sabato

ሮማ እና አክሱም


ኢጣሊያዊዉ የታሪክ ተመራማሪ ስቴፋኖ ማሲይ "የአለም ታሪክ የሮማ ታሪክ ነዉ" ይላሉ። እዉነቱን አኳሹት እንጂ አልዋሹም። የሮማን ታሪክ የአለም ታሪክ ግማድ ካደረገዉ የዘንድሮው የሚያዚያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የሮማ ሁነት ይገኝበታል። ሮሞች የእስካሁን ታሪካቸውን እንደ አለም ታሪክ ውርስ እንደጠበቁት ሁሉ የዘንድሮውን ሚያዚያ የሮማ-አክሱም ሁነት ታሪካቸዉን የሚያደምቀው ግማድ መሆኑ አያከራክርም።
አቢሲኒያ ጥንታዊ ነች። መፅሐፍ ቅዱስ ቅድስትነቷን መስክሮላታል። ታሪክ አዋቂዎች አሞግሰዋታል። ሆሜር ለሕዝቧ ቅን ደግነት ቅኔ ዘርፎለታል። ነቢዩ መሐመድ ፍትሐዊነትዋን መስክረዉ ፀልየውላታል። ከጥንታዊቷ አቢሲኒያ ብዙ በጎዎች መሐል-ነፃነትን የማስከበር ተጋድሎዋ፣ ዉርስ-ቃሏን ማስከበሯ፣ በግሪኮች ጥንታዊ ዉዳሴና አድናቆት ማትረፏና እስካሁንም በመቀጠል በነማንዴላ ተደገመ። ሁለቱን ትላልቅ ሐይማኖች የማማከልዋ ፍትሐዊነት፣ ክርስትናን፣ እስልምናን፣ አይሁድን፣ ከየሐይማኖቶቹና ከእምነት የለሹ ጋር አሰባጥራ በማኖርዋ፣ ከቫቲካን እስከ አቴና፣ ከሜካ እስከ እየሩሳሌም የአቢሲንያን የስልጣኔ ርቀት፣ የመንግስቷን ገናናነትና ግዝፈትን በማያሻማ ቃላት የመሰከረ ቀዳሚም ተከታይም የሆነ ሀገር የለም።
በአምስት አመተ-አለም ታላቁ ሳይሩስ የመሰረቱት የፋርስ ገናና መንግስትን በሁለተ መቶኛ አመቱ ታላቁ አሌክሳንደር ሲያንኮታኩቱት፣ ሳይሩስን ተከትለዉ ከአዉሮጳ ከተማቸዉ ወጣ ወጣ ማለት የጀመሩት ሮሞች ክንዳቸዉ ፈርጥሞ ከአዉሮጳም እልፍ ማለት ጀምረዉ ነበር። ፋርሶች ያፈረሷቸዉን አፍርሰዉ እንደገና ለማንሰራራት ሲፍጨረጨሩ ሮሞች በጡንቻቸዉ ሲያስገብሩ ከሁለቱም ቀድመዉ አቢሲኒያና ቻይና ላይ የገነኑት የአክሱምና የሻንግ ሥርወ መንግስታት ግዛቶቻቸዉን በአዲሶቹም በአሮጌዎቹም የሚያስደፍሩ አይነት አልነበሩም።ፋርሶች-ዳግም በገነኑበት፣ ሮሞች ከፊል አለምን በተቆጣጠሩበት፣ አክሱሞች እስከ ደቡብ አረቢያ በተለጠጡበት፣ ቻይኖች ግዙፍ ግንባቸዉን ባስገነቡበት ዘመን ፋርሳዊዉ ፈላስፋ ተወለደ። ማኒቻኤስ ዞራስትሪያን ከተባለዉ የፋርሶች ሐይማኖት አፈንግጦ ማኒቻኤስዊ የተሰኘ ሐራጥቃ መመስረቱን በሁለት መቶ አርባ አምስት ሲያዊጅ የሮማ ገዢዎች ቅዱስ ጴጥሮስን የዝቅ-ዝቅ ሰቅለዉ-ገደለዉ ክርስትናን ለመፈፀም ሞክረዉ ነበር። ቻይኖች ቡድሐን ተቀናቃኝ ሐይማኖት ከግዛታቸዉን እንዳይዘልቅ ግንባቸው መከታቸው ነበር። ክርስትናን እኒህ ሶስቱ ሐያሎች ባይወጉት ሲያሸሹት አክሱሞች ግን ሊቀበሉት አንድ ሁለት ይሉ ነበር። ከሐይማኖታዊነቱ ይልቅ ፈላስፋነቱ፣ ከፋርሳዊነቱ ይብስ ብዙ ተጉዞ ብዙ አካባቢዎችን ማየት ማጥናቱ፣ መሠረት የሆነዉ ማኒቻኤስ የሮማ፣ የፋርስ የአክሱም የቻይና ነገስታትን አራቱ የአለም ሐያል ገዢዎች አላቸዉ። ባንድ ዘመን የመግነን-መሠልጠናቸዉ፣ መቀናቀን፣ ክርስትናን የመቀበል አለመቀበላቸዉ ልዩነት፣ በፋርሱ ፈላስፋ እማኝነትም የተቃርኖ ታሪክ መጋራት የጀመሩት አክሱም-ሮሞች ብዙ ታሪክ ግን የተቃርኖ ታሪክ እንደተጋሩ አሉ። ክርስትና ኦርቶዶክስ ካቶሊክ ተብሎ በሁለት መከፈሉ የአክሱም ሮሞች የጋራ ተቃርኖ ታሪክ ቅጣይ ነዉ። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ክርስቲያኒቱ ኢትጵያን ዳግም እንዲያጠምቁ ያዘመቷቸዉ ሰባኪዎች ሰበካ በአስራ ሰባተኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን ኢትዮጵያዉንን ማፈጀቱ የአክሱም ሮሞች የጋራ ታሪክ አንድ መጥፎ ገፅታ ነዉ። ወደ ሮማ የተጓዙ ኢትዮጵያዉያን የሐይማኖት ሊቃዉንት አዉሮጳን ማወቃቸዉ የአክሱም ሮሞች የጋራ ምናልባት ደግ ታሪክ እማኝ ነዉ። የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት መሞከሩ አድዋ ላይ ተሸንፎ አፍሮ መመለሱም የአክሱም-ሮሞች የተቃርኖ ታሪክ ቁንጮ ነዉ። የፋሺስቶች ወረራ ግፍ የአክሱም-ሮሞች ገዳዳ ታሪክ ነዉ። ሮሞች በጲላጦስ ወንጀል፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ግድያ፣ በመስቀል ጦረኞች ግፍ፣ በሙሶሊኒ አረመኔነት የወረደባቸዉ እርግማን በዘመን ሒደት ምርቃት ሆኖ ከአለም ጥቂት ምርጥ ቱጃር ሀገር ሆነው ይገኛሉ።
ሐበሻ ችግር ችጋር እንደገፋ ዘመን ሸኝቶ ዘመን መቀበሉ እየቀጠለ ነው። ፋሽስታዊ ፖለቲካዊ ፍልስፍና፣ እብሪት፣ ማንአሕሎኝነት፣ አርባ ዘመን የተቀበረ ቂምም የነዳቸዉ ዱቼ ወይም ቤኒቶ ሞሶሎኒ ያዘመቱት ጦር አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ማግስት ግንቦት 1936 ለድል ብሥራታቸዉ ነጋሪት «የኢጣሊያ ኢምፓየር» መመስረቱን ከሮም ሲያዉጁ ያጨበጨበላቸዉ እንጂ ከኢትዮጵያ ሌላ ያወገዛቸዉ በርግጥ በጣም ትንሽ ነበር። በመጀመሪያዉ የአለም ጦርነት ማብቂያ የለም መንግስታት ማሕበር ሊግ ኦፍ ኔሽንስን ለመመስረት የፈረንሳዮችን ያሕል የተሟገተ የለፋም አልነበረም። ሞሶሎኒ ግዳይ ለጣሏት ኢትዮጵያ ንጉስ ቪክቶር ኢማኑኤልን «የአቢሲኒያ ኢምፐረር» ብለዉ ሲሾሙ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ በኢጣሊያ ላይ የተጣለዉን ማዕቀብ ገቢር ላለማድረግ ፈረንሳይ ታንገራግር ነበር። ጀርመን ከማሕበሩ ብትወጣ አያስገርምም፣ ኦስትሪያና ሐንጋሪ ማዕቀቡን እንደማያከብሩ በግልፅ ማስታወቃቸዉ ግን ድንቅ ነበር። የሞሶሎኒ እብሪት እነፈረንሳይ እንዳሰቡት በኢትዮጵያ ጭዳነት አልሰክን ብሎ ከሒትለር እብጠት ጋር አለምን ሲያጋይ ኦስትሪያ፣ ፈረንሳይና ሐንጋሪ ሌሎችም ከኢትዮጵያ እኩል መክሰል ነበረባቸዉ።
ፋሺት ኢጣሊያ የዘረፈችዉ የአክሱም ሐዉልት ለኢትዮጵያ እንደሚለስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወሰነዉ ጦርነቱ ባበቃ በሁለተኛ አመቱ ነበር። 1947 ። ናትሴ-ፋሺስቶች በአዉሮጳ ሕዝብ ላይ ለፈፀሙት ግፍ የየሐገራቱ ተከታይ ትዉልድ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካሳ ሲከፍል፣ የየዘረፉትን ሐብት ንብረት ሲመልስ የነ-ኢዛና ዉርስ፣ የኢትዮጵያ ኩራት፣ ከሮም-አክሱም ለመግባት ስልሳ ስምንት አመት መጠበቅ ግድ ነበረበት። በፋሽስቶች የመርዝ ቦምብ ያለቀዉ ኢትዮጵያዊ ደም እስከ ዛሬ ከደመ ከልብነት የተሻለ ሥፍራ አላገኘም። ሊግ-ኦፍ ኔሽንስ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአለምን መሪነት የተፈራረቁበትም ሐያላንም ለሌሎቹ ሲሟገቱ የደሐይቱን ሐገር ቅርስ ደም የረሱት ደሐ ከመሆንዋ ሌላ ምናልባት ጩኸትዋን የሚጨኽ መሪ ከማጣትዋ ሌላ ልዩ ምክንያት ሥለነበራቸዉ አልነበረም።
ሞሶሎኒ ሥልጣን ከመያዛቸዉ ጥቂት ቀደም ብለዉ የሞቱትን ቤኔዲክት አስራ አምስተኛን ተክተዉ የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነቱን ሥልጣን የያዙት ፒዩስ አስራ አንደኛ የጀርመን ናሴዎች በ1935 ጤናቸዉ የተጓደለ ያሏቸዉን ዜጎቻቸዉን ማኮላሸታቸዉን አጥብቀዉ ነበር ያወገዙት። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያዉንን በመርዝማ ቦምብ መፍጀቱ ግን ለያኔዋ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከቁም የሚጻፍ አልነበረም።
የአክሱም ሐዉልት ፒዩስ እንደመንፈስ አባት የዘነጉት፣ ሐያላኑ ሐገራት ጥቅማቸዉ ሥላይደለ እንደዘበት ያለፉት የፋሺስቶች ግፍ ያንዠቀዠቀዉ የሐበሻ ደም ጩኸት ገደል ማሚቶም ነዉ። ሐዉልቱ የተመለሰዉ የፒዮስ ሰባተኛ ተከታይ፣ ዳግማዊ ዩሐንስ ጳዉሎስ ባረፉ ቤኔዲኬት አስራ ስድስተኛ በአለ ሲመታቸዉን ባከበሩ ማግስት መሆኑ አዲሶቹ የሮማ ካቲሊካዊት ቤተክርስቲያን መሪዎች ኢትዮጵያን እንደ ጥንት ብጤዎቻቸዉን እንዳይጨክኑባት ማስታወሸ ሊሆን ይገባል።አለም በርዕሠነ ሊቃነ ጳጳሳት ሕልፈት ሹመት ከሮማ በሚቀዳዉ የዘንድሮ ሚያዚያ ታሪኩ መሐል በቀጭኑም ቢሆን የሚጭረዉ እዉነት ሊሆንም ሐቅ ነዉ። የአክሱም ሐውልት መመለስ ለሮማ አክሱሞች የዘመናት የተቃርኖ ታሪክ መቃናት ብስራት ነዉ። ለዛሬዉ ኢትዮጵያዊ ዳቦ ግን አይሆንም። ኢትዮጵያዊዉ ታሪኩን ደረቱን ነፍቶ እንዲናገር ከረሐብ መላቀቅ አለበት። የአክሱም ሐውልት መመለስ ብሥራት ነው። ኢትዮጵያ ላይ ያጠላውን የጦርነት ደመና ሊገፍ ግን አይችልም። ሐውልቱ የቱሪስት መስሕብ ነዉ። ምቾት፣ እንክብካቤ የሚሻዉ ሐገር ጎብኚ በሽታ የተዛመተባት መገናኛ ያልተሟላባትን ሐገር ለማየት የሚጓጓበት ምክንያት ግን የለውም። በየኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን ላይ ለደረሰው ተደጋጋሚ በደል የውጪዎቹ ከተወገዙ ማንቺያኤስ የአለም ታላቅነቷን የመከረላት አቢሲኒያ የአለም የድሆች ድሐ ኢትዮጵያን ለማትረፏ ሰበብ የሆኑት ገዢዎችዋ የማይወቀሱበት ምክንያት አይኖርም።


Nessun commento: