giovedì

የጠጠረው የስደተኛ መመሪያ በጣሊያን


የኢጣልያ መንግሥት ከአለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ clandestini ወይም ሕገ ወጥ ስደተኞችን ወደመጡባቸው ሀገሮች ወደ ሊቢያ እና ቱኒዝያ መልሶ ልኳል። በርካታ ሰዎች ከሰሜን አፍሪቃ የባህር ዳርቻ በትንንሾቹ መርከቦች በሜድትሬንየን ባህር ወደምትገኘዋ የኢጣልያ ደሴት ላምፔዱዛ መጓዝ ይዘዋል። በዚሁ ሂደት መደዳ በመርከብ መስመጥ አደጋ ቁጥራቸውን መገመት የማይቻለው የመርከቡ ተሳፋሪዎች ሕይወታቸውን አሳልፈዋል። ይሁንና የላምፔዱዛ ስደተኞች መቀበያ ጣቢያዎች በመሙላታቸው ኢጣልያ በስደተኞቹ አንፃር አሁንም ጥጥሩን ርምጃ መውሰድዋን ቀጥላለች።
ኢጣልያውያኑ ከሊቢያና ከቱኒዝያ በአዳጋቹ የመርከብ ጉዞ ላምፔዱዛ በደረሱትና ጉዳያቸው ሳይታይላቸው ወዲያውኑ በአይሮፕላን በሚመልሱዋቸው በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ስደተኞች ይህ አሠራር ብርቱ ቁጣ ቀስቅሶዋል። ይሁንና በላምፔዱዛ ያለው የስደተኞቹ መቀበያ ጣቢያ ለተወሰኑ ብቻ እንጂ ለሺህ የሚሆን ቦታ እንደሌለው የታወቀበት ድርጊት ቁጣውን በመጠኑ ሊያበርደው ይችል ይሆናል። ቢሆንም ስደተኞቹን ወደሌላ ትልቅ የኢጣልያ ደሴት ወይም መሀል ሀገር ወስዶና በዚያም ጥቂት አቆይቶ ወደመጡበት መመለሱም ትርጉም አይኖረውም። ከስደተኞቹ መካከልም አንዳንዶቹን በኢጣልያ ኤኮኖሚ ገበያ ላይ ለማሠራት በተቻለም ነበር። ግን ኢጣልያ ውስጥ ሥራ መሥራት የሚችል ግለሰብ ኢጣልያ ከመግባቱ በፊት የሥራ ፈቃድ ማውጣት ግዴታ አለበት።
ኢጣልያ በሌሎች አውሮጳውያት ሀገሮች እንደሚታየው ለዘብ ያለ የተገን አሰጣጥ ሕግ የላትም። በመሆኑም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ተመልካች መሥሪያ ቤት ሊቢያን ብቻ ሳይሆን ኢጣልያንም ተመሳሳይ ሕግ እንድታወጣ መጠየቁም ይታወሳል።
እነዚህ ስደተኞች በወቅቱ በብዛት ከሰሜን አፍሪካ ለሚጎርፉበት ድርጊት በየዓመቱ እንደሚታየው የአየሩ ፀባይ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚበላሽበትና የመርከቡ ጉዞ አዳጋች የሚሆንበት ድርጊት ተጠያቂ ነው። የኢጣልያ ተቃዋሚ ወገኖች የመሀል ቀኙ መንግሥት የሚከተለው የፍልሰት ፖሊሲ ግቡን እንደሳተ ቢያስታውቁም የሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ወደሀገሩ የገቡ ሕገ ወጥ የሚላቸው ስደተኞች አሀዝ ባለፈው ዓመት መቀነሱን አመልክቶ ወደፊትም ተመስሳይ ርምጃ እንደሚወስድ ገልፆዋል።
ስድሳ ሚልዮን ወደሚኖሩባትና በየአመቱም አሥር ሺህ ክላንዴስቲኒ ስደተኞች ወደሚገቡባት ኢጣልያ ከሰሜን አፍሪቃ በጥቂት ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች መግባታቸውን ማጋነኑ ባልተገባ ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ። የኢጣልያ መንግሥት በወቅቱ ብዙ በሚያከራክረው የፍልሰት ጉዳይ ላይ የያዘው አቋም አሁንም ግልፅ አይደለም። አንዳንዶቹ ባለሥልጣናት በሀገሩ ያልተመቸው ሁሉ ወደ አውሮጳ መግባት የለበትም የሚል አቋም ሲይዙ፣ ሌሎጭ ደግሞ የኤኮኖሚ ችግርም ለተገን አሰጣጡ ደምብ በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል ይላሉ። የኢጣልያ ሀገር አስተዳደር ሚንስትር ይሚሉትም ስደተኞች ወደ አውሮጳ ከመምጣታቸው በፊት የሚያርፉበት አንድ የስደተኞች መቀበያ ጣቢያ በሰሜን አፍሪቃ እንዲቋቋም የቀረበውን ሀሳብ ሲደግፉ ኢጣልያዊው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሀሳቡን ውድቅ አድርገውታል። በዚሁ ፈንታ ስደተኞቹን በየሀገሮቻቸው ለማቆየት ይቻል ዘንድ ለነዚሁ ሀገሮች ኤኮኖሚያዊ ርዳታ ቢሰጥ ትክክለኛ መሆኑን ገልፀዋል። ይሁንና የኢጣልያ መንግሥት በዚሁ ሀሳብም ላይ የያዘው አቋም ተፃራሪ ነው። ለዚህ አመትም ባወጣው የበጀት ረቂቅ ለልማቱ ርዳታ የመደበው ከፊል ንዑስ የሆነበት ድርጊት የሕገ ወጥ ስደተኞች ችግር ለማቃለል እንደማይረዳ አሳይቶዋል።


Nessun commento: