mercoledì

አሳዩን አትንገሩን


ዶክተር ዘለቀ እሬሶ
...... አንድ ጸሐፊ በቅርቡ የአገራችን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት “አሳዩን አትንገሩን” በሚል አርስት የሚከተለውን አስፍሮ ነበር:: በአለምም ሆነ በአንድ አገር ታሪክ ዉስጥ የአገር መሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች አዛዉንቶች፣ ህዝብና ሌሎች ሌሎች የሚፈተኑበት ልዩ ወቅት ይከሰታል:: ያም ወቅት አብዛኛዉን ጊዜ ችግር በሚከሰትበት ወቅት ይሆናል:: ያን ችግር ለመፍታት በሚያደርጉት አዎንታዊ እንቅስቃሴ፣ ያን ችግር ለማባባስ በሚጫወቱት ሚና ወይም በሚይዙት የአያገባኝም ወይንም ደንታቢስነት ሚና ማንነታቸዉ ይለካል:: መልክቱ ባጭሩ ተግባራዊ እንሁን ማለቱ ይመስለኛል::
...... በኢጣሊያን አገር የሚኖሩትን የዉጭ አገር ዜጎች የኑሮ ሁኔታ በተመለከተ ሰሞኑን ከምን ጊዜዉም በበለጠ የተለያዩ ወሬዎች ይነፍሳሉ አልፎም ይተረካሉ:: ይህ ዜና አዎንታዊ እንቅስቃሴ? ወይንስ ችግር የማባባስ ዘመቻ? መልሱ እንደፊደል ምርጫ ጥያቄ ሁሉም ሊሆን ይችላል::
...... የመጀመሪያዉ የዉጭ አገር ዜጋዉ ከገጠሙት የቢሮክራሲ ዉጣ ዉረድ እንዲላቀቅ፣ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳይኖረዉ፣ የስራና የህክምና ችግሮች እንዳይገጥሙት ማለትም ግዴታዉን ተረድቶ መብቱ ተከብሮለት አምራች ዜጋ እንዲሆን አስፈላጊዉን ሁሉ ለማድረግ ቢያንስ የሚሞክሩትን አነስተኛ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያጠቃልላል::
...... ሁለተኛዉ ደግሞ በሰዉ ቁስል እንጨት ስደድበት አይነት ነገር ነዉ:: የዉጭ አገር ዜጋዉን ከወንጀል ጋር በማጣመር ሁሉንም ወንጀለኛ በማድረግ የዉጭ አገር ዜጎች ገደሉ፣ ሰረቁ፣ አጭበረበሩ፣ ቀጠፉ፣ ደፈሩ፣ አቆሸሹ፣ ወዘተ በማለት የዉጭ አገር ዜጋዉ ከህግ ዉጭ እንደሆነና የተመቻቸ ኑሮ እንዳለዉ አስመስለዉ በማቅረብ እንዲያዉም ይባስ ብሎ የመንግስት እርዳታ ሁሉ የሚሰጠዉ ለዉጭ አገር ዜጋ ብቻ ነዉ በማለት የአገሬዉን ህዝብና የዉጭ አገር ዜጋዉን ለማጣላትና ለማጋጨት ከፍተኛ ቅስቀሳ በስዉር እየተካሓደ ነዉ::
...... ይህንንም ስል ሁሉም የዉጭ አገር ዜጋ ወንጀል አይሰራም ለማለት ፈልጌም አይደለም:: እንዲያዉም ሰርቶ ከመኖር ይልቅ ሀገ ወጥ በሆነ መንገድ ሐብታም መሆን እንደሚቻል መጥፎ ትምህርት በማስተማር ላይ የሚገኙም እንዳሉ ተስኖኝ አይደለም:: ታዲያ እንክርዳዱን ከስንዴ መለየት አስፈላጊ በሆነበት ባሁኑ ሰአት አብዛኞች የኢጣሊያን አገር የዜና ማሰራጫዎች የሚጽፉአቸዉ ጽሁፎችና አርስታቸዉ ከመለያየቱ የተነሳ ሕግ አክባሪዉንና ወንጀለኛዉን የዉጭ አገር ዜጋ እንኳን በአግባቡ ለይቶ ማወቅ አልተቻለም::
በጠቅላላዉ ለመዝጋት ያህል ሰሞኑን በአንዳንድ የኢጣሊያን አገር ጋዜጦች ላይ የዉጭ አገር ዜጋን በተመለከተ ጥሩ ጥሩ አርስቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፣ ለዉጭ አገር ዜጋዉ ግን ምንም የተቀየረለት አንዳችም ነገር አይታይምና ወሬዉ በተግባር መተርጎም እንዳለበት የሚመለከተዉን ክፍል ከመጠየቅ ወደ ኋላ ማለት አይገባም::
...... ስለ ጽሁፉ አስተያየት ካለዎት zeleke_eresso@yahoo.it

Nessun commento: