዉን ሁሉ ወንጀለኛ አድርገዉ ያቀርባሉ:: በዚሁ የተሳሳተ መልክት የተነሳ በየመንገዱ “አሁንስ እነኚህ የዉጭ ሃገር ዜጎች በዙ ይዉጡልን” የሚሉትንና የመሳሰሉትን ዘረኛ ቃላት መስማቱ ጆሮዬ ዳባ ልበስ ሆኖአል:: ይህም እንግዳዉንና አስተናጋጁን አይጥና ድመት ሆነዉ የጎሪጥ እንዲተያዩ ያደርጋቸዋል::
... ለማጠቃለል ያህል በዚህ ብልጠትና እራስ ወዳድነት በበዛበት በተለይም ባሁኑ ወቅት የዉጭ ሀገር ዜጋዉ ከምን መጠንቀቅ አለበት:
... 1. በማሳወቅና በማስተማር ፋንታ “አንተ አታዉቅም፣ ቋንቋ አትችልም፣ እኔ እሰራልሀለሁ፣ እኔ አስብልሃለሁ” ከሚሉት የአፍ እርዳታ ሰጪዎች በሚገባ መጠንቀቅ;
... 2. በተቻለ መጠን ተደብቆ በጥቁር መስራትን ማስወገድና ለመንግስት አስፈላጊዉን የስራ ግብር በወቅቱ መክፈል;
... 3. በስራ የሚተዳደረዉ የዉጭ ሀገር ዜጋ እድሜ ገፍቶ ጡረታ እንዳለ በመረዳት አስፈላጊዉን የጡረታ ማስከበሪያ የታክስ ሁኔታ ከሚመለከተዉ መንግስታዊ አካል የራስን ሁኔታ መከታተል;
... 4. ትምህርትን በተመለከተ በመማር ላይ ያለዉ ትምህርቱ “ጊዜን ገዳይ ብቻ” እንዳይሆንበት ተጠንቅቆ ትምህርቱ እንዳበቃ ስራ ማግኘት የሚያስችለዉን የትምህርት አይነት መማር እንዳለበት ከሚያዉቁት ሰዎች ጠይቆ መረዳት;
... 5. ከዘረኝነት በሽታ፣ ከሃይማኖት የበላይነት፣ ከአጉል ፉክክር፣ ከማይጠቅም ምቀኝነት፣ ከማያሳድግ ሃሜትና አሉባልታ እና ከመሳሰሉት ኋላ ቀር አመለካከቶች በመራቅ ሰላማዊ ኑሮን ከሚያስፋፉ የህብረት ክፍሎች ጋር መተባበር;
... 6. ግዴታን ከተወጡ የግል መብትንም ለማስከበር መጣር::
በሚቀጥለዉ እስክንገናኝ መልካም ቆይታ


የፋሺስት ኢጣሊያ ግፍ አሁንም ያነጋግራል


19 07 2008
ከዛሬ 73 ዓመት በፊት የፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊት በኢትዮጵያኖች ላይ አሰቃቂ ግፍና ጭፍጨፋ መፈፀሙ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው። በወቅቱ የፋሺስት ሠራዊት በተጠቀመው የመርዝ ጋዝ ያደረሰው እልቂት ከፍተኛ ነበር። በዚያን ጊዜ የፋሺስት ሠራዊቱ የጦር አዛዥ ከነበሩት መካከል በጨካኝነቱ ለሚታወቀው ጄነራል አልፒኒ መታሰቢያ የተተከለው ሐውልት እስካሁን ድረስ እየተከበረ መገኘቱ አዲስ ውዝግብን ሊቀሰቅስ ችሏል።
በ1936 እ.ኤ.አ. በአልፒኒ ስም የቆመው ሐውልት በራሱ በአልፒኒ ምስል የተቀረፀ ነው። ይህ በሰሜን ኢጣሊያ የሚገኘው የአልፒኒ መታሰቢያ ሐውልትና በስሙ የሚጠራው መንገድም ”አልፒኒ ኖርዘን ኢታሊያ” የሚባል ነው። በኢትዮጵያውያኖች ላይ ጭፍጨፋን የመራ ግለሰብን እስካሁን ድረስ እንደ ጀግና ተቆጥሮ መከበሩ ብዙዎችን ያስደነቀና ያስደነገጠ ጉዳይ ሊሆን ችሏል። ሰሞኑን ወደ ሰሜን ኢጣሊያ አቅንተው የነበሩት በኢጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ግሩም አባይ በተመለከቱት ነገር እንደተገረሙ ተናግረዋል።
የአልፒኒን ሐውልት ያሠራው የፋሺስት ኢጣሊያ መሪ የነበረው ቤኒቶ ሙሶሎኒ ነበር። አልፒኒ በተለይ በጦርነቱ ወቅት የሚታወቅበት ፋሺስቱ ሠራዊት ዘረፋ እንዲያካሂድ፣ እንዲገድልና አስገድዶ እንዲደፍር ግልፅ ትዕዛዝ በመስጠቱ ነበር። እ.ኤ.አ. በ1936 የተተከለው የአልፒኒ መታሠቢያ ሐውልት፣ በዚያን ጊዜ ቢሆን ተቃዋሚ ያላጣ እና ይኸው ተቃውሞ ለበርካታ ዓመታትም ሳይቋረጥ ቆይቷል። በሐውልቱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት የተሰነዘረው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሳይጠናቀቅ በፊት ሲሆን፣ ከዚያም በተከታታይ በ1956፣ በ1959፣ በ1966 እና በ1979 ጥቃት ተሰንዝሮበት በከፊል ሊጎዳ ችሏል። በአሁኑ ወቅት በአልፒኒ ሐውልት ጉዳይ ላይ ተቃወሞውን እያቀረበ የሚገኘው 'sudtiroler schutzenbund' የተባለ የባህል ተቋም ነው። ይኸው ተቋም አምባሣደር ግሩም ዓባይን ወደ ሰሜን ኢጣሊያ “ሳውዝ ትሮይል” ጋብዞ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ችሏል። ለአምባሳደር ግሩም ዓባይ የጦር ወንጀለኛውን የአልፒኒ ሐውልትን ወስዶም አሳይቷል። በኢጣሊያ በርካታ ከተሞች የተተከሉ የፋሺስት ኢጣሊያ የጦር መሪዎች መታሰቢያ ሐውልቶችና በስማቸው የተሰየሙ መንገዶች ይገኛሉ። ከአልፒኒ ባልተናነሰ የጦር ወንጀል የፈፀሙ ቪያ-አምባ-አላጊ እና ቪያ ፓተር ጂሊያኒ የተባሉ የፋሺስት የጦር መሪዎች ስም በጣሊያን መንገዶች ይጠራሉ። አምባሳደሩ ከባህል ተቋሙ ጋር ሁለት ሰዓት የፈጀ ወይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ምንም ምንኳ የኢትዮጵያ ህዝብ ጣልያኖችን ይቅርታ ያደረገላቸው ቢሆንም በሰሜን ኢጣሊያ የጦር ወንጀለኛውን የአልፒኒ ሐውልትን በተመለከተ “ሐውልቱ በኢትዮጵያውያኖች ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በድጋሚ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። የባህል ተቋሙ፣ በኢጣሊያ በጦር ወንጀለኝነት የሚታወቁ የጦር አዛዦች ስም የቆሙ ሐውልቶችና በስማቸው የሚጠሩ መንገዶች ዝርዝር ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል። የባህል ተቋሙ አባል የሆኑት ፖል ባቸር እንደተናገሩት፣ ከጣልያን መንግሥት የሚጠበቀው ነገር ጣልያንን ካዋረዳት የፋሺስቶች ተግባር ምን ያህል ርቀት እንዳለው እና በመላው ጣሊያን የሚገኙ የፋሺስት ሠራዊት መታሰቢያዎችን ማስወገድ ነው ብለዋል።
ሞሶሎኒ በኢትዮጵያ ላይ ያወጀው ጦርነት የተጀመረው እ.ኤ.አ. ጥቅምት 3 ቀን 1935 ዓ.ም ነበር። በጊዜው የኢትዮጵያ ንጉሥ ጉዳዩን በሊግ ኦፍ ኔሽን አሰምተው ነበር። የፋሺስት ጦር ኢትዮጵያ ላይ የተጠቀመውን የመርዝ ጋዝ ከጀርመን ናዚ ጋር ለሚያካሂደው ጦርነት መሞከሪያ ለማድረግም ነበር። የፋሺስት ጦር ድርጊትን አስመልክቶ ብሪታኒያዊው ሐኪም ጆን ሜሊይ እንደገለፁት፣ “ይህ ጦርነት አይደለም፤ በጭካኔ ደም ማፍሰስ ብቻም አይደለም፣ ሊባል የሚችለው ነገር፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መከላከያ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ በመርዝ ጋር መጨረስ ነው” ብለዋል። የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ተወካይ የነበረው ማርሴል ጂኖድ በጊዜውን የዓይን እማኝነቱን የገለፀው “በየቦታው በመሬት ላይ የተጋደሙ ሬሳዎች ነበሩ፣ የሰው እግሮችና ሳምባዎች ሳይቀሩ በመሬት ላይ ይታያሉ። ያየሁት ነገር አሰቃቂ ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ብቻ አይደለም” ሲል ተናግሯል። ጦርነቱ በኋላ የፋሺስት አጣሊያ መንግሥት ለፈፀመው የዘር ፍጅት በዓለም አቀፉ የጦር ፍርድ ቤት ለመክሰስ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸናፊ በመሆኑ ሊቀር ችሏል። የጣሊያን መንግሥት ግን በካሳ መልክ ለኢትዮጵያ የ25 ሚለዮን ዶላር ቢሰጥም አሁንም ድረስ በይፋ ይቅርታ አልጠየቀም።
ኢትዮጲያ ዛሬ


በጣሊያን የሮማው ኦሎምፒክ ጊዜ
(ዘመን የማይሽረው ሕያው ታሪክ)


ሮም የኢትዮጵያ ደመኛ አገር የነበረችዋ የጣሊያን ዋና ከተማ ናት። በሮም፣ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ፣ በአዲስ አበባ የጣሊያን ባንዲራ በመተከሉና ኢትዮጵያ በጣሊያን እጅ በመውደቋ የድንፋታ ንግግር ለአገሬዉ ሕዝብ ያደረገበት ከተማ ናት። ከሃያ ስድስት አመታት በኋላ፣ እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ 1952 ዓ.ም ባንዲራችን መሬት ወድቆ ጮቤ በተረገጠባት ከተማ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ከፍ ብሎ ተዉለበለበ። በዚያን ቀን ታሪክ ተሰራ።


ጥንታዊት ሮማ ዳግም የታደሰች መስላለች። መንገዶቹ ሁሉ የፊት ማያ መስተዋት መስለዋል። እንዴት አደርሽ ጣሊያን? እንዴት አደርሽ ሮማ? የሚል የጣሊያን ሬዲዬ ድምፅ ይስተጋባል። ሁሉም የክቱን፤ እንዲሁም ደግሞ የማእረግ ልብሱን በየበኩሉ ለብሶ የኦሊምፒክ ውድድር የመዝጊያውን ቀን ሥነ-ሥርዓት ለማየትና ለመሰናበት ከየቦታው ወደ ሮማ ስታዲየም ይጐርፋል። ይተማልም።

ጊዜው እ.ኤ.አ. 1960 ነው። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ ላይ በብስክሌትና በሩጫ ውድድር የተካፈለች ሲሆን፤ የብስክሌት ተወዳዳሪው በውድድሩ ላይ ተጠልፎ ከወደቀበት ተነስቶ 7ኛ ሊወጣ ቻለ።

ገረመው ደንቦባ።
የመጨረሻውን እና ተናፋቂውን ማራቶን ለመጀመር «በስመ-አብ ወወልድ« ብሎ አማትቦ እስኪጨርስ ድረስ እንኳ ፋታ አላገኘም። የውድድሩን መጀመር የሚያበስረው የሽጉጥ ድምፅ አስደነገጠው። እንደ ሽጉጧ ጥይት ተተኩሰው ያፈተለኩትን ከተለያዩ ክፍለ- ዓለማት ከተውጣጡ 79 ወጣት ተወዳዳሪዎች ጋር ተከትሎ ተነሣ። በሕልሙ ይሁን በእውኑ በውል አልታወቀውም። ግን መሮጡን አላቆመም፤ ይሮጣል፤ ይቀድማል፤ ወደፊት ይገሰግሣል... ይሁን እንጂ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነበር ውድድሩ ላይ መሆኑን የተገነዘበው። ያውም ማራቶን! 42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር ርቀት! ከተወዳዳሪዎቹ መካካል ለየት ያለ ቀለም ያለው አንድ አትሌት ይታያል። ታዲያ ማንም ስለ አንድ አፍሪቃዊ ብቸኛ ጥቁር አትሌት ቦታ መስጠት ቀርቶ በንቀት መልክ ነበር የሚገላምጡትና የሚሣለቁበት። በውድድሩ መንፈስ ውስጥ ብቻ የነበረው ቆፍጣናው አፍሪቃዊ የIትዮጵያ ልጅ ከፊት መሪ ተወዳዳሪዎቹ ጋር ፍልሚያ ተያይዟል።

ውድድሩን በመቀባበል በየኪሎ ሜትሩ ፍጥነታቸውን በመጨመር አያንዳንዱ ተወዳዳሪ ለሐገሩ ክብር የጭንቀት ውድድር ውስጥ ይገኛል። ብርቅዬውና ውዱ የኢትዮጵያ ልጅዓበበ ቢቂላ ከእነዚህ ተወዳዳሪዎች አንዱ ነው። ውድድሩ ከተጀመረ 20 ደቂቃ Aልፎታል። አበበ በመሪነት ካሉት መካካል አንዱ ቢሆንም ከተወዳዳሪዎቹ ጋር አብሮ መጓዝ ግን ፈፅሞ አልተዋጠለትም። ተፎካካሪዎቹ ሣያስቡት የፊት መሪነቱን ቦታ ይዞ ፍጥነቱን በመጨመር ውድድሩን ቀጠለ። ማንም ሯጭ በአጠገቡ የለም። ለዓለም ሕዝብና ለመላው የጣሊያን ነዋሪ የሚተላለፈው የዜና ማሰራጫ ለአንድ አፍታ ፀጥ Aለ። ውድድሩን የሚያስተላልፈው ጣሊያናዊ ጋዜጠኛም አይኑ ፈጧል። ይንቆራጠጣልም። የደነገጠም የተገረመም ይመስላል። ድንገት ከሕልሙ አንደባነነ ሰው ድምፁን ከፍ በማድረግ መጮህ ጀመረ። «ምን ዓይነት ጉድ ነው! እኔ አላምንም! ይገርማችኋል! ማ ማ ሚ ያ! ይደንቃል!» ይል ጀመር። ንግግሩን በመቀጠል «አንድ ጥቁር አፍሪቃዊ በማይታመን ሁናቴ ውድድሩን ብቻውን፤ የመሪነት ቦታውን እስካሁን በሞኖፖል ተቆጣጥሮታል። ጥቁር እፍሪቃዊ ነው።» ደጋግሞም የጥቁርነቱን ምልክት ይናገራል፤ ይጮሃል፤ ይለፈልፋልም። Iትዮጵያዊ መሆኑን ግን በትክክል ያውቃል። አንዳይናገረው አንደበቱን የቆለፈው ታሪክ ግን አለ። Iትዮጵያ ጣሊያን ባዘጋጀው ኦሊምፒክ ማሸነፍ ማለት ጣሊያን ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ እንደተሸነፈች ነበር ለጋዜጠኛው የታየው። ሣልሣዊ ውርደት!! ጋዜጠኛው አሁንም የሬዲዬ መልእክቱን ማስተላለፉን አላቆመም። «...ማ ማ ሚ ያ! ፍጥነቱን ከልክ በላይ ጨምሯል፤ የድካም ምልክት አይታይበትም፤ ይጨርስ አይጨርስ ግን በትክክል አላውቅም፤ የሚገርማችሁ ነገር ቢኖር አግዜር አንደፈጠረው ባዶ አግሩን ነው፤ ኢትዮጵያዊ ነው። አቢሲኒያዊ ነው። ይጨርሣል ብዬ አልገምትም ...» ብሎ ያሟርታል። ውድድሩን በጥሞና በመከታተል ላይ የነበሩትና የአበበም አሰልጣኝ አንዲሁም የቡድኑ መሪ ሆነው የሄዱት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ውስጣቸው ተረብሿል። አንዴ ይቀመጣሉ፤ ሌላ ጊዜ ይነሣሉ... በተመስጥኦ ውጤቱን ይከታተላሉ። በዚህ መካከል አንድ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ በለሰለሰ አንደበትና ሥነ-ሥርዓት ጐንበስ በማለት «አቶ ይድነቃቸው ባልሣሣት እርስዎ ነዎት?« በማለት ሲጠይቃቸው «አዎ ምን ነበር?» በማለት መለሱለት። ጋዜጠኛውም ቀጠል አድርጐ «የእርስዎ ተወዳዳሪ ውድድሩን በከፍተኛ ርቀት በመምራት ላይ ነው። ውጤቱ ምን ይመስለዎታል?» በማለት ሲጠይቃቸው፤ «ለጥያቄህ አመሰግንሃለሁ። ውጤቱን በኋላ አብረን አናየዋለን።» ነበር ያሉት በትህትና። የውድድሩን ሂደት በጥሞና Eእየተከታተሉ የሚዘግቡት የተለያዩ አገር ጋዜጠኞችም ቢሆኑ ከጣሊያናዊው ጋዜጠኛ ብዙም ባይለዩም በንግግራቸው፤ በአገላለጣቸውና በአቀራረባቸው ሁሉም የአበበን ሥእላዊ ድርሰት በየተራ የሚያነቡ ይመስላሉ። የአቤን እጅ አወዛወዝ፤ የእግር አጣጣሉን፤ ቁመናውን፤ አፍሪቃዊነቱን ጥቁርነቱን በመደጋገም ለመግለፅ ይሞክሩ እንጂ የአበበን ውስጣዊ መንፈስና ሞራለ-ጠንካራነት ብሎም አይበገሬነት ግን ከርሱ በስተቀር ማንም የተረዳው ሰው አልነበረም። ውድድሩን በከፍተኛ ፍጥነትና በሙሉ ኃይል እንዲሁም በአስተማማኝ ርቀት የሚመራው አበበ፤ ሮማ ስታዲዮም ሲደርስ ተመልካቹ ሕዝብ ከመቀመጫው ብድግ በማለት ጭብጨባውን አቀለጠለት። ጀግናው ኢትዮጵያዊ አዲስ የኦሊምፒክ ክብረ ወሰን በባዶ እግሩ በመስበር አሸነፈ። ድልን ተቀዳጀ። ድሉ ለኢትዮጵያ ብቻም ሣይሆን ለአፍሪቃም ጭምር ሆነ። በነገራችን ላይ አበበ ውድድሩን እንደቀላል ነበር የጨረሰው። በውጤቱም ቀደም ሲል በሩሲያዊው ሰርጌይ ፖፖቭ በ2፡30፡00 የተያዘውን የሰዓት ሪኮርድ በ2፡16፡02 አሻሻለው። በዚህ በሮሙ ውድድር የተሰለፈው አበበ ዋቅጅራ ደግሞ እግሩ ፈንድቶ በሰርጌይ ፖፖቭ ለጥቂት ተቀድሞ 7ኛ ወጣ። ከርሱ በኋላ ተከታትለው በመግባት ላይ ያሉትም ተራ በተራ ፍንግል እንደያዛት ጫጩት ሜዳ ላይ ተዘርረዋል። በቃሬዛም በድጋፍም የተወሰዱ ነበሩ። አበበ ግን ለውድድሩ እንደሚዘጋጅ ተወዳዳሪ ጂምናስቲክ ይሠራል። አካሉንም ያዝናናል። አበበ ልዩ ተስጥዎ የነበረው ሞራለ-ጠንካራ አትሌት ነበር። ኢትዮጵያ ከሮማ ኦሊምፒክ በፊት በ1956 በሜልቦርን ኦሊምፒክ ተሣትፋ ነበር። ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት በ100 ሜትር አቶ ንጉሤ ሮባ፤ እንዲሁም በማራቶን ባሻ ተብለው የሚጠሩት ዛሬ በሕይወት ያሉና የፌዴሬሽኑ ዘበኛ ነበሩ። በውጤቱም ባሻ ውድድሩን ጨርሰዋል። አቶ ንጉሤም አፈሩን ያቅልልላችውና ውድድሩን ፈፅመዋል።

የዓለም የማራቶን ውድድር ስም ከተነሣ ከሮማ ኦሊምፒክ በፊት በተደረጉት ውድድሮች በርካታ ተወዳዳሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ብዙዎቹ አቋርጠዋል። በዚያን ዘመን ያሸነፉትም ቢሆኑ ከ3 ሰዓት በላይ ነበር የፈጀባቸው። አበበ ግን በማይታመን ሁናቴ ከላይ በተገለጠው መሠረት አዲስ ሬኮርድ ነው ያስመዘገበው።

አበበ ከሮማ ኦሎምፒክ ሜዳ የአበባ ጉንጉንና የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያውን በአንገቱ አስገብቶ ወደ እናት ሐገሩ በደስታ ተመለሰ። የሐገሩ ሕዝብም በጭብጨባ፤ በደስታ፤ በእልልታና በጭፈራ ተቀበለው። በተለይም ደግሞ የክፍሉ የሥራ ባልደረቦች የሆኑት የክብር ዘበኛ ጦር አባላት በልዩ ልዩ ዘፈንና ወኔ በተሞላበት፤ በከፍተኛ የሐገር ቅር ስሜት ነበር የተቀበሉት። የዘመሩለትም።
አቤም ለሐገሩ ላስገኘው ክብር፤ ለራሱም ላስመዘገበው ክብረ-ወሰን ለሽልማት ግርማዊነታቸው ፊት ቀረበ። «ደጉ ንጉሣችንም» የምክትል አሥር አለቃነት የበታች ሹማምንቶች ማእረግ አከናነቡት። አቤት ደግነት ይሉታል ይህ ነው!

አበበ ቢቂላ በማራቶን ብቻም ሣይሆን በ5ሺህ፤ በ10ሺህ፤ በ21 ኪሎ ሜትር፤ በ12 ኪሎ ሜትር በሄደበት ሐገር ሁሉ ማሸነፍ ብቻም ሣይሆን ክብረ-ወሰንም ጭምር ነበር የሰበረው። አንድ መረሣት የሌለበት ጉዳይ ቢኖር አበበ በሮም ኦሊምፒክ ውድድር ካሸነፈ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃለ-ምልልስ ላይ የተናገረው ነው። ይኸውም፤ «... እኔ የዛሬ ኦሊምፒክ አሸናፊ ከዓለምም አንደኛ ነኝ። በሐገሬ ላይ ግን ሁለተኛ ነኝ» ነበር ያለው። እንዴትና ለምን? ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ሲመልስም «እኔን የሚበልጠኝ ጓደኛ አለኝ። ይበልጠኛል። በውድድሩ ላይ ሣይሣተፍ የቀረውም በሰውነቱ ላይ ዘጠኝ ቦታ ቡግንጅ ወጥቶበት ነው። ስሙም ዋሚ ቢራቱ ይባላል። ስለዚህ ነው ብቻዬን የመጣሁት» ብሏል። የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ስለ ዋሚ ቢራቱ ያላሉት የለም። ሞራለ-ጠንካራውና «እድለ ቢሱ» ዋሚ ለኦሊምፒክ አይመረጥ እንጂ ከአበበና ከማሞ ወልዴ ጋር ብዙ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተካፍሎ አሸንፏል። ከማሞና ከአበበ ጋርም ተከታትሎ ገብቷል። ዛሬ ዋሚ ቢራቱ በሕይወት የሚገኙ አዛውንትና የ5 ልጆች አባት ናቸው። እኚህ እውቅ አትሌት የሐገሪቱ ባለውለታ፤ በውድድር ዘመናቸው ፉክክር ሁሉ ለሐገሩ ክብር ማስገኘት ብቻ ስለነበር ምንም ዓይነት ቋሚ ንበረትና ሃብት አልነበራቸውም። ምሥጋና ይግባቸውና ዛሬ አቶ አላ-ሙዲ የተባሉ ባለቱጃር መኖሪያ ቤት አሠርተውላቸዋል። የአበበ፤ የማሞና የዋሚ ታሪኮች የተያያዙ በመሆኑ በመሃከሉ ጀባ አልኳችሁ እንጂ የአበበ የውድድር ወይም የስፖርት ታሪኩን ለማየት ስንሞክር በርካታ ጥሎ ያለፋቸው አሻራዎች እንዳሉ እንገነዘባለን። ዓለም-አቀፍ ውድድሮች ላይ በአሸናፊዎች መድረክ ላይ ባንዲራችንን ማውለብለብ የቻለው አቤ ዳግም ሌላ ህልም ነበረው። የሚጨበጥ ራእይ! በ1964 ላይ በጃፓን ሊደረግ ስለታሰበው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ ለመሣተፍ ልምምዱን

ጠዋትና ማታ ያካሔድ ነበር። በርካታ አበበዎችም አፍርቷል። ተከትለውታልም። በሮማ ኦሊምፒክ የልፋቱን ዋጋ ከሐገሩ መንግሥት በትክክል ባያገኝም የላቀ ክብር አግኝቷል። ሞራሉ የበለጠ ተጠናከረ። ክብሩንም ላለማስነካት ለቶኪዮው የኦሊምፒክ ውድድር ዝግጅቱን አጠናቀቀ። የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ እያለ ስንክሣር አያጣምና አበበም ታሞ ሆስፒታል ገባ። ሁናቴው የኢትዮጵያን ሕዝብ ቢረብሸውም ፈጣሪ ምሥጋና ይግባውና! አቤ የቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጐለት ወጣ። ወዲያውኑ ልምምዱን ጀመረ። ዝግጅቱንም አጠናቀቀ።
ይሁን እንጂ አበበ ያሸንፍ ይሆን? የሚለው ጥያቄ በበርካታ የስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ አከራክሮ ነበር። ከሆስፒታል በወጣ በ36ኛ ቀኑ የኦሊምፒክ ውድድር እጩ የሆነው አትሌታችን ውድድሩን ለመካፈል ወደ ጃፓን ዋና ከተማ ወደ ቶኪዮ በረረ። በነገራችን ላይ ይህች ውብ ከተማ የተቆረቆረችው በወንዝ ላይ ነው። አበበ ቶኪዮ ዓየር ማረፊያ ሲደርስ በከዘራ ተደግፎ ነበር። በዚህም ምክንያት ምእራባውያን ጋዜጠኞችና ተችዎች ኢትዮጵያ እንደማታሸንፍ በሰፊው አናፈሱ።
ከዚያ ቀደም ሲል የአበበን ሁናቴ በቅርብ ሆነው ይከታተሉ የነበሩ የዓለም ጋዜጠኞች እሱ ወደታከመበት ሆስፒታል ድረስ በመሄድ አጨናንቀውት ነበር። ውድድሩ እስኪደርስ ድረስ አበበ በተደጋጋሚ ቃለ-ምልልሶችን አድርጓል። ለቀረበለት ጥያቄ ሁሉ «አትጨነቁ፤ አሸንፋለሁ።» በማለት ነበር በሙሉ ልብ የሚመልስላቸው የነበረ። ጀግናው በቶኪዮ ለመሮጥ ያሰበው በጫማ ነው። ቶኪዮ በልዩ ልዩ ኅብረ-ቀለማትና በኦሊምፒክ ዓርማ አሸብርቃለች። የዓለም ሕዝብ በጉጉት ይጠብቀው የነበረው የኦሊምፒክ መዝጊያ ውድድርም እልህ Aስጨራሽና ወኔንና ጉልበትን የሚጠይቅ ነበር። ውድድሩ እንደተጀመረ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተወዳዳሪዎች አንዱን ከአንዱ በማይለይበት ሁናቴ ማፈትለክ ጀመሩ። ቢሆንም ከመጀመሪያው አንስቶ የመሪነቱን ቦታ አበበ ብቻውን ተያይዞታል። እናም ቃሉን አላጠፈም። ዳግም የኦሊምፒክ ክብረ-ወሰን በመስበር ድልን ተቀዳጀ። በሮም ከተማ የሰበረውን ሰዓት በ2፡12፡15 አሻሻለው። ዓለም ዳግመኛ ጉድ አለ!።
የማይደገመው ተደገመ፤ ተደግሞ የማያውቀው የማራቶን ድል ተደገመ። ለአቤም እንዲህ ሲባል ተቀኘለት፤
ሮምን በባዶዕግሩ፤ ቶኪዮን በጫማ
ድል አድርጓል አቤ በሁለቱም ከተማ
ይህ ድንቅ አትሌታችን ክብሩን ጠብቆ፤ ታሪኩን ደግሞ፤ የሐገሩንም ሰንደቅ-ዓላማ ከፍ ብላ እንድትውለበለብ አደረገ። በዓለም ዙሪያ የመነጋገሪያ ርእስ ሆነ። እስከዛሬም ድረስ ቢሆን የዓለም ሕዝብ አበበን ጠንቅቆ ያውቀዋል።...

«ከ 1960 ጀምሮ የኦሊምፒክ ማራቶን የአውሮጳውያንና የአሜሪካውያን የግል ሃብት መሆኑ አበቃ። ከኢትዮጵያ ደጋዎች የተወለደ አንድ ሰው የሮማን የንጋት ውጋጋን ስሜት ፈጠረ። ይህ ያልታወቀ ሰው አበበ ቢቂላ ይባላል። ባዶ እግሩን ይሮጣል። ከአራት ዓመት በኋላ፤ ግን ጫማ አጥልቆ በድጋሚ ቶኪዮ ያሸንፋል»

ለአፍሪቃ፤ ለጥቁር ሕዝቦችና ለኢትዮጵያም የስፖርት በር ከፋችና ምሣሌ በመሆን ጀግናው አበበ በቶኪዮ ዳግም ድል አድርጐ ወደ ሐገሩ ተመለሰ። ከፍተኛ የክብር አቀባባልም ተደረገለት። ለእናት ሐገሩ ባለውለታነቱና ለራሱም ላጐናፀፈው ክብር፤ የልፋቱን ዋጋ ከሐገሩ መንግሥት ለማግኘት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፊት ለሁለተኛ ጊዜ ቀርቦ የምክትል የመቶ አለቃነት ማእረግ ሹመት ተቀበለ። የማራቶን ጀግናነቱንም አረጋገጠ። ቀጣዩ ኦሊምፒክ ለአበበም ሆነ ለኢትዮጵያ በጣም አስፈለጊ ብቻም ሣይሆን ታሪካዊነቱም የላቀ እንደሚሆን ግንዛቤ እየያዘ መጣ። ቀጣዩ የኦሊምፒክ ውድድር ሊደረግ የታሰበው ከአራት ዓመታት በኋላ ሜክሲኮ ላይ ነው። ለአበበም ሆነ ለተከታዮቹ የሚታያቸው ራእይ ከውድድሩ በስተጀርባ ያለው ቁም ነገር ብቻ ነው። በተከታታይ ለሦስት ጊዜ ማሸነፍ ከቻሉ የማራቶን ንጉሥ የሚለው ክብር ማግኘት ነበር ለጥንካሬያቸው ተጨማሪ ግፊት። በነገራችን ላይ ለሦስት ጊዜ የኦሎምፒክ ማራቶንን በመከታተል ያሸነፈ እስከዛሬ የለም። ጀርመናዊው ሯጭ እንዲሁ እንደ አበበ ሁለት ኦሊምፒኮችን ብቻ ነበር በተከታታይ ያሸነፈው። እንደ ሕይወቴ ሩጫን እወዳለሁ። ሕይወቴም ሩጫ ናት (running is my life) ነበር ያለው። አበበ ብዙዎች አበበዎችን አፍርቷል። ብቻውን አይደለም። ማሞ ወልዴም ከኮሪያ ዘመቻ በድል ተመልሷል። ዋሚ ቢራቱ፤ ባሻ ፍቅሩ፤ በየነ አያኖም፤ የትነበርክ በለጠ፤ ሽብሩ ረጋሣ... እነዚህ ሁሉ ከአበበ የማይተናነሱ የዘመኑ ፈጣኖች ነበሩ። ቢሆንም የኢትዮጵያ ችግር «ምንጊዜም» አይጠፋምና በበጀት ምክንያት ሁሉም አይሄዱም። የምርጦች ምርጥ ይመረጣል። በ1968 የሜክሲኮ ኦሊምፒክ የምርጦች ምርጥ አበበና ማሞ በመሆን ተመረጡ። ጊዜው ሲደርስም ጉዞው ወደ ሜክሲኮ ሆነ፤ ከበዙ ሰዓት የዓየር በረራ በኋላ ሜክሲኮ ሲቲ ሲገቡ የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ጋዜጦች ርእሰ አንቀጽ ገፆችን አበበና ማሞ ሸፈኑት። ሁለቱም ምርጥ አትሌቶቻችን በአካልም በመንፈሰም ተዘጋጅተዋል። አበበ የኦሊምፒክ የማራቶን ንጉሥ ለመባል፤ ማሞም በበኩሉ የመጀመሪያ ውጤቱን ለማየት!። በሜክሲኮ ጥቂት ቀናት ቆይታቸውም ከአካባቢው ዓየር ጋር ለመተዋወቅ የልምምድ ፕሮግራምም ነበራቸው፤ በቀረው ትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ ልዩ ልዩ ታሪካዊና መዝናኛ ቦታዎችን በመጐብኘት አሣለፉ። አይደርስ አይቀር የውድድሩ ቀን ደረሰ። ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር በመሆን የማስነሻውን ጥይት ተኩስ ይጠባበቃሉ፤ ውድድሩ ከተጀመረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጀግኖቹን አበበንና ማሞን የሚፎካከራቸው ጠፋ፤ የዕለቱ ዓየር ጠባይም ፀሃያማና ተስማሚ ስለነበር ተራ በተራ የመሪነቱን ቦታ ይቀባበላሉ። የውድድሩን ሂደት የሚከታተለውና የሚያስተላልፈው የሜክሲኮ ሬዲዬም ያለምንም ማጋነን የሁለቱን Iትዮጵያውያን በተለይም ደግሞ የAበበን ታሪክ አስመልክቶ ነበር ልዩ ትኩረት የሰጠው። ማሞንም በሚመለከት ከአራት ቀናት በፊት በ10ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የመሆኑን ታሪክ በሰፊው ያትታል፤ ውድድሩን በየተራ ለብቻቸው ይቀባበሉ ስለነበር ማን ያሸንፍ ይሆን? የሚል ጥያቄ መነሣቱ አልቀረም። ይሁንና ሁለቱም አትሌቶቻችን ከባዱን ጐዳና ተያይዘውታል። የውድድሩን የመጀመሪያ 25 ኪሎ ሜትር አገባደውታል።

በመሀሉ ማሞ ባልገመተውና ባላሰበው ሰዓት በጆሮው ተምዘግዝጐ የገባውን የአበበን ቃላት ማመን አቃተው። እንደመደንገጥ ብሎ «ምን አልከኝ?» በማለት ጠየቀው። አበበም የማሞን መደናገጥ ስለተገነዘበ እንደ ማባበል ዓይነት አለና «አይዞህ ታሸንፋለህ፤ እኔ አልቻልኩም፤ የእግሬ ወለምታ በጣም ተሰምቶኛል፤ ሌላም የማላውቀው ስሜት እየተሰማኝ ነው። ስለዚህ አደራዬን ተቀበለኝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠብቀናል፤ እኔ ስላልቻልኩ አንተ ቀጥል፤ የኢትዮጵያ አምላክ ይከተልህ» ካለው በኋላ አስፋልት ዳር ወደቀ። እውነትም በጣም ታሟል። ወዲያውኑ አበበ ሜክሲኮ ሆስፒታል በአስቸኳይ ተወሰደ። ማራቶን ልእልቷ አቤን ከዳችው። እርግጥ ነው በዚህ ውድድር የተጠበቀው አበበ ቢቂላ ነበር። የአበበ ውድድሩን ማቋረጥ ብዙዎቹን በማስደንገጡ በስቴዲየሙ የተገኙ ኢትዮጵያውያኖች የአበበ ማቋረጥ እንደተሰማ ስቴዲየሙን ለቀው ማሞ ወልዴን ለማበረታታት ወደ አደባባይ ወጡ። በዚያን ወቅት የነበረውን ሁናቴ ታዋቂው ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ እንዲህ ገልፆት ነበር፤ «የአበበን መውጣት ስሰማ ማሞን ለማበረታታት የጮህኩት ጩኸት ድምፄን ለሦስት ቀናት ያህል ዘግቶት ነበር።» ማሞ ብቻውን ቀሪውን ኪሎ ሜትር እየመተረ፤ በከፍተኛ ሞራል በመገስገስ ያለተቀናቃኝ የሜክሲኮን ኦሎምፒክ አሸንፎ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆነ። ማሞ በዚህ የሜክሲኮ ውድድር የ10 ሺህ ኪሎ ሜትር ማጣሪያና ፍፃሜ ውድድርን ጨምሮ 62 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር በመሮጥ የAንድ የወርቅና የአንድ ነሐስ ባለቤት በመሆን ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ሣይሆን አይቀርም። አበበ ከሆስፒታል ወጥቶ ማሞን ባየ ጊዜ እጅግ ከመደሰቱም በላይ ስቅስቅ ብሎ ካንጀቱ አለቀሰ። «የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠብቀናል» ብሎት ስለነበር ማሞ ..ረውም። በሦስት ተከታታይ የማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆኗ ዓለምን ቢያስደንቅም የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስታው ከመጠን በላይ ሆኗል። የቡድኑ አባላት ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ እለትም አበበንና ማሞን ለመቀበል ሕዝቡ በነቂስ ነቅሎ ወጥቷል። እልልታው፤ ዘፈኑ፤ ዝማሬው፤ ጭፈራው የአዲስ አበባ ጐዳናዎችን ከማስጨነቁም ባላይ አዲስ አበባ ከመመሰቃቀሏ የተነሣ የሠርግና የደስታ አውድማ መስላለች። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በየአግጣጫው ይውለበለባል። የክብር ዘበኛው ባንድ ጀግኖቹን ለመቀበል በልዩና በሚያስደስት ቅንብር ያሣየው ትርኢት ድንቅ ነበር። እንዲህ ነው ጀግንነት! እንዲህ ነው ወንድነት! አበበና ማሞ አንድና ሁለት! በማለት እንዲህ ሲባል ተገጠመላቸው፤

ማራቶን ማራቶን ማራቶን ውዲቷ
አበበና ማሞ ሆነዋል ባለቤቷ
ማራቶን ጠብቀሽ አቤን ብትቆጪ
ሆኖም አልቀረልሽ የትም አታመልጪ
አበበ ቢወጣ በእግር ወለምታ
ማሞ ተተክቷል የሐገሩ መከታ
ሮምን በባዶ እግሩ ቶኪዮን በጫማ
ድል አድርጓል አቤ በሁለቱም ከተማ
ተባለላቸው፤ ተዘመረላቸው። ተጨፈረላቸውም።

አበበ አንደ ዛሬ የዘመኑ ሥልጣኔ ባልተስፋፋበት ጊዜ በባዶ እግሩም፤ በጫማም የኦሊምፒክ ውድድርን ብቻ ሣይሆን በተለያዩ ውድድሮች አሸንፏል። ከዋሚና ከማሞ ጋርም ብዙ የዓለም-አቀፍ ውድድሮች ላይ ተካፍለው አሸንፈዋል። በዚያን ጊዜ አበበ የገባበት ሰዓት ዛሬም ቢሆን በቀላል Aይገባም። አበበ ቁመቱ ሎጋ፤ የቀይ ዳማና መልከ-መልካም Iትዮጵያዊ ነበር። በመልኩና በቁመናው እንዲሁም ባስመዘገበው ውጤት በመላው ዓለም ትልቅ ስምና ክብር አግኝቷል።
ከዚህ ውድድር በኋላ የጀግናው ሕይወት እንዴት ነበር የሚል ጥያቄ አንባቢያን ሊሰነዝሩ ይችላሉ። አበበ የጀግንነት ክብር ማግኘቱ፤ ዝናና ታዋቂነት ማትረፉ፤ በአጠቃላይም ስሙ በሐገር ውስጥም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጐልቶ ይታወቅ እንጂ በሕይወት ዘመኑ በርካታ ፈተናዎች ውስጥ ገብቷል። ዝነኛ ሰው ብዙ ችግሮች አጋጥመውታል። ቅናት እና ፍቅር ዋነኛዎቹ ናቸው። አበበም ከሁለቱ ለማምለጥ አልቻለም። ጀግና ይወደዳል፤ ይፈቀራል፤ ይከበራል። በ1972 ዓ.ም. በጀርመን ሙኒክ ከተማ የተካሄደው የማራቶን ውድድር ለኢትዮጵያውያኖች መጨረሻ ድል ነበር። አበበ ቢቂላ በሙኒክ ከተማ የተገኘው እነዚያ የሚወናጨፉ እግሮቹን ጣጥፎ፤ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ (1) ሲሆን፤ በስታዲየሙ የተገኙ ተመልካቾች ከመቀመጫቸው ተነስተው በጭብጨባ ነበር ተቀበሉት። በዚሁ በሙኒክ ውድድር በAርባ ዓመት እድሜው የተሣተፈው ማሞ 2፡14፡31 በመግባት 3ኛ ወጥቶ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቃ።

(2)

በነገራችን ላይ በሙኒኩ ውድድር Iትዮጵያ በማራቶን ነሐስ ሜዳሌያ ከማግኘቷ ሌላ በ10ሺህ ኪሎ ሜትር በአትሌት ምሩፅ ይፍጠር አማካይነት ሁለተኛውን ነሐስ አግኝታለች። ግናው አበበ ቢቂላ በተሽከርካሪ ወንበር ላይም ሆኖ በድጋሚ የዓለም የቀስት ሻምፒዮን ሆኗል። በእግሩ ያጣውን የወርቅ ሜዳሊያ በዓይኖቹና በእጆቹ ለማግኘት ችሏል። በ1966 ዓ.ም. አቤ ለዘላለም ይለየን እንጂ። ሻምበሉ ምን ጊዜም ሕያው ነው። ስሙ ከመቃብር በላይ ነው። አበበ ዛሬም ለሚሊዮን ኢትዮጵያውንና ሌሎች አትሌቶች አርዓያና «Inspiration» ምንጭ በመሆን በርካታ አበበዎችን ተክቶልን አልፏል። የዚህ እውቅና ድንቅ አትሌታችን የክብር መታሰቢያ ሐውልት በባእድ ሐገር በቶኪዮ በክብር ከመቆሙም በላይ ልዩ እንክብካቤም እንደሚደረግለት አንባቢያን እንዲገነዘቡልኝ እሻለሁ። በሐገራችን ያለው የአበበ ሐውልት ጉዳይ ግን እጅግ አሣዛኝ ነው። አቶ አቤ ሴሎም በክብር ያሠሩለት ሐውልት ዛሬ ምን እንደሚመስል ለአንባቢያን እተዋለሁ። በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከ1972 ዓ.ም. በኋላ ለማራቶን ድል ባትታደልም በተሣተፈችባቸው ኦሊምፒኮች ሁሉ የሩጫን ድል Aላጣችም። በ10ሺህና በ5ሺህ ኪሎ ሜትር ውድድሮች ብርቱ አትሌቶች ድል አጐናፅፈውታል። ምሩፅ ይፍጠር፤ መሐመድ ከድርና ቶሎሣ ቆቱ በ10ሺህ፤ መሐመድ ከድር፤ ዮሐንስ፤ ምሩፅ ይፍጠርና እሸቱ ቱራ የቡድን ሥራ በመሥራት በ5ሺህ ኪሎ ሜትር ተከታትለው በመግባት ሞስኮ ላይ ታሪክ ሠርተዋል።

ኢትዮጵያ በ1992 ዓ.ም. በስፔን ባርሴሎና በተካሄደው ውድድር በደራርቱ ቱሉ በ10ሺህ፤ በፊጣ ባይሣና በአዲሱ አበበ 1የወርቅና 2 የነሐስ አግኝታለች።1996 ዓ.ም. በአትላንታ ኦሊምፒክ ኃይሌ ገ/ስላሴ፤ ጌጤና ፋጡማ ሮባ በድል አንበሽብሸውናል። ንጉሱ በንግሥት ተተካ። በአትላንታ። አበበ የባረከውን፤ ማሞ የደገመውን የማራቶን ድል Aትሌት ፋጡማ ሮባ አፀናችው። ኢትዮጵያ በወንዶች ብቻ ሣይሆን በሴቶች ማራቶን እንደገና ንግሥት ሆና ብቅ አለች። በአበበ ቢቂላ ፈር ቀዳጅነት ጥቁር ሕዝቦችን ያኮራው የማራቶን ድል በማሞ ወልዴ አርማ አንሺነት የፀደቀው የማራቶን ድል፤ ዛሬ ከማንም በላይ ለኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት ሁሉ ተናፋቂ ነው። በሚቀጥለው ተረኛ ባለታሪክ እስከምንገናኝ ድረስ ቸር ይግጠመን።

የግርጌ ማስታወሻ
በዘመኑ በIትዮጵያ ራዲዬ እንደተነገረው አበበ ሸኖ በምትባል አካባቢ መኪና ተገልብጦ አደጋ ደረሰበት የሚል ዜና ተሠራጨ። በእውነት አበበ የሚኪና አደጋ ነው የደረሰበት? እንዴት ሁለቱን ፈጣን እግሮቹን ብቻ Aደጋ ደረሰባቸው? ዓይኑ አልተነካ፤ እጁ ላይ ቁስል አልደረሰበት። ምንድነው ምስጢሩ? እስካሁን ድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአበበ አሟሟት ትክክለኛ መንስዔ በትክክል ካለመታወቁም ባለይ እንቆቅልሽም ሆኖ ይገኛል። የአሟሟቱ መንስዔ የተሣፈረባት ቮልስቫገን ሣትሆን «ልዩ እጅ» የነበረው ስለመሆኑ በጊዜው ልንሰማ ችለናል።
ሶራ ጃዌ
.
ሮም የኢትዮጵያ ደመኛ አገር የነበረችዋ የጣሊያን ዋና ከተማ ናት። በሮም፣ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ፣ በአዲስ አበባ የጣሊያን ባንዲራ በመተከሉና ኢትዮጵያ በጣሊያን እጅ በመውደቋ የድንፋታ ንግግር ለአገሬዉ ሕዝብ ያደረገበት ከተማ ናት። ከሃያ ስድስት አመታት በኋላ፣ እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ 1952 ዓ.ም ባንዲራችን መሬት ወድቆ ጮቤ በተረገጠባት ከተማ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ከፍ ብሎ ተዉለበለበ። በዚያን ቀን ታሪክ ተሰራ።


domenica

በፖስታ ቤት የደረሰኝ ወረቀት የወጡ እስከ 30 10 07 ድረስ መመለስ ነበረባቸው


06 11 07
ውደ ድሮው ሕግ ተመለሰን።
ከእንግዲህ ወዲህ በደረሰኝ ወረቀት ብቻ ከጣሊያን መውጣት አይቻልም። የወጡም ተመልሰው መግባት አይችሉም።
የመመሪያው ማሻሻያ ነጥብ ጊዜያዊ ነበር።
.
በጣሊያን የመኖሪያ ፈቃድ እስከሚታደስላቸው በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙት የውጪ ሀገር ዜጎች የሀገር ውስጥ አስተዳደር ሚኒስትር አውጥቶ የነበረው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ደርሶ መመለስ የሚያስችለው ጊዜያዊ መመሪያ የቀን ገደብ እንደነበረው ይታወቃል። ይኸውም እስካለፈው ወር መጨርሻ ላይ ማለትም አስከ 30 10 2007 ድረስ ነበር። በወጣው መመሪያም ላይ ይህ የጊዜ ወሰን ተጠቅሶ እንደነበረ ይታወቃል። ይኸውም የሚያስረዳው “የሶጆርኖ መታደስን ለሚጠብቁ ለዚህም መጠባበቂያ የፖስታ ቤት ደረሰኝ ያላቸውና በጉዞ ላይ የነበሩ በሙሉ ይኼ ቀን ሳያልፍ መመለስ ይኖርባቸዋል” የሚል ነበር። ስለዚህ የሶጆርኖ ታዳሽ ተጠባባቂ ሆነው ከጣሊያን የወጡ ከሆነ የመመለሻቸው የጊዜ ገደብ ቀን ሳይወድቅ የተመለሱ መሆን ይኖርባቸውል ማለት ነው።
ማሳሰቢያ
ከእንግዲህ ወዲህ በደረሰኝ ወረቀት ብቻ ከጣሊያን መውጣት አይቻልም። "በደረሰኙ ፈቃድ የወጡና አስከሚመለሱ ድረስ የቀኑ ገደብ ያለፈባቸው ተመልሰው መግባት ይችላሉ ወይ?" ለሚለው ጥያቄ መልሱ "አይችሉም" ይሆናል።......
.
.
Rientri col cedolino Non si passa più per l'Ue
06 11 07
Finite le agevolazioni, si ritorna alle vecchie regole
ROMA - Niente più tappe europee per chi aspetta il rinnovo e vuole viaggiare tra l'Italia il suo Paese d'origine: il 30 ottobre è scaduto l'accordo temporaneo che permetteva a chi aveva con se passaporto, permesso scaduto e cedolino di fare scalo in tutti gli aeroporti e in alcuni porti dell'Ue. Sono così ritornate in vigore le vecchie limitazioni: uscita e reingresso in Italia dallo stesso valico di frontiera e viaggio che non preveda il transito in altri Paesi Schengen. Bisogna inoltre portare con sé il passaporto e la ricevuta dell'ufficio postale, che verranno timbrati dalla polizia sia all'uscita che al reingresso in Italia.
Regole simili sono in vigore anche per chi è arrivato con i flussi o con un ricongiungimento familiare ed è ancora in attesa del primo permesso di soggiorno per lavoro. In questo caso però, dal momento che non si ha un permesso, bisognerà esibire alla frontiera anche il visto rilasciato dal consolato che specifica il motivo del soggiorno in Italia.
(6 novembre 2007) Elvio Pasca