mercoledì

ፈለገ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ኢጣሊያ ሚላኖ


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጣሊያን ሀገር ተቋቁማ ለምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች:: በጣሊያን ህልውና እና ቦአ ይዘው ያሉ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንናት ሁለት ሲሆኑ እነሱም 1ኛ የሮም ደብረጽዮን ቅድስት ማርያምና 2ኛ የሚላኖ ፈለገ ለላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ናቸው::

የፈለገ ለላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በልዩ ልዩ ምክንያት ከሀገራቸው ወጥተው ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ከፍተኛ የሆነመንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ:: ቤተ ክርስቲያኑ ከዕለት ወደ ዕለት እያደገና እየሰፋ፣ የሕዝቡ ቁጥር እየበዛ የሚሰጠው አገልግሎት እየተጠናከረ፣ ብዙ ገብረ ተአምራት በቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት በእግዚአብሔር ቸርነት እየተፈፀመ ይታያል::

በዚህ ቤተ ክርስቲያን ኢ-አማንያን ወደ እምነት፣ መናፍቃን ወደ ተዋህዶነት ተመልሰዋል፣ ሕሙማን በፀበል ድነዋል፣ የተጨነቁና ያዘኑ በትምህርት ተፅናንተዋል:: በየሳምንቱ በዕለተ ሰንበት ቅዳሜና እሁድ በዓበይት በዓላት ሥርዓተ ቅዳሴ ይደረጋል፣ ክርስትና ይፈፀማል፣ ሥርዓተ ተክሊል፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ ሕሙማንን ማጥመቅ የወንጌል ስብከት፣ የምክርና የማስታረቅ አገልግሎት ይሰጣል:: በቋሚነት የተመደቡና በትርፍ ጊዜያቸው የሚያገለግሉ ካህናት አሉ የፍቅርና የሰላም አገልግሎት ይሰጣል:: ቤተ ክርስቲያኑ ዘመናዊ አሠራርን እንዲከተል አገልግሎቱ እንዲጠናከር ተልዕኮው እንዲሰምር፣ የሕዝቡም ቁጥር እንዲጨምር፣ የልማት ሥራ እንዲኖር የወንጌል ትምህርት እንዲስፋፋ ሰበካ ጉባኤውና አስተዳደሩ እንዲሁም ካህናቱና ምዕመናኑ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ::

የሰበካ ጉባኤ
በኢትዮጵ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ከመንበረ ፓትርያርክ እሰከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተቋቁሞአል:: ቤተክርስቲያን በካህናትና በምዕመናን ሕብረት በሰበካ ጉባዔ እንድትደራጅ ታስቦ በአዋጅ ቁጥር 83/85 መሠረት ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም. ታትም በወጣው ቁጥር 1 ቃለ ዓዋዲ ሚያዝያ 19 ቀን 1990 ዓ.ም. በተሻሻለው ታህሳስ 10 ቀን 1974 ዓ.ም. በታተመው ማሻሻያ ደንብ ግንቦት 9 ቀን 1977 ዓ.ም. በወጣው ውስጠ ደንብ መሠረት አንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን የምትመራዉ በሰበካ ጉባኤ ነው:: ቤተ ክርስቲያን በማህበረ ካህናትና ምዕመናን መደራጀቷ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ አስተዳደር መመራቷ ከጥንት ጀምሮ ያለና የነበረ የሚኖር ነው እንጂ እንግዳ የሆነ አዲስ ነገር አለመሆኑን በታሪክና በቅዱሳት መጻሕፍት የተፃፈውን መመልከት ይቻላል::
የቤተ ክርስቲያን አመራር ዋና አስተዳደሯ በክርስቶስ ዘመን በሐዋርያት ጉባኤ ተመክሮና ተወስኖ በተላለፈው ሕግና ሥርዓት መሆኑን በማህበረ ካህናቱ እና ምዕመናን የአንድነት ጉባኤ በተመረጡ ቅዱስ መንፈስ በአደረባቸው ኃላፈዎች ሥራ አስፈጻሚነት ይካሄድ እንደነበረ እንረዳለን:: ቤተ ክርስቲያን ከምዕመናን አስተዋፅኦ ተሰብስቦ በሚገኘው ገንዘበብ ለአገልጋዮቿ መተዳደሪያ፣ ለሐዋርያዊ ሥራ ማስኬጃና ለችግረኞች መርጃ እንዲዉል መደረጉን ቅዱስ መጽሐፉ ይነግረናል::
በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ አለመግባባት ቢፈጠር በፍትሕ መንፈሳዊ መተያየትና መወሰን ያለበት መሆኑን በመገንዘብ ወጣቶችን በሰንበት ት/ቤት ለማደራጀት ሰበካ ጉባኤ ተቋቁሞአል::
ሰበካ ጉባኤ ያለ ቤተ ክርስቲያን ሊኖር አይችልም:: ከሰበካ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ትቀድማለች:: ቤተ ክርቲያን ከሌለች ሰበካ ጉባኤ የለም ማለት ነው:: የጣሊያን ሚላኖ ፈለገ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርሰቲያን በእግዚአብሔር ፈቃድ በምዕመናኑና በካናቱ ጥረትና ትብብር የተቋቋመው ታህሣሥ 22 ቀን 1993 ዓ.ም. ሲሆን ለጥቂት ጊዜ በመሥራች ኮሚቴው አስተባባሪነትና አደራጅነት በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ ውስጥ አገለልግሎት ሲሰጥ ቆይቶአል::
በመቀጠልም ቃለ አወዋዲውን መሠረት በማድረግ ሰበካ ጉባኤ ተቋቁሞአል ሰበካ ጉባኤው ከካህናትና ከምዕመናን እንዲሁም ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተውጣጡ 9 አባላት ይገኙበታል:: ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው ሰበካ ጉባኤ ከደብሩ አስተዳዳሪና ከካህናት እንዲሁም ከምዕመናን ጋር በፍቅርና በአንድነት የሚመራ ቤተ ክርስቲያንን የሚወድና ሃይማኖቱን የሚያከብር ስለሆነ ለቤተ ክርስቲያን ልማትን በማሰብ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ መለያየት ዘረኝነት እንዲጠፋ፣ ሰንበት ት/ቤት እንዲስፋፋ፣ ንዋየ ቅድሳት እንዲሟላ፣ የካህናት ኑሮ እንዲስተካከል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል::
የፈለገ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሚገለገልበት ሕንፃ በትውስት የተገኘ በመሆኑ ራሱን የቻለና የራሳችን የምንለው ቤተ ክርስቲያን እንዲሰጠን ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ሲያቀርብና ጉዳዩን ሲከታተል ብዙ ጊዜ ከፈጀ በኋላ ለፍጻሜ አድርሶ ለመረከብ በቅቷል:: ከዚህም ሌላ ቤተክርስቲያንም ሕጋዊነት እንዲኖራት በማሰብ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር አሰስፈላጊውን በማሟላት በሀገሩ ህግና ደንብ መሠረት እውቅና እንድታገኝ ፈቃድ እንዲኖራት አድርጓ::
ከምዕመናኑ በስጦታ፣ በንዋየ ቅድሳት ሽያጭ፣ በሰበካ ጉባኤ እና በሙዳየ ምፅዋት እንዲሁም ከልዩ ልዩ ክፍያ የሚገኘው ገንዘብ በደብሩ ስም ባንክ ተከፍቶለት ሕጋዊ በሆነ ገቢና ወጪ እንዲሰራ አድርጓል:: ወጪውም በምዕናንና በካናት ጥምር ፊርማ ይንቀሳቀሳል:: ሰበካ ጉባኤው እንደ አስፈላጊነቱ በየ ሳምንቱና በየወሩ መደበኛ ስብሰባ እያደረገ ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እድገት ስለ ሕዝቡ አገልግሎት፣ ስለ ወጣቱ ትምህርት ሰፈፋ ያለ ውይይት ያደርጋል በየዓመቱም ለምዕመናኑ ሪፖርት ያቀርባል::

ስብከተ ወንጌልን በሚመለከት ከደብሩ አስተዳዳሪና ካህናት ጋር በመነጋገር ኮርስ እንዲሰጥ፣ በካሴት፣ በጽሁፍ ትምህርት እንዲዘጋጅ ልዩ ጉባኤ እንዲኖር ታዋቂ መምህራን እንዲጋበዙ አድርጓል:: በቃለ አዋዲው መመሪያ መሠረት ምዕመናን በሰበካ ጉባኤ አባልነት እንዲመዘገቡ፣ አሥራት እንዲያወጡ፣በቤተ ክርስቲያን መመሪያ ሥር እንዲኖሩያደርጋል:: ንዑሳን ኮሚቴዎችን አቋቁሞአል የልማት ኮሚቴ፣ የሰንበት ት/ቤት የሥራ አመራር ኮሚቴ፣ የሽያጭ ኮሚቴ፣የገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴና የበዓል አዘጋጅ ኮሚቴ ተቋቁሞአል::


1 commento:

serkemamare ha detto...

ወንድሞቼ !
ድህረ-ገፃችሁ በቅርቡ ሰለአገኘሁት ብዙ ጠቃሚ ጉዳዮችን ያዘለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ::
ሆኖም ሰለሚላኖ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያኑ የተፃፈው ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም :: ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር:: ይህንን ለማለት የፈለኩት አጠገቡ ሰለምኖርና የቤተ ከርስቲያኑን ስም ለማዳን የተበተነ ጽሑፍ በመሆሩ እውነተኛ ታሪኩ ይህ አይደለም:: የውስጥ ችግሩ አሁንም አላለቀም ::
ሰላም ሁኑልኝ