martedì

የፋሺስት ኢጣሊያ ግፍ አሁንም ያነጋግራል


19 07 2008
ከዛሬ 73 ዓመት በፊት የፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊት በኢትዮጵያኖች ላይ አሰቃቂ ግፍና ጭፍጨፋ መፈፀሙ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው። በወቅቱ የፋሺስት ሠራዊት በተጠቀመው የመርዝ ጋዝ ያደረሰው እልቂት ከፍተኛ ነበር። በዚያን ጊዜ የፋሺስት ሠራዊቱ የጦር አዛዥ ከነበሩት መካከል በጨካኝነቱ ለሚታወቀው ጄነራል አልፒኒ መታሰቢያ የተተከለው ሐውልት እስካሁን ድረስ እየተከበረ መገኘቱ አዲስ ውዝግብን ሊቀሰቅስ ችሏል።
በ1936 እ.ኤ.አ. በአልፒኒ ስም የቆመው ሐውልት በራሱ በአልፒኒ ምስል የተቀረፀ ነው። ይህ በሰሜን ኢጣሊያ የሚገኘው የአልፒኒ መታሰቢያ ሐውልትና በስሙ የሚጠራው መንገድም ”አልፒኒ ኖርዘን ኢታሊያ” የሚባል ነው። በኢትዮጵያውያኖች ላይ ጭፍጨፋን የመራ ግለሰብን እስካሁን ድረስ እንደ ጀግና ተቆጥሮ መከበሩ ብዙዎችን ያስደነቀና ያስደነገጠ ጉዳይ ሊሆን ችሏል። ሰሞኑን ወደ ሰሜን ኢጣሊያ አቅንተው የነበሩት በኢጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ግሩም አባይ በተመለከቱት ነገር እንደተገረሙ ተናግረዋል።
የአልፒኒን ሐውልት ያሠራው የፋሺስት ኢጣሊያ መሪ የነበረው ቤኒቶ ሙሶሎኒ ነበር። አልፒኒ በተለይ በጦርነቱ ወቅት የሚታወቅበት ፋሺስቱ ሠራዊት ዘረፋ እንዲያካሂድ፣ እንዲገድልና አስገድዶ እንዲደፍር ግልፅ ትዕዛዝ በመስጠቱ ነበር። እ.ኤ.አ. በ1936 የተተከለው የአልፒኒ መታሠቢያ ሐውልት፣ በዚያን ጊዜ ቢሆን ተቃዋሚ ያላጣ እና ይኸው ተቃውሞ ለበርካታ ዓመታትም ሳይቋረጥ ቆይቷል። በሐውልቱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት የተሰነዘረው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሳይጠናቀቅ በፊት ሲሆን፣ ከዚያም በተከታታይ በ1956፣ በ1959፣ በ1966 እና በ1979 ጥቃት ተሰንዝሮበት በከፊል ሊጎዳ ችሏል። በአሁኑ ወቅት በአልፒኒ ሐውልት ጉዳይ ላይ ተቃወሞውን እያቀረበ የሚገኘው 'sudtiroler schutzenbund' የተባለ የባህል ተቋም ነው። ይኸው ተቋም አምባሣደር ግሩም ዓባይን ወደ ሰሜን ኢጣሊያ “ሳውዝ ትሮይል” ጋብዞ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ችሏል። ለአምባሳደር ግሩም ዓባይ የጦር ወንጀለኛውን የአልፒኒ ሐውልትን ወስዶም አሳይቷል። በኢጣሊያ በርካታ ከተሞች የተተከሉ የፋሺስት ኢጣሊያ የጦር መሪዎች መታሰቢያ ሐውልቶችና በስማቸው የተሰየሙ መንገዶች ይገኛሉ። ከአልፒኒ ባልተናነሰ የጦር ወንጀል የፈፀሙ ቪያ-አምባ-አላጊ እና ቪያ ፓተር ጂሊያኒ የተባሉ የፋሺስት የጦር መሪዎች ስም በጣሊያን መንገዶች ይጠራሉ። አምባሳደሩ ከባህል ተቋሙ ጋር ሁለት ሰዓት የፈጀ ወይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ምንም ምንኳ የኢትዮጵያ ህዝብ ጣልያኖችን ይቅርታ ያደረገላቸው ቢሆንም በሰሜን ኢጣሊያ የጦር ወንጀለኛውን የአልፒኒ ሐውልትን በተመለከተ “ሐውልቱ በኢትዮጵያውያኖች ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በድጋሚ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። የባህል ተቋሙ፣ በኢጣሊያ በጦር ወንጀለኝነት የሚታወቁ የጦር አዛዦች ስም የቆሙ ሐውልቶችና በስማቸው የሚጠሩ መንገዶች ዝርዝር ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል። የባህል ተቋሙ አባል የሆኑት ፖል ባቸር እንደተናገሩት፣ ከጣልያን መንግሥት የሚጠበቀው ነገር ጣልያንን ካዋረዳት የፋሺስቶች ተግባር ምን ያህል ርቀት እንዳለው እና በመላው ጣሊያን የሚገኙ የፋሺስት ሠራዊት መታሰቢያዎችን ማስወገድ ነው ብለዋል።
ሞሶሎኒ በኢትዮጵያ ላይ ያወጀው ጦርነት የተጀመረው እ.ኤ.አ. ጥቅምት 3 ቀን 1935 ዓ.ም ነበር። በጊዜው የኢትዮጵያ ንጉሥ ጉዳዩን በሊግ ኦፍ ኔሽን አሰምተው ነበር። የፋሺስት ጦር ኢትዮጵያ ላይ የተጠቀመውን የመርዝ ጋዝ ከጀርመን ናዚ ጋር ለሚያካሂደው ጦርነት መሞከሪያ ለማድረግም ነበር። የፋሺስት ጦር ድርጊትን አስመልክቶ ብሪታኒያዊው ሐኪም ጆን ሜሊይ እንደገለፁት፣ “ይህ ጦርነት አይደለም፤ በጭካኔ ደም ማፍሰስ ብቻም አይደለም፣ ሊባል የሚችለው ነገር፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መከላከያ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ በመርዝ ጋር መጨረስ ነው” ብለዋል። የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ተወካይ የነበረው ማርሴል ጂኖድ በጊዜውን የዓይን እማኝነቱን የገለፀው “በየቦታው በመሬት ላይ የተጋደሙ ሬሳዎች ነበሩ፣ የሰው እግሮችና ሳምባዎች ሳይቀሩ በመሬት ላይ ይታያሉ። ያየሁት ነገር አሰቃቂ ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ብቻ አይደለም” ሲል ተናግሯል። ጦርነቱ በኋላ የፋሺስት አጣሊያ መንግሥት ለፈፀመው የዘር ፍጅት በዓለም አቀፉ የጦር ፍርድ ቤት ለመክሰስ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸናፊ በመሆኑ ሊቀር ችሏል። የጣሊያን መንግሥት ግን በካሳ መልክ ለኢትዮጵያ የ25 ሚለዮን ዶላር ቢሰጥም አሁንም ድረስ በይፋ ይቅርታ አልጠየቀም።
ኢትዮጲያ ዛሬ


Nessun commento: