mercoledì

የነገው የውጪ ዜጎች ዕጣ


የዛሬ 10 ዓመት በፊት ክነበረው ጋር በማወድደር በመጨረሻዎቹ 5 ዓመታት ውስጥ በርካታ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ሲፈልሱ ታይቷል። ይኸው ጉዳይ የፖለቲከኞችና የህዝቡ መነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ሰነበቷል። በአንድ በኩል የውጪ ዜጎች የስራ ዕድል ተሻሚ ናቸው ሲባል በሌላ ወገን ደግሞ ወደፊት የአውሮፓ ሰራተኛ ህዝብ ቁጥር እየቀነሰ ስለሚሄድ የውጭ ዜጎች ይህን ክፍተት ይሞላሉና ፍልሰቱ መቀጠል አለበት የሚል ክርክርም ይነሳል። በዚህም ምክንያት አሁን በአውሮፓ ያለው ሁኔታ ለስደተኞች ምንም የሚያበረታታ አይደለም።
ብዙዎች በየብስ ሆነ ባባህር ድንበር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት በሚያደርጉት ሙከራ መንገድ ላይ ህይወትን እስከማሳለፍ ደረጃ የሚደርሱበት ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። በተለይም በቀይ ባህር አድርገው ወደ ልዩ ልዩ የአውሮፓ አገራት ለመግባት በየስደተኞች ሰፈር የሚጠባበቁ ከቀድሞው የባሰ ፈተና ነው የሚጠብቃቸው። ምክንያቱም ወደ አውሮፓ የመሻገሪያው ድንበር እጅግ ከፍ ብሎ እየታጠረ በመሆኑና እዚህም በሚገኙት ላይ ከዚህ ቀደም ልል የነበረው ህግ እየጠበቀ በመምጣቱ ነው።
በተለያዩ ሀገሮች ያሉ ፖለቲከኞች በስደተኛ ላይ የያዙት አቅዋም የተለያየ በመሆኑ ከብዙ አቅጣጫ ትችት እየተሰነዘረበት ነው። በእያንዳንዱ የአውሮፓ ሀገር ውጭ ዜጎች ፍልሰት ህግ ሁሉም እኩልና አንድ ወጥ የሆነ ህግ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። በተለይ ሽብርተኞች በዩናይትድስቴትስ ላይ ካደረሱት እ.ኤ.አ የመስከረም 11 2001 ጥቃት ጋር አያይዘው የአውሮፓ ሀገሮች በውጭ ዜጎች ላይ ቁጥጥሩን በማጥበቃቸው ብዙዎቹ የተለያዩ ህጎችና ድንጋጌዎችን ስላወጡ ብዙ ተተችቶበታል።
ለምሳሌ አብዛኛዎቹ መሪዎችና ፖለቲከኞች ስደተኞችን እየመረጡ የማስገባቱን መርህ ደጋፊዎች ናቸው። ከነዚህም አንዱ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኒኮላሳ ሳርኮዚ ናቸው። ኒኮላስ በአንድ ወቅት “ዕርዳታ ፈላጊ ስደተኛ አንፈልግም እኛ የምንፈልገው ለኛ የሚስማሙንን ነው። ይህም ማለት በአስተማማኝ ሁኔታ ለፈረንሳይ ዕድገት አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉትን ነው በተለይ የምንመርጠው“ ብለው ነበር። ይህ አባባል በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ተቀባይነት የለውም።
በአውሮፓ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ብዙሀኑ በዕድሜ እየገፉ ስለሚሄድ የውጭ ዜጋ ወደ አውሮፓ እንዳይገባ ገደብ ይጣል መባሉ የትም እንደማያደርስ ነው የተገመተው። አሁን ባለው ግምት መሰረት እ.አ.አ. እስከ ሁለት ሺህ አስራ አምስት ከአውሮፓ ህዝብ አንድ ሶስተኛው ዕድሜው ከሀምሳ ዓመት በላይ እንደሚሆን ነው የተገለፀው። እናም ያኔ ስደተኞች ስራ ይሻሙናል የሚል ስጋት ቀርቶ ሳይወዱ በግድ ስደተኞችን መሻታቸው አይቀርም። ይሁንና ተጨባጩ ሁኔታ ብናጤነው የህብረተሰቡ ስጋት ምኑ ላይ እንደሆነ ለመለየት ይቸግራል።
ብዙዎቹ ስደተኞች ህጋዊ ባለመሆናቸው የስራ ዕድል የላቸውም። የስራ ሽሚያውም አይመለከታቸውም። ስራ ለማግኘት ብዙ ነገሮችን ማሟላት ያስፈልጋል። ብዙ እስያውያን ሴቶች ህፃናትን የሚንከባከቡ፣ የህፃናት ሞግዚት ሆነው የሚሰሩ፣ በቤት ውስጥ ስራ የተሰማሩ፣ በየመዝናኛ ስፍራዎች ሲያገለግሉ ነው የምናያቸው።
ያለንበት ዘመን ዓለም ዓቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር ዘመን ስለሆነና ጊዜው የነፃ ገበያ ወቅት በመሆኑ ህዝቦች ከአንዱ አገር ወደ ሌላው ለስራ መሰደዳቸው ጤነኛ አካሄድ ነው። አውሮፓውያን መሪዎችና ፖለቲከኞች ስደተኛውን እንደ አደጋ ሳይሆን ጠቃሚ የልማት አስተዋፅኦ ሊያበረክት የሚችል ሀይል አድርገው መመልከትና እንዲህም የውጭ ዜጎች ወደ አውሮፓ የሚገቡበትን ስርአት በደንብ ማስተካከል ይገባቸዋል።

Nessun commento: