giovedì

ሚሌኒዩምን እንዴትና ለምን ማክበር ያስፈልጋል?


የግል አስተያየት
እንዴትና ለምን ማክበር?
ኢትዮጲያ የራሷ የሆነ ቀን መቁጠሪያ አላት። በዓለም ውስጥ ልዩ ያደርጋታል። ዘመን መቁጠሪያችንን ዘመናትና ነገሥታት ሳይሽሩት ቀደምት አባቶቻችን ያስተላለፉልን ቅርስና የኢትዮጵያዊነት አንዱ መግለጫችን ነው:: ታዲያ ዓመት አልፎ አመት ሲመጣ "እንኳን አደረሳችሁ"..."መጭው ዓመት የስላም የጤና የስራ ዓመት ይሁን"... ብለን ተባብለን አመቱን በደስታ እንቀበላለን እናሳልፋለን።
.
መቼም እንደሚታወቀው የሚቀጥለው እንቁጣጣሽ ካለፉት ሁሉ የተለየ ነው:: ይኸውም ከተለመደው ከአመት ወደ አመት መሸጋገር ወይም ከዘመን ዘመን መሸጋገሪያ ሌላ ለየት የሚያደርገው የምዕተአመቱ መለወጫ (ሚሊኒየም ወይም የ1000 ዓመት ለውጥ) በመሆኑ ነው። ከሺህ ዓመት በኋላ አንድ ጊዜ ብቻ የሚመጣ በመሆኑና ከአለፉት ብዙ ትውልድ መሐከል በእኛ ትውልድ ላይ መጋጣጠሙ ነው። በዚህም ምክንያት ለእያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ሎተሪ እንደደረሰው ያህል ነው የሚቆጠረው። ለዚህ ሚሌኒይም የደረሰው የእኛው ትውልድ ብቻ ስለሆነና ለዚህም በሕይወት በመገኘታችን እንኳን ደስ አለን።
.
ይህንን ልዩ የሆነውን የምዕተ አመት ለውጥ በሌላ ጊዜ ለማክበር ሌላ አንድ ሺ አመት ስለሚያስጠብቀን ይሄ እድል ሳያመልጠን ተጠቅመንበት ቁምነገሮች ልንሰራበት የሚገባ ይመስለኛል:: ስለዚህም በፀዳ ሁኔታ በባህል፣ በታሪክ፣ በኃይማኖትም ሆነ የተለያዩ ዘርፎችን ያካተተ እንዲሆን አድርጎ፣ አስተባባሪ አቋቁሞ ተሰባስበን በመተጋገዝ በዓሉን ለማክበር ከአሁኑ በጋራ ብንዘጋጅ ጥሩ ነው::
.
በእርግጥም በጣሊያን የሚገኙትን ኢትዮጲዊያን የሚያሰባስብ አህጉራዊ የሆነ ዝግጅት ለማድረግ በጀት (ገንዘብን) የሚጠይቅ ብቻ አይደለም። ጊዜን፣ መተባበርና ታጥቆ መሥራትን፣ እውቀትንና ጉልበትን፣ ቁሳቁሶችን ወዘተ... የሚጠይቅ ነው። አስተዋጽዖ የሚያደርጉ በጎ ፈቃደኞች ያስፈልጋሉ። ከዚህም በላይ ጠንካራ የኢትዮጲያ ኮሚኒቲዎች ካሉ በያሉበት ህብረተሰቡን በማስተባበርና ለዝግጅቱ ተሳትፎ እንዲኖር በማድረግ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ድርሻና ግዴታ እንዲወጡት መሆን አለበት።
የዚህ አይነት ዝግጅትን ለማስተባበርና ለማቀነባበር ልምድ ያላቸው ኮሚኒቲ ካላደረጉት በስተቀር ለሌሎች አስተባባሪዎች ወይም አዘጋጆች ከወራት
በፊት ይሚጀምሩትና ቀደም ተብሎ የሚታሰብበት ጉዳይ ይመስለናል። ማለትም «የኢትዮጲያ ሚለኒየም ፌስቲቫል በጣሊያን» ተብሎ የተሰየመ ደማቅ በዓል ለማዘጋጀት ከተፈለገ ሁሉንም በሚያሰባስብ አዳራሾች፣ ድንኳን፣ የእንግዶች መስተንግዶ፣ ..... ...... ..... ......
በአጠቃላይ በጊዜ እጥረት ምክንያት አህጉራዊ ፌስቲቫል ለማዘጋጀት ፕሮጄክቶችን በማቀድና በማጽደቅ ቀደም ተብሎ መሠራት የሚገባቸው ነገሮች ነበሩና። ...... (ይቀጥላል...)
.
ቢሆንም መለስተኛ የሆነ ዝግጅቶችን ለማቀነባበር ሕጋዊነት ያላቸው የኮሙኒቲ ማህበራት ከአሁኑ ጀምረው በማስተባበር ሊያደርጉት ይችላሉ። አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሥሩ ደግሞ የተለያዩ የሥራ ክፍፍል ያለው ንዑስ ግሩፕ በማቋቋምና መለስተኛ በዓል ለማድረግ። የደመቀ እንዲሆን ለማድረግ ደግሞ የኢትዮጲያን ገፅታ በማስረጃዎች ለማሳየትና በማቅረብ ከዚህም ጋር ሀገራችንን በይበልጥ ማስተዋወቅ የሚረዳን ስለሆነና ልዚሁም ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ ሁሉም ለበዓሉ መከበር የዜግነቱን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ይደረግ ....
.
ለምን

- ለዚሁ ለሚያስተናግደን ሀገር ህዝብ የተለያዩ የአገራችንን ቅርሶች፣ ታሪክና ባህል ለማስተዋወቅ የምንችልበት አጋጣሚ ጊዜ ስለሚሆን...
- ኢትዮጲያ ከተቀረው ዓለም ሚሌንየሟን ከሰባት ዓመት በኋላ የምታከብርበት ምክንያት ከጁልየስ ቄሳር ተመሳሳይነት ባለው የቀን መቁጠሪያ የምትጠቀም መሆኑን ለማሳወቅና ያለንበት ዓመተምህረት በ7 ዓመት ወደኋላ እንደምንገኝ፣ 13 ወር እንዳለን፣ ከ80 በላይ ቋንቋዎችና ብዙ ብሔሮችን አቅፋ ... ፣ ከ200 በላይ ፊደልና ልዩ ቁጥሮች (አኃዝ) ...ወዘተ... እንዳለን፣
- በኢንቬስትሜንት እንድትለማ ማስረጃዎችን በማቅረብ አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን።
- የሀገራችንን የቱሪዝም መስህብነት ለማሳደግ... (የሰው ልጅ መገኛና የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያላት መሆኗን ለማስገንዘብ... የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ገና ያልተነካ መሆኑን የሚያሳዩት በሀገሪቱ ያሉትን የአክሱም ሃውልት፣ የአጼ ፋሲለደስ ቤተ መንግስት፣ የላሊበላ አብያተክርስቲያን፣ በጣና ሃይቅ ውስጥ የሚገኙትን ድንቅ አብያተክርስቲያን፣ የባሌው ሼክ ሁሴን ፣ የነጋሽ መስጊድ፣ የሐረር ጀጎል፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የጅማው አባ ጅፋር እንዲሁም በአገሪቱ ብቻ የሚገኙ ድንቅ እንስሳትና የተለያዩ አዕዋፋት ...ወዘተ... እንደሚገኙባት ለማሳወቅ...)
- የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት መሆንዋን ለማስገንዘብ...
- እኛም እራሳችን ብንሆን ስለሀገራችን የማናውቀውን የምንማርበት አጋጣሚ ስለሚሆንልን...
- በተለያዩ የጣሊያን ክፍል የምንገኝ ኢትዮጲያዊያን/ት እርስ በእርሳችን ትውውቅ የምናደርግበትና የሚያስተሳስር አንድ ማህበረሰብ ለመመሥረት ወርቃማ አጋጣሚ ይሆንልናል።

እንዴት

- አነስተኛ ባዛሮችንና ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት...
- የኢትዮጲያ ብሔረስብ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ የስራ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ፎቶግራፎች፣ ....
- የፌስቲቫል የሙዚቃ ኮንሰርት በማድረግ...
- የተለያዩ የስፖርት ዝግጅቶች እንዲከናወኑ በማድረግ (ምሳሌ - ሀገራዊ ሻምፒዮን የእግር ኳስ ቡድኖችን የሚያሳትፍ ዝግጅቶችን በማቀነባበር። ለዚህ ደግሞ ጊዜው ማጠሩ ብቻ ብቻ ሳይሆን ቀደም ያሉ ዝግጅቶችም ያስፈልጉ ይመስለኛል)
- በጣሊያን ድርጅቶችና በመንግሥት ቅርንጫፎች ድጋፍና እርዳታ እንዲገኝ በማድረግ...
- ደግሞ ከተለያዩ የጣሊያን ክፍሎች ለሚመጡት የግሩፕ መጓጓዣ እንዲኖር ሁኔታዎችን ማመቻቸትና መስተንግዶ እንዲኖራቸው ማድረግ፣...
- ኢትዮጲያውያን ብቻ ሳይሆኑ ኅብረተሰቡም በሚሌኒየሙ እንዲገኝልን ቅስቀሳ ማድረግ አለብን። በመገናኛዎች ማስታወቂያና ጥሪዎችን በማሰራጨት ፈረንጆቹም ለሚሌኒየሙ እንዲገኙ ለመጋበዝ ኢትዮጲያውያን/ት በሙሉ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ብዙ ይጠበቅባቸዋል።
- በዚህ ረገድ ኮሚኒቲዎች እንዲሰባሰቡና የጋራ ልምዳቸውን መሰረት አድርገው እንዲያስተባብሩ፣
- አህጉራዊ በዓል የሚዘጋጅ ከሆነ ከተለያዩ የጣሊያን ከተማዎች ለሚመጡት የግሩፕ መጓጓዣ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ጥሩ መስተንግዶ እንዲያገኙ፣
- ወጣት ኢትዮጲያውያን/ት በሙሉ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ብዙ ይጠበቅባቸዋል።
.
በዓሉ የዘመናት ታሪካችን የሚዘከርበትን ሁኔታ እንዲኖረው ያስፈልጋል:: ኢትዮጵያችን በዓለም ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ የሚሰጣት የቅኝ ገዥዋን አንበርክካ በራሷ ነፃነቷን ጠብቃ ለዘመናት የኖረች ብቸኛ አፍሪቃዊት አገር መሆኗ ነው:: ስለዚህም ይህ የሚሊኒየም አውደዓመታችን ያለፈውን ታሪካችንን በማስታወስ በተለይም ጣሊያን የቅኝ አገዛዝዋን ሙከራ በመስበር ያሽነፍንበት ዘመን መሆኑን ለማሳደስ። ሌሎቹንም ታሪካችንን የምናድስበት፣ አንድነታችን የምናጠናክርበት፣ ያለፈውን አዝጋሚ ጉዞ መለስ ብለን የምንዳስስበትና መጪውን ጎዳና የምንመለከትበት አጋጣሚ ሊሆን ይገባል።
.
የዛሬ ሰባት ዓመት ፈረንጆች ሚሌኒየማቸውን ሲያከብሩ ሁሉም አንድ ላይ ነበሩ። እኛም ልክ እንደነሱ ወደ ሦስተኛው ሚሊኒየም ስለምንሸጋገር እጅ ለእጅ ተያይዘን ማክበር እንችላለን። ይህ አውዳመት ሀገራችን የሁለትና ሦስት ሺ ዘመን ጉዞ እንዳደረገች ለምናምነው ዜጎቿ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል:: በዚሁ በጣሊያን ሀገር ሕግና የዲፕሎማሲ መርህ መሠረት ... (ይቀጥላል...)
አብራሃም ዘውዴ Gugno 2007


Nessun commento: