giovedì

የጣሊያን የምንስትሮች ምክር ቤት አዲስ የኢምግሬሽን የሕግ ረቂቅ አወጣ


(ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ)
.....በጣሊያን አገር የሰሞኑን የኢምግሬሽን የሕግ ለዉጥ በተመለከተ የተለያዩ ህሳቦች በተለይም ከእዉነት የራቁ ወሬዎች ከየአቅጣጫዉ ይሰነዘራሉ:: በመጀመሪያ ደረጃ ይህ የሕግ ረቂቂ እንጂ ተግባራዊ የሆነ ሕግ አለመሆኑን ላሳስብ እወዳለሁ:: በአንድ አገር አንድን ሕግ ተግባራዊ ሕግ ነዉ ሊያሰኘዉ የሚችለዉ የአገሪቱ ፓርላማ አፅድቆት በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣ በኋላ ነዉ:: ከዚህ ሁሉ የዉጣዉረድ ጉዞዉ በኋላ ሕጉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሕግ ነዉ ብሎ ማለት ይቻላል:: ይህ ሕግ ገና ብዙ መሰናክሎችን ያላለፈ እንደመሆኑ መጠን ተጠቃሚዉን ክፍል ችግር ላይ ጥሎት ሰሞኑን አንዳንድ ግለሰቦች... "አዲስ ሕግ ወጥቷል ብለዉ የሆኑ ጣሊያኖች ሲያወሩ ሰማሁ እዉነት ነዉ?" "የዜግነት ጥያቄስ አሁኑኑ ማቅረብ እችላለሁ?" ... እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ:: በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከተዉና በጣሊያን አገር ነዋሪ የሆነዉ የዉጭ አገር ዜጋ በተለይም የአማርኛን ቋንቋ አንብቦ መረዳት የሚችል ሁሉ ትክክለኛዉን መልእክት ማግኘት ይችላል ብዬ በማመን የሕጉን ለዉጥና መንፈስ አጠር ባለ መልኩ ከዚህ በታች ላስቀምጥ እሞክራለሁ::

FLUSSI DI INGRESSO
ካሁን በፊት በየአመቱ የዉጭ አገር ዜጎች ወደ ጣሊያን አገር በመምጣት መስራት እንዲችሉ የተወሰነ ቁጥር ገደብ ተደርጎ ፕሮግራም ይወጣል በአዲሱ ህግ ግን ይህ ቁጥር በሶስት አመት አንድ ጊዜ ይወሰናል ቁጥሩም እንዳስፈላጊነቱ ሊጨምር ይችላል::
.
LAVORATORI ALTAMENTE QUALIFICATI
ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸዉ የዉጭ አገር ዜጎች ጣሊያን አገር መጥተዉ ለመስራት ጥያቄ ካቀረቡ የመምጣት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ይላል ካሁን ቀደም የነበረዉ ህግ ግን የጉልበት ስራን ብቻ ይመለከት ነበር::

LISTE DI COLLOCAMENTO
ማንኛዉም የዉጭ አገር ዜጋ ጣሊያን አገር ገብቶ ስራ ለመስራት ባለበት አገር የጣሊያን አምባሲ በሚገኘዉ የስራ ፈላጊዎች ዝርዝር ሰነድ ላይ መመዝገብ ይኖርበታል::

AUTOSPONSORIZZAZIONE
አንድ የዉጭ አገር ዜጋ በራሱ ሃላፊነት የራሱን ወጪ ችሎ ዋስትናዉን እራሱ ከሸፈነ ጣሊያን አገር ገብቶ ስራ የመስራት መብት አለዉ:: ለምሳሌ በዚህ አንቀጽ መሰረት አንድ ግለሰብ በቂ ገንዘብ አለኝ ለጣሊያን ቪዛ ይሰጠኝ ብሎ ቢጠይቅ ቪዛዉን የማግኘት እድል አለዉ ማለት ነዉ::

VISTI D’INGRESSO
አንድ የዉጭ አገር ዜጋ ጣሊያን አገር ለመምጣት ቪዛ በሚጠይቅበት ወቅት ያለአንዳች ቢሮክራሲና ዉጣዉረድ ለጥያቄዉ መልስ ባስቸኳይ ሊሰጠዉ ይገባል:: ጣሊያንም ከመጣ በኋላ ካሁን በፊት እንደነበረዉ የመኖሪያ ኮንትራት (contratto di soggiorno) የመፈረም ግዴታ አይኖርበትም::

DURATA DEI PERMESSI
የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት የጊዜ ገደብ ካሁን በፊት ከነበረዉ የረዘመ ይሆናል:: ለምሳሌ የስራ ኮንትራቱ የጊዜ ገደብ አነስተኛ ከሆነ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀቱ ለስድስት ወር ይሰጠዋል:: የስራ ኮንትራቱ የጊዜ ገደብ ከስድስት ወር በላይ ከሆነ ግን የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀቱ የሁለት አመት ይሆናል:: የስራ ኮንትራቱ የጊዜ ገደብ የሌለዉ ከሆነ የሶስት አመት የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ይሰጠዋል:: የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀቱ በሚታደስበት ወቅት የጊዜ ገደቡ እጥፍ ይሆንና የስድስት ወር የነበረዉ ለአንድ አመት፣ የሁለት አመቱ ለአራት አመት ይታደስለታል ማለት ነዉ::
.
PERMESSI PER MOTIVI UMANITARI
የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት በስራ ብቻ ሳይሆን በሰባዊ መብት ምክንያትም ለአንድ አመት ሊሰጥ ይችላል:: የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀቱንም ለማሳደስ ግለሰቡን ሊያኖር የሚችል የገቢ ሁኔታ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል::
.
PASSAGGIO DELLE COMPETENZE AI COMUNI
ይህ ሕግ በተግባር ሲተረጎም የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት የማሳደሱ ተግባር ሃላፊነቱ የፖሊስ ጽ/ቤት ሳይሆን የማዘጋጃ ቤት ይሆናል:: ይህም በየፖሊስ ጽ/ቤቶች በራፍ ሲደረግ የነበረዉን የሰዉ ልጅ የማያልቅ ሰልፍ ሊያስወግድ ይችላል::

INSERIMENTO DEI MINORI STRANIERI
በጣሊያን አገር ነዋሪዉ የዉጭ አገር ዜጋ ህጻናትም ጭምር ከህብረተሰቡ ተዋህዶ አምራች ዜጋ መሆን እንዲችል የስራ፣ የትምህርት፣ የህክምና፣ የመኖሪያ ቤት፣ የጡረታ እኩልነት መብቱ ሁሉ ይከበርለታል::

ELETTORATO ATTIVO E PASSIVO ALLE AMMINISTRATIVE
በወንጀል ያልተነካካ በጣሊያን አገር በህጋዊነት ለአምስት አመት ያህል ነዋሪ የሆነ ማንኛዉም የዉጭ አገር ዜጋ በሚኖርበት ክፍለ ሀገር በሚደረገዉ የአስተዳደር ምርጫ በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት የመካፈል መብት ይኖረዋል::

PROGRAMMI DI RIMPATRIO E ASSISTITO
በተለያዩ ምክንያቶች በጣሊያን አገር መኖር የማይችሉት የዉጭ አገር ዜጎች ፕሮግራም ይዘጋጅና በወጣዉ ፕሮግራም መሰረት እርዳታ ተደርጎላቸዉ ወደየመጡበት አገራቸዉ እንዲመለሱ ይደረጋል:: አገራቸዉም ከገቡ በኋላ እንደገና ተመልሰዉ ጣሊያን አገር በስራ የመምጣት እድል ቅድሚያ ይሰጣቸዋል::

MODALITA’ DI ALLONTANAMENTO
አንድ በጣሊያን አገር የሚኖር የዉጭ አገር ዜጋ ወንጀል ከተገኘበት እንደየወንጀሉ ክብደት፣ ቀላልነትና አደገኛነት ፍርድ ቤት ቀርቦ ይታሰራል ወይንም አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ይደረጋል::

CENTRI DI PERMANENZA TEMPORANEA
ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ጣሊያን አገር የገቡ የዉጭ አገር ዜጎች ተይዘዉ ማንነታቸዉ ተረጋግጦ ወደያገራቸዉ እስከሚመለሱ ድረስ እስከ ስልሳ ቀናት ያህል ይቆያሉ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ይደረጋል:: የማረፊያ ቤቶቹም ቁጥር ካሁን ቀደም ከነበረዉ አነስተኛ ይሆናል::
ለማጠቃለል ያህል ይህ የሕግ ረቂቅ ከሞላ ጎደል ሲታይ የሰዉን ልጅ መብት የሚያስከብር ሌሎች በዴሞክራሲ የበለጸጉ አገሮች ካላቸዉ የኢሚግሬሽን ሕግ ጋር የሚቀራረብ ይመስለኛል ሆኖም አንዳንድ የጣሊያን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጉ እንዳይጸድቅና ግቡን እንዳይመታ ከመፈለጋቸዉ የተነሳ ጣሊያን በዉጭ አገር ዜጋ ልትወረር ነዉ፣ አገሪቱ የወንጀለኛ ማጠራቀሚያ ልትሆን ነዉ፣ እና ወዘተ በማለት በህብረተሰቡ ላይ ሽብር በመንዛት ፍርሃት በመፍጠር ላይ ይገኛሉ:: ጉዳዩ "አለባብሰዉ ቢያርሱ ባረም ይመለሱ" እንደሚለዉ የአባቶች ተረት እንዳይሆን የጣሊያን መንግስት ጥንቃቄ ሊያደርግበት ይገባል ብዬ እላለሁ::
Bologna, 30/04/2007


Nessun commento: