venerdì

የሀገራችን ባህላዊ ምግቦች አሠራር


እህቶቼ ወንድሞቼ ... በዚህ ገፅ ላይ በተለያዩ አርዕስት ላይ አስተዋፅዖ ማድረግ ይችላል ስለተባለ እኔም እስቲ ሙያዬ በሆነው ልካፈል ብያለሁ። ያው የምታውቁትን አንዳንዱን የሀገራችን የምግብ አሰራር እንዴት እንደሆነ በጽሁፍ ልማቅረብ ፈልጌ ነው። ይህም እኮ ቢሆን ባህላችንን ለማሳየት ይጠቅማል። አይደለም እንዴ? ምቼም እናንተም ወንዶችም ብትሆኑ የሴት ስራ ብላችሁ ከማንበብ እንደማትቆጠቡ ተስፋ አደርጋለሁ:: ለምሳሌ "የምስር ወጥ እንዴት ተደርጎ ነው የሚሰራው?" ብዬ ብጠይቃችሁ "ከምስር ነው" እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ:: እኛ ምን አገባን ፓስታና መኮረኒ እያለ፣ እኛ ምን አገባን ሩዝ እያለ ካላችሁም መልካም ነው:: ለማንኛውም የአሰራሩን፣ ቅደም ተከተሉን፣ የእሳቱን መጠን፣ የምስሩን መጠን፣ የጨዉን መጠን፣ ወዘተ... ተጠንቀቁ:: ይህንንም ለሴተ ላጤዎችና ለወንድ ላጤዎች ነገሩ እንዲገባቸው በዝርዝር ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።
.
ያበሻ ጎመን በበርበሬ
.
* መጀመሪያ ጎመኑ በጣም ደቆ ይከተፋል ::
* ከዚያም በብረት ድስት ወይም ሸክላ ድስት (እዚሁ ጣሊያን ሀገር ከተገኘ) በደንብ ታጥቦ ይጣዳል ::
* ጎመኑ ብቻ ድስቱ ዉስጥ ይገባና በደንብ ተከድኖ እንዲበስል ይደረጋል :: (አስታዉሱ ምንም ዉሀም ሆነ ሌላ ነገር አይገባበትም በደረቁ ነው ... የራሱ ዉሀ ስላለው በንፋሎትና በራሱ ዉሀ ይበስላል :: እንዲበስል የእሳቱ መጠን እኔ በጋዝ ስለምሰራ .. እንዳያር በጣም መከፈት የለበትም ለሰስ ያለ መሆን አለበት :: እሳቱ ከበዛ የስሩን ቶሎ ያሳርረዋል እረጋ ሲል ግን እንፋሎት እንዲኖረው ይረዳል :: ከ20 ደቂቃ በሁዋላ ከፍቶ ማማሰል ያስፈልጋል ..ከአረንጓዴነቱ ወጥቶ ጠቆር ያለ አረንጓዴ ከሆነ በስሏል ማለት ነው)
* ድስቱን አዉጥቶ ጎመኑን በሌላ ሰሀን መገልበጥ
* ሽንኩርት ድቅቅ አድርጎ መክተፍ (ትልቁ ከሆነ 2 ራስ ሽንኩርት ይበቃል)
* ነጭ ሽንኩርት ግማሽ ራስ አድቅቆ መክተፍ (መፈጨት የለበትም)
* ድስቱን ጥዶ መጀመሪያ ቀይ ሽንኩርትና ዘይቱን በጣም እንዳይሞት አድርጎ መጥበስ
* ከዚያም በርበሬ ሳይበዛ ጨመር አድርጎ ማቁላላት
* ጎመኑን መቀላቀልና ማዋሀድ
* ቀጥሎ ነጭ ሽንኩርቱን መጨመር
* በመጨረሻ ለጋ የበሻ ቅቤ ትንሽ ጣል አድርጎ ካዋሀዱ በሁዋላ አዉጥቶ ትንሽ ቅምስ ማድረግ።
አቤት ሲጣፍጥ!! ስትፈልጉ እዚሁ በፓዴላ ላይ በምንሰራው እንጀራ ወይም በዳቦ መብላት ነው። አደራችሁን እጃችሁን እንዳትቆረጥሙ ታዲያ::
ሌላ የምግብ አሠራር ይዤ እስከምቀርብ እስቲ ይመቻቸሁ እላለሁ።
Marta Pedrini
.
የዶሮ አሰራር
.
አብዛኛዉ ሰው ሲሰራ ያየሁት ሁሉንም በተራ እያስገቡ ሲያበስሉ መዋል ነው:: ከዛ ይልቅ አጠር ያለ መንገድና የሚጣፍጠው::
* ለ1 ዶሮ 3 ኪሎ ሽንኩርት በጣም ደቆ ይከተፋል
* ሁለት ራስ ነጭ ሽንኩርትና ዝንጂብል በጣም ሳይበዛ መፍጨት ... (ዝንጂብሉ ሳር ነገር እንዲኖረው መሆን የለበትም። በደንብ ይድቀቅ)
* የተከተፈዉን ሽንኩርት ከሩብ ሊትር ዘይት ጋርና ጨው ጨምሮ ድስቱ ዉስጥ አስገብቶ በደንብ መግጠምና መጣድ (ምንጊዜም ወጥ ሲሰራ ሳት መብዛት የለበትም)
* ከ15 ደቂቃ በሁአላ መክፈትና ማየት (እርግጠኛ ነኝ ሽንኩርቱ በደንብ ሙሽሽ ብሎ ይበስላል)
* ከዚያም በርበሬ ወይም ድልህ መጨመር (ሁለት ጭልፋ (የወጥ ማዉጫ ማንኪያ ) ትልቅ ጭልፋ መሆን የለበትም መካከለኛው ይበቃል)
* ከዚያም በደንብ እጅ ሳይቦዝን እያማሰሉ እንዳያር ማማሰል ... በደንብ ከለሩ ወደ ደማቅ ቀይ ሲሆን የተገነጣጠሉትን ዶሮዎች አብሮ ማዋሀድና ከድኖ ማብሰል ::እንዳያር በየጊዜው እየከፈቱ ማገላበጥ ::
* የተፈጨዉን ነጭ ሽንኩርትና ዝንጂብል ማስገባት :: ከዚያም የማዉጫ ዉሀ በጣም እንዳይቀጥን ሆኖ መጨመር ::
* እጥር ምጥን ሲል ማለትም ዉሀዉን ሲመጠው እና ሲማሰል ለድለድ ሲል ቅቤ በጭላፋ ዛቅ አድርጎ መጨመርና ማዋሀድ ከዚያም ማዉጣትና እስኪበርድ መጠበቅ
* የተቀቀለ እንቁላል ከላጡ በሁዋላ በሹካ ወጋ ወጋ አድርጎ ወጡ ዉስጥ ቢቀላቀል የበለጠ የዶሮ ባህላዊውን አሰራር ያጎላዋል::
. ... ከዚያማ አቤት አቤት!! ... ስንት ጊዜ "እጂሽን ለወርቅ እንጂ ለእሳት አይበለው" ተብዬበታለሁ መሰላችሁ!!
Marta Pedrini
.
የክትፎ አሠራር
.
1ኛ. ብዙን ጊዜ ለክትፎ ስራ የቂቤው አይነት እና የቂቤው አነጣጠር በጣም ወሳኝነት አለው። ነገር ግን ሁሉም እንደፍላጎቱ ቅቤውን ሊያዘጋጅ ይችላል። በብዛት ግን ያልበሰለ እና ለጋ ቂቤ ይመረጣል። 2ኛው አስፈላጊ ነገር የሚጥሚጣው አዘገጃጀት ነው።3. የስጋው አይነት ቀይ ስጋ በተቻለ መጠን ዉሀ እንዳያዝል ትኩስ ስጋ ቢሆን ይመረጣል .. በ እጅ ወይም በማሽን ከተከተፈ በሁአላ .. በዉስጡ ያለውን ስራስር እናነጭ ስጋ ለቅሞ ማውጣት ያስፈልጋል። እንዲሁም ስጋው በማሽን ከተከተፈ .. ሊያያዝ ስለሚችል .. ከተከተፈ በሁላ የተያያዘ ስጋ ካለ መበታተን .. አስፈላጊ ነው። አዘገጃጀቱ ፡-
በመጀምሪያ በዝርግ መጥበሻ በጣም በዝቅተኛ እሳት .. ለግማሽ ኪሎ ስጋ ... ወደ 3ጭልፋ ቂቤ ማቅለጥ (እንደፍላጎት ማድረግ ይቻላል ) ... እና እዚያው የቀለጠው ቂቤ ላይ ሁለት የሾርባ ማንኪያ ሚጥሚጣ እና ግማሽ የሾርባ ማንኪያ የተፈጨ ጨው አድርጎ መቀላቀል .. እሳቱ ሳይበዛ ቂቤውን ለማቅለጥ ብቻ መሆን አለበት.. ቅቤው ነንደቀለጠ እና እንደተዋሀደ መጥበሻውን ከሳት ላይ አዉርዶ ስጋውን ጨምሮ በጣም በፍጥነት መለወስ ወይም መታሸት ይኖርበታል። ከዚያ ወደ ማቅረቢያ እቃ ዉስጥ ገልብጦ ማቅረብ። ታዲያ ምን ያደርጋል! እዚህ አይቻልም እንጂ ቢቻል በቆጮ ነበር ... ከጠፋም ያው በfarina እንጀራችን ... አደራ .. እንግዲህ ሙያ እንደየቤቱ ይለያያል ... መልካም ክትፎ
Marta P.
.
ቀይ የስጋ ወጥ
.
(ለ4 ሰው የሚሆን የሚያስፈልጉን)
- 3ራስ ቀይ ሽንኩርት
- 1ራስ ነጭ ሽንኩርት
- ዝንጅብል (እንዳስፈላጊነቱ )
- ኮረሪማ፣ ጥቁር/ነጭ ቅመም የመሳሰሉት
- ግማሽ ኪሎ ስጋ (በሚፈለገው መንገድ ሳያንስ እና ሳይተልቅ መክተፍ ):
- 2 የሾርባ ማንኪያ በርበሬ :
- 2 የበሰለ ቲማቲም :
- ጨው እና ዉሀ .. ዘይት
አሠራሩ
1. የተከተፈውን ቀይ ሽንኩርት በ መካከለኛ እሳት ላይ ከድኖ መጣድ እና ሽንኩርቱን ለ3-5 ደቂቃ በ እንፋሎቱ እንዲበስል ማድረግ
2. ቲማቲሙን አንዴ በፈላ ዉሀ ገንፈል ካደረግነው .. እንዲላጥልን ከሆነ .. በሁላ ቲማቲሙን ልጦ .. ከትፎ ሽንኩርቱ ላይ መጨመር እና ለ2/3 ደቂቃ ከሽንኩርቱ ጋር ማዋሀድ
3. ከዚያ ዘይት ጨምረን ታሁንም ከሁለት ደቂቃ በሁላ 2 የሾርባ ማንኪ በርበሬ ጨምሮ (አሁን ዉሀ አይኖረውም ሽንኩርት ቲማቲም እና ዘይት ብቻ ነው ነንፋሎቱ ስለሚወጣ ) ለ5ደቂቃ በርበሬው እንዳያር ቶሎ ቶሎ ማማሰል እና .. ዉሀ ጠብ እያደረጉ ለተወሰ ደቂቃ ማብሰል ..
4. አሁን ከትፈን ያዘጋጀነውን ስጋ መጨመር እና አሁንም ዉሀ ሳይኖረው በደረቁ በዘይቱ እና በበርበሬው እንዲጠበስ ማድረግ ስጋውን .. ድስቱን ግን እየያዘ ካስቸገረን ዉሀ ጠብ እያደረጉ ለ 10 ደቂቃ ስጋውን ከ ቁሌቱ ጋር በደንብ ማብሰል .. እና የተፈጨ ዝንጅብ እና ነጭ ሽንኩርቱን ጨምረን አብረን ማብሰል .. ከዚያ ስጋውን በ 15 ደቂቃ በደረቁ በቁሌቱ ካበሰልን በሁላ 5. አንድ ሌትር ዉሀ ከልሰን ለ10 ደቂቃ እሳቱን ጨመር አድርገን ማንተክተክ ..ጨውም እንደሚፈለገው መጠን (1 የሻይ ማንኪያ ) እና እንደ መከለሻ .. ጥቁር /ነጭ ቅመም መጨረሻ ላይ መጨመር ... ሊወጣ ሲል ወይም ከ ቁሌቱ ጋ ዉሀ ሳንከልስ ሁለት የሾርባ ቂቤ ብንጨምርበት ሸላይ ይሆናል .. ወጡ በደንብ ከበሰለ .. አረፋ ነገር አይኖረውም ... ስለዚህ ዉሀ ከጨመርን በሁአላ ለ 15 ደቂቃ አብስሎ ማውጣት ..
ከዚያማ በቃ ከዛማ በእንጀራ ማገላበጥ ነው ... ቢቻል መጎራረስ !
.
የበግ ዱለት ለ4 ሰው
.
* ጨጓራዉ በደንብ ንጹህ እስከሚሆንና ሽታዉ ጭራሽ እስኪጠፋ መታጠብ አለበት ከዚያም አንጀቱንና ጨጓራዉን ዉሀ ጥዶ ገንፈል ማድረግና ማዉጣት
* ከዚያም ጥቁሩ ጨጓራ ጸጉሩ መገፈፍ (መፋቅ ) አለበት አንዳንድ አንጀቶች ዉስጥም መዉጣት ያለበት አለ እሱን እየላጉ ማዉጣት ከዚያም በጣም አድቅቆ መክተፍ
* ሌሎቹ የዱለት ክፍሎች እንደ ልብ ኩላሊት እና ጉበት ንጹህነታቸው ታይቶ በደንብ ጸዳድተው ደቀው ተከትፈው በንጹህ ሰሀን ይቀመጡ
* ሁለት ራስ ሽንኩርት የፈረንጅ ሽኝኩርት ነው በደንብ ደቆ ይከተፋል
* አንድ ራስ ነጭ ሽንኩርት አይፈጭም ደቆ ይከተፍ
* ሁለት ረጃጅም የሚያቃጥሉ ቃሪያዎች በደንብ ደቀው ይከተፉ
* ብረት ድስት መጣድና ሳቱን ለሰስ አድርጎ ከፍቶ ዘይቱ ሳይበዛ ከቀይ ሽንኩርቱ ጋር አድርጎ በጣም እንዳይሞት አድርጎ ጠበስ ማድረግ ከዚያ ላይ ነጭ ሽንኩርቱን መጨመር አስታዉሱ ዉሀ አይገባበትም
* ከዚያም ሳይከደን መሰል መሰል አድርጎ ደቆ የተከተፈዉን ጨጓራና አንጀት መጨመር ከ 2 ደቂቃ ማማሰል በሁዋላ ሌሎቹን የዱለት ነገሮች መጨመር አብረው ለብ ሲሉ እያማሰሉ ወዲያው አንድ የሾርባ ማንኪያ ሚጥሚጣ የደቀቀዉን ቃሪያና ለጋ ቅቤ ጣል አድርጎ ማዋሀድና ወዲያው ማዉጣት
ታዲያ በመጀመሪያ ለሴት ስይሆን ለወንድ ልጅ ማጉረስ ወንደ ላጠዎችና ሴተ ላጠዎች አስቡበት ትዳር መመስረትን በዚህች አለም ላይ ጥሩ ስምንና ራስን ተክቶ ማለፍ ነው ትርፉ ሌላ ምንም የለም!
Marta P.
.
የበግ አልጫ
.
2 ራስ ሽንኩርት የተከተፈ በዘይት ማቁላላት ከዚያም የተቆራረጠውን የበግ ስጋ ጨምሮ ካለ ውሀ ለስለስ ባለ እሳት ማቁላላት
- ቀጥለውም ትንሽ ውሀ ጠብ እያደረጉ ማማሰል ትንሽ ጠየም ማለት ሲጀምር ውሀ መጨመርና እሳቱን ትንሽ ከፍ ማድረግ
- መንተክተክ ሲጀምር የተፈጨ ዝንጅብልና ነጭ ሽንኩርት፣ ነጭ ቅመም፣ ትንሽ እርድ በላዩ ላይ ማድረግ አንድ የሾርባ ማንኪያ ቅቤ ጨምሮ ጨውን ማስተካከል
- ከመውጣቱ በፊት 2 ቃሪያ ሰንጠቅ አድርጎ ማውጣት :: ከዚያ ብኋላማ መረቁን ከተገኘ በእንጀራ ፈትፈት ነው ካለበለዚያም ያው በተገኘው ...
ማርታ
.
ህልበት
.
ስንቶቻችን እንሆን ህልበትን የምናውቀው? በጾም ግዜ የሚበላ ምግብ ነው።
ህልበት የሚሰራው ከባቄላ፣ ምስር እና የበቀለ አብሽ ዱቄት ነው። (ህልበት እና ስልጆ አንድ አይደሉም ይለያያሉ)
መጀመሪያ ዱቄቱ ሲዘጋጅ
3 ኬሎ ...የተከካ ባቂላ
እሩብ ከሎ በደምብ የተከካ ምስር
እሩብ ኬሎ የበቀለ አብሽ
እነዚህ ሲፈጩ የህልበት ዱቄት ይሆናሉ።
አሰራሩ
መጀመሪያ በንጹህ ድስት 2 ኩባያ ውሀ እንጥዳለን። ከዚያ ውሀው እስኪፈላልን ድረስ በንጹህ ሳህን 4 የጠረጴዛ ማንኪያ የህልበት ዱቄት በአንድ ኩባያ ቀዝቃዛ ውሀ እንበጠብጠዋለን። ...ከዚያ ውሀው ሲፈላ የበጠበጥነው ቀስ እያልን እየጨመርን ማማሰል ... ወፈር እስኪል ድረስ እናማስለዋለን። በደምብ ሲበስል ልክ እንደሽሮ ... አውርደን በሌላ እቃ ገልብጠን እናቀዘቅዘዋለን ...ከዛ ሰፋ ባለ ሳህን ላይ አድርጎ እስኪኮረፍ እና መልኩ እስኪቀየር (ነጭ ) እስኪሆን ድረስ በደምብ ይመታል። ይመታል ያኔ ለምግብነት ሲዘጋጅ በደምብ የደቀቀ ነጭ ሽንኩርት እና ቃርያ አድርገን እናዋህደዋለን
... ማርታ ...
.
ሽሮ
.
የምጣድ ሽሮ
* አንድ አነስ ያለ የፈረንጂ ሽንኩርት ወይም አንድ 4 ራስ ያበሻ ሽንኩርት ደቀቅ ብሎ ይከተፋል::
* ሁለት የሚያቃጥል ቃሪያ ደቀቅ ብሎ ይከተፋል ::
* አንድ ጭላፋ ምጥን ሽሮ
* ግማሽ ስኒ የቡና (ፍንጃል ) ዘይት አሰራሩ ሁሉንም በጎድጓዳ ሰሀን መቀላቀል እናም መበጥበጥ የንጀራ ምጣድ ማጋል ወይም እንጀራ ተጋግሮ ሲያበቃ በጋለው ላይ ያንን ማፍሰስ ቀጭን ስለሚሆን ራሱ እንደቂጣ ይዘረጋል
*መክደንና ከ5 ደቂቃ ብሁዋላ አክንባሎዉን (ሞግዱን )መክፈት
*ከዚያም በማማሰያ ወይም በማንኪያ ምጣዱ እንዳይላጥ አድርጎ ቀስ አድርጎ ባንድ ላይ ሰብስቦ ማገናበጥ ... ደረቅ ሲል ማዉጣት
* ጨው መቸም መመጠን የናንተ ፋንተ ነው እዚህ ላይ የሚጻፍ መጠን አይኖርም .. ምጥን ካልሆነ ሽሮው በርበሬ ትንሽ ጣል አድርጎ ማገናኘት መጀመሪያ ላይ አቤት ሲጣፍጥ!!
.
ቦዘና ሽሮ
* ሽንኩርት አንድ ራስ ሸርከትከት አድርጎ መክተፍ
* ከዚያም ሽንኩርቱን በዘይት ማቁላላት
* ዉሀ መጨመር በዛ አድርጎ እንደሰው ብዛት ይወሰናል ዉሀው
* ዉሀዉ ሲፈላ ሽሮዉን ነስንሶ ማማሰል ቀጠን ማለት አለበት
* በሰል ሲል ቃሪያ ሁለት ወይም ሶስት ሰንጠቅ አድሮ ጣል ማድረግና ማዉጣት።
ሽሮን እንደምታዉቁት በትኩሱ ነው :: እንጀራ ላይ አድርጎ ላፍ ላፍ ነዋ!!
ሽሮ ሳት ካልመታው ጥሩ አይደለም አንደኛ ሆድ ይነፋል ሁለተኛ ሊጥ ሊጥ ይላል ጣዕም አይኖረውም::
.
ሽሮ በቋንጣ
ያዉ አንድ ራስ ሽንኩርት መክተፍና ቋንጣዉን ቆረጥ ቆረጥ አድርጎ ሽንኩርቱን ዘይት ጨምሮ ማቁላላት .. ከዚያም ዉሀ ጨምሮ እስኪፈላ መቆየት .. ዉሀዉ ከፈላ በሁዋላ ሽሮዉን መነስነስ:: ቋንጣ ካለበት ቀይ ሽሮ ወይም ምጥን ሽሮ ቢሆን ጥሩ ነው። ሩብ ራስ ነጭ ሽንኩርትም ሊወጣ አካባቢ አስገብቶ ማብሰልና ትንሽ ቂቤ ጣል አድርጎ በትኩሱ አዉጥቶ መብላት ነው።
ማስታወሻ መልካም የሽሮ ቀን (Marta P.)
.
የቋንጣ ፍርፍር ለ3 ሰው
.
ልክ እንደማንኛውም ወጥ አሰራር በመጀምሪያ 2ራስ ቀይ ሽንኩርት ከትፈን (መድቀቅ የለበትም) ከ1ራስ ነጭ ሽንኩርት ጋር ለ3 ደቂቃ ማብሰል (ቲማቲም ከትፈን መጨምር እንቻላለን የበርበሬውን ማቃጠል ሊቀንስ ስለምችል። የቆርቆሮ ቲማቲም ከሆነ ሁለት ማንኪያ ይበቃል) ከዚያ አንድ የቡና ሲኒ የሚሆን ዘይት ጨምረን እንደገና ማብሰል። ከዚያ 2 የሾርባ ማንኪ በርበሬ (በጣም እንዲያቃጥል ካልፈለግን 1) አድርገን አሁንም በዘይቱ ከጠበስነው በሁዋላ ቋንጣውን በሌላ ምጣድ ወይንም ዝርግ መጥበሻ በደረቁ ከቆላነው በኋላ ደረቅ ሲል ቁሌቱ ዉስጥ መጨመርና ሁሉንም አብሮ አዋህዶ ለ5 ደቂቃ ማብሰል ከዚያ 1 የሾርባ ማንኪያ ቂቤ መጨመር። ቁሌቱ በደንብ ከበሰለ እና ከተዋሀደ በሁዋላ ሁለት ብርጭቆ ዉሀ በግምት አድርገን ጨው ግማሽ ማንኪያ (በምንፈልገው መጠን) አድርገን ከድኖ ማብሰል። ዉሀው ሲፈላ እና በደንብ ለ5 ደቂቃ ከተንተከተከ በሁዋላ በአገር ቤት ምጣድ 1 እንጀራ መሰባበር/መበጣጠስ እና እሳቱን በጣም እስከመጨረሻ ቀንሰን ወይም አውጥተን እንጀራውን ጨምሮ ቀስ ብሎ ቢቻል በሹካ ማገላበጥ (ካማሰልነው ሊቦካ ስለሚችል)
ከዚያ እንጀራው ከመረቁ ጋር ከተዋሀደ በዳቦ እንክት።
ድርቆሽ ከሆነ የውሀውን መጠን ጨመር ማረግ አለብን።
ማርታ ፔድሪኒ
.
የዶሮ አገነጣጠል
.
አገነጣጠሉን በአይን ካላያችሁት ለመማር ይከብዳል። ቢሆንም ያው እዚሁ ሀገር ከስፐር መርካቶ መውሰድ እንጂ ማረድ አይቻል አይደል? (ታዲያ ትንንሾቹን መግዛት ይሻላል ምክንያቱም ስጋው ወጡ ውስጥ ሲበስል ከመፈራረስ ይድናል) ትናንሾቹን ስላችሁ ደግሞ ተሳስታችሁ ወፎቻቸውን እንዳትበሉ።
1 - ክንፏ መሀል ላይ ያለውን ቆዳ እስከ ታች መቁረጥና እንዳለ ቆርጦ ማውጣት:: ከግማሽ አጥንት እስከ ትከሻዋ ያለው ይቀራል ማለት ነው ::
2 - ከአንገቷ እስከ ታች ድረስ ቆዳዋን ብቻ መሰንጠቅና ልክ ሸሚዝ እንደሚወልቅ ግፍፍ አድርጎ ማውጣት::
3 - እግርና እግሯን ወደኃላ መስበርና በቢለዋ ከላይ ከወገቧ ጀምሮ እስከ ታች መለየት ከሰውነቷ ላይ::
4 - ያንን የቀረውን ክንፍ ከትከሻ ላይ ቆርጣችሁ ከነመላላጫው ገፋችሁ ታወጡታላችሁ::
5 - በጀርባዋ በኩል ትንሽ አጥንት ከትከቻዋ የመጣና በስጋ የተሸፈነ ታገኛላችሁ ወደ ላይ በቢለዋ ታላቅቁትና በእጃችሁ ከአንገቷና ፈረሰኛውን ይዛችሁ ታላቅቁታላችሁ::
6 - አንገት፣ ጀርባ፣ የጎን አጥንት፣ ከታች በኩል ያለው የጀርባ አጥንት ይቀራል። ሁሉንም መለያየትና ጀርባውንና የጎን አጥንቱ ውስጥ ያለውን የሆድ እቃ መጣል ልቧን ማስቀረት ይቻላል (አገር ቤት ጉበቱ እሳት ውስጥ ተጠብሶ ይበላል)
7 - ፈረሰኛው ጎንና ጎኑ ላይ ስስ ከአጥንት ጋር የተያያዘውን ነገር አለ ቆርጦ ማውጣት::
8 - አንገቱን ሁለት ወይም ሦስት ቦታ መቁረጥና ወፈር ባለ ስንጥር ከመሀሉ ጨምሮ ውስጡ ያለውን ነጭ ነገር ማውጣት::
9 - እግሩ መለያያ አጥንቱ ላይ መቁረጥና (አጭሬና ረጅሜ ብሎ መለየት )
10 - ከኃላ ሆኖ ወደታች በኩል ያለው አጥንት ለሁለት ይለያል እና የመሀል ፓርቱ ይጣላል::
የረሳሁት ካለ ሙሉበት::
ማርታ
.

ቅቤ ለማንጠር
.
አራት መአዘኖቹን የዳቦ ቅቤዎች (ጨው የሌለበትን) ከሱፐርመርካቶ መግዛት። ከዛ ቅቤውን በተገኘው ቅመም (ጥቁር አዝሙድ, ኮሰረት, ኮረሪማ ... ይበቃል) መለወስና ከሁለት እስከ ሶስት ቀን ማስቀመጥ። በለስላሳ እሳት ማንጠር እና ማጥለል። የቅቤ ቅመም ከሀገር ቤት የምታስመጡ ከሆነ ግን ተቀላቅሎ የተፈጨው ጥሩ ነው። ለማንኛውም የተፈጨው ከሌላችሁ ኮረሪማውን (የተፈለፈለ) መቼም የቡናም ብረት ምጣድ ወይም ማንከሽከሻ አታጡም በሱ ትንሽ እሳት ሳታበዙ አመስ አመስ ካደረጋችሁ በኃላ አውጡትና በቡና መፍጫ በደንብ ጠራርጋችሁ ትፈጩታላችሁ። ከዛ አራት መአዘኑን የዳቦ ቅቤ ጋር ቀላቅለሽ ያው በለስላሳ እሳት ማንጠር ነው።
እዚህ የቂቤ ቅመም የት እንደሚገኝ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ። ይህንን ማንም የሚያውቀው ሰው እንደሌለ አውቃለሁ። ህንዶች ቤት ታገኛላችሁ። ኮረሪማ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ... ወዘተ ... ከፈለጋችሁ። ኮሰረት ግን የሚገኝ አየመስለኝም።
ማርታ ፔድሪኒ


3 Comments:

At 10:25, Anonymous ማንዴላ said...

ወንደላጤ ነኝ ::ያገሬ ምግብ በጣም እወዳለሁ በተለይ ዶሮ ወጥ :: በየቀኑ የአበሻ ምግብ ቤት እየሄድኩ ለመብላት ታድያ ይሄ የኤውሮ ገንዘብ አቅም የለኝም :: እችለው እንደሁ ብየ ስጋ ሽንኩርት ቃሪያ ቲማቲምና ዘይት ከሱቅ ሸምቼ ወጥ ልስራ ብል ውጤቱ ወጥ ሳይሆን የመረሬ አፈር ጭቃ መስሎ ወጣ !!ወይ ጣጣ !! እባካችሁ እርዱኝ !! በተለይ ሴቶቻችን

የተቸገረው ወንደላጤ ወንድማችሁ
ማንዴላ

 
At 19:58, Anonymous BM said...

ቦዘና ሽሮ ስራ (ጣል ጣል ያለበት ሽሮ)
የሚያስፈልጉት ...
3 ራስ ሽንኩርት
ግማሽ ኪሎ ስጋ
ትንሽ ዘይት (1 የቡና ስኒ መለኪያ)
2 የሾርባ ማንኪያ (እንዳስፈላጊነቱ ይጨምራል/ይቀንሳል)
3 የሾርባ ማንኪያ በርበሬ (ሽሮው ምጥን ከሆነ በርበሬው አያስፈልግም)
ሽሮ (ነጭ ሽሮ ወይም ምጥን)
ለጋ ቅቤ
5 መካከለኛ ብርጭቆ ውሀ
መካከለኛ በሆነ ድስት ሽንኩርቱን ከትፎ መጣድ ..
ሽንኩርቱ የራሱን ውሀ ሲመጥ ትንሽ ወሀ ጭምሮ ማብሰል ...
ውሀውን ሲመጥ ጎረድ ጎረድ ተደርጎ የተፈተፈውን ስጋ መጨመር ...
ስጋው የራሱን ውሀ እስኪመጠው ድረስ አልፎ አልፎ እያማሰሉ መብሰል ...
ከዛም ዘይቱን ጨምሮ ስጋውን መጥበስ .....(10 ደቂቃ)
በርበሬ ጨምሮ ውሀ ጠብ እያደረጉ ማቁላላት (10 ደቂቃ ) (ሽሮው ምጥን ከሆነ ግን ይህ ስቴፕ አያስፈልግም )
ውሀውንና ጨውን ጭምሮ ሲፈላ ሽሮውን ጨምሮ ማማሰል ... (ሽሮው እንዳይጓጉል ሽሮውን እንደጨመሩ ቶሎ ቶሎ ማማሰል ያስፈልጋል)
ከዛም እንዳይገነፍል እየተጠነቀቁ ድስቱን በመክደን ሽሮውን ማብሰል ነው (መብሰሉ የሚታወቀው አረፋውን ጨርሶ መንደክደክ ሲጀምር ነው)
ሊበስል ሲል ቅቤውን መጨመር ...
ከዛማ በቃ ....በእንጀራ እያደረጉ መብላት ነው :: በዳቦም መብላት ይቻላል ግን ዳቦ በወጥ ! "በግዜር"
Bereket M (RO)

 
At 14:38, Anonymous ወንደላጤው (ታሪኩ እባላለሁ) said...

ደግሞ ለሞያ ማን ብሎኝ ላስተምራችሁ ...
በመጀመርያ ውሀ በብረት ድስት ሞልተህ ትጥዳለህ ...
ከዛ እሳቱን ትለኩሳለህ ...
ውሀው ሲፈላ ፓስታ ትጨምራለህ ...
ከ 15 ድቂቃ ቦሀላ ፓስታውን ታወጣና ታጠላለህ ...
በቃ ፓስታ ሰራክ ማለት ነው .....[መቼስ ሰው ባለው ነው የሚሸናው .....እኔም ያለኝን አስተምርያለሁ ...

 

Posta un commento

Links to this post:

Crea un link

<< Home

   Copyright © 2009 ethiopia

Notizie ed Eventi (gibe3.com.et/EEPCo.html)Reaction to Issues Raised by ‘South China Morning Post’ Concerning the Gibe III HEP

the sole reason that Ethiopia has shifted to China is that the international financiers have taken much more time in approving the fund ...

Read More ...

EEPCo signs accord with Chinese Company for Gibe III Project

The Ethiopian Electric Power Corporation (EEPCo) and Dongfang Electric Corporation (DEC), Chinese state-owned company, signed a company, signed a contractual agreement amounting to about USD 500 million ...

Read More ...

Distorted Facts Vs the Reality The Actual Picture of Gibe III Hydroelectric Project

Needless to say, many deliberate and irresponsible reports are being fabricated regarding the Gibe III Hydroelectric Project (HEP).   

Read More ...

Gibe III HEP Launches Satellite Office at Jinka Town

The Gibe III Hydroelectric Project (HEP) Office opened an Environmental and Social Impact Management and Mitigation Team branch office at Jinka town on Feb 2010.    

Read More ...

Office performs Public Consultations, Disclosure with Project-Affected Communities

the Gibe III Hydroelectric Project Office carried out a wide range public Consultations & disclosures and complimentary discussions with the upstream communities of the Project    

Read More ...

Consultants Reaffirm Gibe III HEP Viable in economic, financial, technical terms

the joint venture international consultants reaffirmed that the Gibe III Hydroelectric Project is considerably viable    

Read More ...

Gibe III Hydroelectric Project said Best Option in Power Sector Development

The African Development Bank (AfDB) and the Work Bank (WB) experts acknowledged Gibe III Hydroelectric Project is the best option in the power sector developments    

Read More ...

EEPCo, TBEA sign Contract for Gibe III-Wolaita substation Transmission Line Project

The EEPCo and TBEA, a Chinese company, singed a contractual agreement on July 24, 2009, amounting to Birr 380,883,690.99 (USD 34,007,472.41) for the installation of power transmision line from Gibe III Main station to the new Wolaita substation.    

Read More ...

Office Establishes Environmental Advisory Panel

The Gibe III Hydroelectric Project Office established Environmental Advisory Panel (EAP) in a bid to consult on the environmental issues during the implementation project.

Read More ...

EEPCo looks to win West African contract

Capita, (26 July 2009, Addis Ababa)-The Ethiopian Electric Power Corporation (EEPCo) recently participated in an international tender to manage the operation of the recently completed Bumbuna Hydroelectric Project (BHP) in Sierra Leone, which was constructed by Italian-based firm. Salini.

Read More ...

Kenya, Ethiopia to benefit from dam project

Kenya and Ethiopia are constructing a-multibillion hydroelectric project to benefit the two neigbouring countries, according to Kenyan officials.

Read More ... 


Newsfeeds (cyberzena.com)/

ቀን መቁጠሪያ

 
ቀን መቁጠሪያ