domenica

የውጪ ዜጎች ለእረፍት ወደ የሀገራቸው ሊሄዱ ይችላሉ


A casa col cedolino delle Poste
በአሁኑ ጊዜ የመኖሪያ ፈቃድ ለማሳደስ ማመልከቻ በፖስታቤት አቅርበው እስከሚሰጣቸው ድረስ የሚጠባበቁ የውጪ ሀገር ዜጎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው። ይህንን የሶጆርኖ እድሳት ለሚጠብቁት በሙሉ ምንም እንኳን በእጃቸው የመኖሪያው ፈቃድ ገና ታድሶ ባይሰጣቸውም በዚሁ ወቅት ላይ ወደ የሀገራቸው ለአጭር ጊዜ እረፍት ለመሄድ እንደሚችሉ ሰሞኑን ከሀገር አስተዳደርና የህዝብ ጥበቃ ክፍል ለድንበር ጠባቂ ፖሊስ ጽህፈት ቤት በተላለፈው የቴሌግራም መግለጫ መሠረት ሊታወቅ ተችሏል። (መግለጫውን ከዚህ ያውርዱ) ይኸውም የመኖሪያ ፈቃዳቸውን ለማሳደስ ፖስታ ቤት በሄዱበት ጊዜ የተሰጣቸውን የደረሰኝ ወረቀት በመጠቀም (cedolino delle Poste) ለእረፍት ወደ ሀገራቸው ሄደው መመለስ ይችላሉ።
.
ከፖስታቤት በተሰጣቸው የእድሳት መጠባበቂያ የሆነው የደረሰኝ ወረቀት ይዘው ለብዙ ወራት በመጠባበቅ የነበሩና በዚህም ምክንያት በአለፈው የፋሲካ እና የገና በዓላት ላይ ሀገራቸው መሄድ ላልቻሉት አሁን ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። ከዚህም በላይ የሶጆርኖ እድሳት የሚጠብቁት የውጪ ሀገር ዜጎች መብታቸው ሶጆርኖ ካላቸው ጋር ሙሉ በሙሉ አንድ አይነት ነው ማለት ይቻላል። ነገርግን ከመጡበት ሀገር ሌላ ወደ ሌሎች ሀገሮች እንደፈለጉት መውጣትና መግባት የመቻልና ያለመቻላቸው ጉዳይ የሚያነጋግር ሆኖ ተገኝቷል። በዚሁም መግላጫ ላይ የአጭር ጊዜ እስከሆነ ድረስ፣ እንደየሚሄዱበት ሀገር የሚወሰንና እንዳላቸው የፈቃድ አይነት ሊለያይ እንደሚችል ይገልጻል። ለምሳሌ (il viaggio non dovrà prevedere il transito in altri Paesi dell'area Schengen)
.
ከጣሊያን በሚወጡበትም ሆነ በሚገቡበት ጊዜ
1 - ከፖስታቤት የተሰጣቸውን የደረሰኝ ወረቀት
2 - ፓስፖርታቸውን
3 - ጊዜው የወደቀበትን የሶጆርኖ ኮፒውን (ግልባጭ) ማሳየት ይገባቸዋል።
4 - (ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ...)
ከላይ የተጠቀሱት ሰነዶች በመውጪያዎም ሆነ በመግቢያዎ ጊዜ በድንበር ፖሊሶች ማህተም የሚደረጉባቸው በመሆናቸው በጉዞ ላይ ምንግዜም በእጅ የሚያዙ ናቸው።
.
ከልጆቻቸው ጋር ለሚጓዙ ወላጆች ጊዜያዊ ሶጆርኖ ይሰጣል
ሌላው ደግሞ በሀገር አስተዳደር የተፈረመበት ሆኖ ለፖሊስ ጽህፈት ቤት (ኩዌስቱራ) በተላለፈ ደብዳቤ ላይ (ደብዳቤውን ከዚህ ያውርዱ) እድሜአቸው 14 ዓመት ያልሞላቸው ልጆች የራሳቸው ሶጆርኖ ሊኖራቸው የማይችሉ በመሆናቸው በወላጆቻቸው ሶጆርኖ ላይ የተመዘገቡ እስከሆነ ድረስ የሶጆርኖውን እድሳት ተጠባባቂ ለሆኑ ወላጆች ለየት ያለና ጊዜያዊ የሆነው የሶጆርኖ ወረቀት ከፖሊስ ጽህፈት ቤት ሊሰጣቸው እንደሚችልና በዚሁ ከልጆቻቸው ጋር አንድ ላይ ለእረፍት ወደሀገራቸው መሄድ እንድሚችሉ ተገልጿል።
ከዚህ በፊት ወላጆች ጊዜው የወደቀበት ሶጆርኖዋቸው ላይ ልጆቻቸውን ያላስመዘገቡ ከሆነና ነገርግን አሁን በሚያሳድሱበት ጊዜ ያስመዘገቡ ከሆነ ከፖስታ ቤቱ ለመጠባበቂያ በተሰጠው የደረሰኝ ወረቀት ላይ የልጆቻቸው ስም ሊኖር ስለማይችል የተሰጣቸውን የፖስታ ቤት ደረሰኝ ማስረጃና ከፓስፖርት ጋር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ይዘው በመቅረብ ፎርም ሞልተው የልጆቻቸው ስም ያለበት ጊዜያዊ ሶጆርኖ ሊያገኙበት ይችላሉ። ይህም ጊዜያዊ ሶጆርኖ የሚያገለግለው ለዚሁ የቤተሰብ (የደርሶ-መልስ) ጉዞ ብቻ ይሆናል።
28 06 2007 Abraham Z.


Nessun commento: