martedì

በጣሊያን የሮማው ኦሎምፒክ ጊዜ
(ዘመን የማይሽረው ሕያው ታሪክ)


ሮም የኢትዮጵያ ደመኛ አገር የነበረችዋ የጣሊያን ዋና ከተማ ናት። በሮም፣ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ፣ በአዲስ አበባ የጣሊያን ባንዲራ በመተከሉና ኢትዮጵያ በጣሊያን እጅ በመውደቋ የድንፋታ ንግግር ለአገሬዉ ሕዝብ ያደረገበት ከተማ ናት። ከሃያ ስድስት አመታት በኋላ፣ እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ 1952 ዓ.ም ባንዲራችን መሬት ወድቆ ጮቤ በተረገጠባት ከተማ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ከፍ ብሎ ተዉለበለበ። በዚያን ቀን ታሪክ ተሰራ።


ጥንታዊት ሮማ ዳግም የታደሰች መስላለች። መንገዶቹ ሁሉ የፊት ማያ መስተዋት መስለዋል። እንዴት አደርሽ ጣሊያን? እንዴት አደርሽ ሮማ? የሚል የጣሊያን ሬዲዬ ድምፅ ይስተጋባል። ሁሉም የክቱን፤ እንዲሁም ደግሞ የማእረግ ልብሱን በየበኩሉ ለብሶ የኦሊምፒክ ውድድር የመዝጊያውን ቀን ሥነ-ሥርዓት ለማየትና ለመሰናበት ከየቦታው ወደ ሮማ ስታዲየም ይጐርፋል። ይተማልም።

ጊዜው እ.ኤ.አ. 1960 ነው። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ ላይ በብስክሌትና በሩጫ ውድድር የተካፈለች ሲሆን፤ የብስክሌት ተወዳዳሪው በውድድሩ ላይ ተጠልፎ ከወደቀበት ተነስቶ 7ኛ ሊወጣ ቻለ።

ገረመው ደንቦባ።
የመጨረሻውን እና ተናፋቂውን ማራቶን ለመጀመር «በስመ-አብ ወወልድ« ብሎ አማትቦ እስኪጨርስ ድረስ እንኳ ፋታ አላገኘም። የውድድሩን መጀመር የሚያበስረው የሽጉጥ ድምፅ አስደነገጠው። እንደ ሽጉጧ ጥይት ተተኩሰው ያፈተለኩትን ከተለያዩ ክፍለ- ዓለማት ከተውጣጡ 79 ወጣት ተወዳዳሪዎች ጋር ተከትሎ ተነሣ። በሕልሙ ይሁን በእውኑ በውል አልታወቀውም። ግን መሮጡን አላቆመም፤ ይሮጣል፤ ይቀድማል፤ ወደፊት ይገሰግሣል... ይሁን እንጂ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነበር ውድድሩ ላይ መሆኑን የተገነዘበው። ያውም ማራቶን! 42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር ርቀት! ከተወዳዳሪዎቹ መካካል ለየት ያለ ቀለም ያለው አንድ አትሌት ይታያል። ታዲያ ማንም ስለ አንድ አፍሪቃዊ ብቸኛ ጥቁር አትሌት ቦታ መስጠት ቀርቶ በንቀት መልክ ነበር የሚገላምጡትና የሚሣለቁበት። በውድድሩ መንፈስ ውስጥ ብቻ የነበረው ቆፍጣናው አፍሪቃዊ የIትዮጵያ ልጅ ከፊት መሪ ተወዳዳሪዎቹ ጋር ፍልሚያ ተያይዟል።

ውድድሩን በመቀባበል በየኪሎ ሜትሩ ፍጥነታቸውን በመጨመር አያንዳንዱ ተወዳዳሪ ለሐገሩ ክብር የጭንቀት ውድድር ውስጥ ይገኛል። ብርቅዬውና ውዱ የኢትዮጵያ ልጅዓበበ ቢቂላ ከእነዚህ ተወዳዳሪዎች አንዱ ነው። ውድድሩ ከተጀመረ 20 ደቂቃ Aልፎታል። አበበ በመሪነት ካሉት መካካል አንዱ ቢሆንም ከተወዳዳሪዎቹ ጋር አብሮ መጓዝ ግን ፈፅሞ አልተዋጠለትም። ተፎካካሪዎቹ ሣያስቡት የፊት መሪነቱን ቦታ ይዞ ፍጥነቱን በመጨመር ውድድሩን ቀጠለ። ማንም ሯጭ በአጠገቡ የለም። ለዓለም ሕዝብና ለመላው የጣሊያን ነዋሪ የሚተላለፈው የዜና ማሰራጫ ለአንድ አፍታ ፀጥ Aለ። ውድድሩን የሚያስተላልፈው ጣሊያናዊ ጋዜጠኛም አይኑ ፈጧል። ይንቆራጠጣልም። የደነገጠም የተገረመም ይመስላል። ድንገት ከሕልሙ አንደባነነ ሰው ድምፁን ከፍ በማድረግ መጮህ ጀመረ። «ምን ዓይነት ጉድ ነው! እኔ አላምንም! ይገርማችኋል! ማ ማ ሚ ያ! ይደንቃል!» ይል ጀመር። ንግግሩን በመቀጠል «አንድ ጥቁር አፍሪቃዊ በማይታመን ሁናቴ ውድድሩን ብቻውን፤ የመሪነት ቦታውን እስካሁን በሞኖፖል ተቆጣጥሮታል። ጥቁር እፍሪቃዊ ነው።» ደጋግሞም የጥቁርነቱን ምልክት ይናገራል፤ ይጮሃል፤ ይለፈልፋልም። Iትዮጵያዊ መሆኑን ግን በትክክል ያውቃል። አንዳይናገረው አንደበቱን የቆለፈው ታሪክ ግን አለ። Iትዮጵያ ጣሊያን ባዘጋጀው ኦሊምፒክ ማሸነፍ ማለት ጣሊያን ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ እንደተሸነፈች ነበር ለጋዜጠኛው የታየው። ሣልሣዊ ውርደት!! ጋዜጠኛው አሁንም የሬዲዬ መልእክቱን ማስተላለፉን አላቆመም። «...ማ ማ ሚ ያ! ፍጥነቱን ከልክ በላይ ጨምሯል፤ የድካም ምልክት አይታይበትም፤ ይጨርስ አይጨርስ ግን በትክክል አላውቅም፤ የሚገርማችሁ ነገር ቢኖር አግዜር አንደፈጠረው ባዶ አግሩን ነው፤ ኢትዮጵያዊ ነው። አቢሲኒያዊ ነው። ይጨርሣል ብዬ አልገምትም ...» ብሎ ያሟርታል። ውድድሩን በጥሞና በመከታተል ላይ የነበሩትና የአበበም አሰልጣኝ አንዲሁም የቡድኑ መሪ ሆነው የሄዱት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ውስጣቸው ተረብሿል። አንዴ ይቀመጣሉ፤ ሌላ ጊዜ ይነሣሉ... በተመስጥኦ ውጤቱን ይከታተላሉ። በዚህ መካከል አንድ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ በለሰለሰ አንደበትና ሥነ-ሥርዓት ጐንበስ በማለት «አቶ ይድነቃቸው ባልሣሣት እርስዎ ነዎት?« በማለት ሲጠይቃቸው «አዎ ምን ነበር?» በማለት መለሱለት። ጋዜጠኛውም ቀጠል አድርጐ «የእርስዎ ተወዳዳሪ ውድድሩን በከፍተኛ ርቀት በመምራት ላይ ነው። ውጤቱ ምን ይመስለዎታል?» በማለት ሲጠይቃቸው፤ «ለጥያቄህ አመሰግንሃለሁ። ውጤቱን በኋላ አብረን አናየዋለን።» ነበር ያሉት በትህትና። የውድድሩን ሂደት በጥሞና Eእየተከታተሉ የሚዘግቡት የተለያዩ አገር ጋዜጠኞችም ቢሆኑ ከጣሊያናዊው ጋዜጠኛ ብዙም ባይለዩም በንግግራቸው፤ በአገላለጣቸውና በአቀራረባቸው ሁሉም የአበበን ሥእላዊ ድርሰት በየተራ የሚያነቡ ይመስላሉ። የአቤን እጅ አወዛወዝ፤ የእግር አጣጣሉን፤ ቁመናውን፤ አፍሪቃዊነቱን ጥቁርነቱን በመደጋገም ለመግለፅ ይሞክሩ እንጂ የአበበን ውስጣዊ መንፈስና ሞራለ-ጠንካራነት ብሎም አይበገሬነት ግን ከርሱ በስተቀር ማንም የተረዳው ሰው አልነበረም። ውድድሩን በከፍተኛ ፍጥነትና በሙሉ ኃይል እንዲሁም በአስተማማኝ ርቀት የሚመራው አበበ፤ ሮማ ስታዲዮም ሲደርስ ተመልካቹ ሕዝብ ከመቀመጫው ብድግ በማለት ጭብጨባውን አቀለጠለት። ጀግናው ኢትዮጵያዊ አዲስ የኦሊምፒክ ክብረ ወሰን በባዶ እግሩ በመስበር አሸነፈ። ድልን ተቀዳጀ። ድሉ ለኢትዮጵያ ብቻም ሣይሆን ለአፍሪቃም ጭምር ሆነ። በነገራችን ላይ አበበ ውድድሩን እንደቀላል ነበር የጨረሰው። በውጤቱም ቀደም ሲል በሩሲያዊው ሰርጌይ ፖፖቭ በ2፡30፡00 የተያዘውን የሰዓት ሪኮርድ በ2፡16፡02 አሻሻለው። በዚህ በሮሙ ውድድር የተሰለፈው አበበ ዋቅጅራ ደግሞ እግሩ ፈንድቶ በሰርጌይ ፖፖቭ ለጥቂት ተቀድሞ 7ኛ ወጣ። ከርሱ በኋላ ተከታትለው በመግባት ላይ ያሉትም ተራ በተራ ፍንግል እንደያዛት ጫጩት ሜዳ ላይ ተዘርረዋል። በቃሬዛም በድጋፍም የተወሰዱ ነበሩ። አበበ ግን ለውድድሩ እንደሚዘጋጅ ተወዳዳሪ ጂምናስቲክ ይሠራል። አካሉንም ያዝናናል። አበበ ልዩ ተስጥዎ የነበረው ሞራለ-ጠንካራ አትሌት ነበር። ኢትዮጵያ ከሮማ ኦሊምፒክ በፊት በ1956 በሜልቦርን ኦሊምፒክ ተሣትፋ ነበር። ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት በ100 ሜትር አቶ ንጉሤ ሮባ፤ እንዲሁም በማራቶን ባሻ ተብለው የሚጠሩት ዛሬ በሕይወት ያሉና የፌዴሬሽኑ ዘበኛ ነበሩ። በውጤቱም ባሻ ውድድሩን ጨርሰዋል። አቶ ንጉሤም አፈሩን ያቅልልላችውና ውድድሩን ፈፅመዋል።

የዓለም የማራቶን ውድድር ስም ከተነሣ ከሮማ ኦሊምፒክ በፊት በተደረጉት ውድድሮች በርካታ ተወዳዳሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ብዙዎቹ አቋርጠዋል። በዚያን ዘመን ያሸነፉትም ቢሆኑ ከ3 ሰዓት በላይ ነበር የፈጀባቸው። አበበ ግን በማይታመን ሁናቴ ከላይ በተገለጠው መሠረት አዲስ ሬኮርድ ነው ያስመዘገበው።

አበበ ከሮማ ኦሎምፒክ ሜዳ የአበባ ጉንጉንና የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያውን በአንገቱ አስገብቶ ወደ እናት ሐገሩ በደስታ ተመለሰ። የሐገሩ ሕዝብም በጭብጨባ፤ በደስታ፤ በእልልታና በጭፈራ ተቀበለው። በተለይም ደግሞ የክፍሉ የሥራ ባልደረቦች የሆኑት የክብር ዘበኛ ጦር አባላት በልዩ ልዩ ዘፈንና ወኔ በተሞላበት፤ በከፍተኛ የሐገር ቅር ስሜት ነበር የተቀበሉት። የዘመሩለትም።
አቤም ለሐገሩ ላስገኘው ክብር፤ ለራሱም ላስመዘገበው ክብረ-ወሰን ለሽልማት ግርማዊነታቸው ፊት ቀረበ። «ደጉ ንጉሣችንም» የምክትል አሥር አለቃነት የበታች ሹማምንቶች ማእረግ አከናነቡት። አቤት ደግነት ይሉታል ይህ ነው!

አበበ ቢቂላ በማራቶን ብቻም ሣይሆን በ5ሺህ፤ በ10ሺህ፤ በ21 ኪሎ ሜትር፤ በ12 ኪሎ ሜትር በሄደበት ሐገር ሁሉ ማሸነፍ ብቻም ሣይሆን ክብረ-ወሰንም ጭምር ነበር የሰበረው። አንድ መረሣት የሌለበት ጉዳይ ቢኖር አበበ በሮም ኦሊምፒክ ውድድር ካሸነፈ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃለ-ምልልስ ላይ የተናገረው ነው። ይኸውም፤ «... እኔ የዛሬ ኦሊምፒክ አሸናፊ ከዓለምም አንደኛ ነኝ። በሐገሬ ላይ ግን ሁለተኛ ነኝ» ነበር ያለው። እንዴትና ለምን? ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ሲመልስም «እኔን የሚበልጠኝ ጓደኛ አለኝ። ይበልጠኛል። በውድድሩ ላይ ሣይሣተፍ የቀረውም በሰውነቱ ላይ ዘጠኝ ቦታ ቡግንጅ ወጥቶበት ነው። ስሙም ዋሚ ቢራቱ ይባላል። ስለዚህ ነው ብቻዬን የመጣሁት» ብሏል። የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ስለ ዋሚ ቢራቱ ያላሉት የለም። ሞራለ-ጠንካራውና «እድለ ቢሱ» ዋሚ ለኦሊምፒክ አይመረጥ እንጂ ከአበበና ከማሞ ወልዴ ጋር ብዙ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተካፍሎ አሸንፏል። ከማሞና ከአበበ ጋርም ተከታትሎ ገብቷል። ዛሬ ዋሚ ቢራቱ በሕይወት የሚገኙ አዛውንትና የ5 ልጆች አባት ናቸው። እኚህ እውቅ አትሌት የሐገሪቱ ባለውለታ፤ በውድድር ዘመናቸው ፉክክር ሁሉ ለሐገሩ ክብር ማስገኘት ብቻ ስለነበር ምንም ዓይነት ቋሚ ንበረትና ሃብት አልነበራቸውም። ምሥጋና ይግባቸውና ዛሬ አቶ አላ-ሙዲ የተባሉ ባለቱጃር መኖሪያ ቤት አሠርተውላቸዋል። የአበበ፤ የማሞና የዋሚ ታሪኮች የተያያዙ በመሆኑ በመሃከሉ ጀባ አልኳችሁ እንጂ የአበበ የውድድር ወይም የስፖርት ታሪኩን ለማየት ስንሞክር በርካታ ጥሎ ያለፋቸው አሻራዎች እንዳሉ እንገነዘባለን። ዓለም-አቀፍ ውድድሮች ላይ በአሸናፊዎች መድረክ ላይ ባንዲራችንን ማውለብለብ የቻለው አቤ ዳግም ሌላ ህልም ነበረው። የሚጨበጥ ራእይ! በ1964 ላይ በጃፓን ሊደረግ ስለታሰበው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ ለመሣተፍ ልምምዱን

ጠዋትና ማታ ያካሔድ ነበር። በርካታ አበበዎችም አፍርቷል። ተከትለውታልም። በሮማ ኦሊምፒክ የልፋቱን ዋጋ ከሐገሩ መንግሥት በትክክል ባያገኝም የላቀ ክብር አግኝቷል። ሞራሉ የበለጠ ተጠናከረ። ክብሩንም ላለማስነካት ለቶኪዮው የኦሊምፒክ ውድድር ዝግጅቱን አጠናቀቀ። የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ እያለ ስንክሣር አያጣምና አበበም ታሞ ሆስፒታል ገባ። ሁናቴው የኢትዮጵያን ሕዝብ ቢረብሸውም ፈጣሪ ምሥጋና ይግባውና! አቤ የቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጐለት ወጣ። ወዲያውኑ ልምምዱን ጀመረ። ዝግጅቱንም አጠናቀቀ።
ይሁን እንጂ አበበ ያሸንፍ ይሆን? የሚለው ጥያቄ በበርካታ የስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ አከራክሮ ነበር። ከሆስፒታል በወጣ በ36ኛ ቀኑ የኦሊምፒክ ውድድር እጩ የሆነው አትሌታችን ውድድሩን ለመካፈል ወደ ጃፓን ዋና ከተማ ወደ ቶኪዮ በረረ። በነገራችን ላይ ይህች ውብ ከተማ የተቆረቆረችው በወንዝ ላይ ነው። አበበ ቶኪዮ ዓየር ማረፊያ ሲደርስ በከዘራ ተደግፎ ነበር። በዚህም ምክንያት ምእራባውያን ጋዜጠኞችና ተችዎች ኢትዮጵያ እንደማታሸንፍ በሰፊው አናፈሱ።
ከዚያ ቀደም ሲል የአበበን ሁናቴ በቅርብ ሆነው ይከታተሉ የነበሩ የዓለም ጋዜጠኞች እሱ ወደታከመበት ሆስፒታል ድረስ በመሄድ አጨናንቀውት ነበር። ውድድሩ እስኪደርስ ድረስ አበበ በተደጋጋሚ ቃለ-ምልልሶችን አድርጓል። ለቀረበለት ጥያቄ ሁሉ «አትጨነቁ፤ አሸንፋለሁ።» በማለት ነበር በሙሉ ልብ የሚመልስላቸው የነበረ። ጀግናው በቶኪዮ ለመሮጥ ያሰበው በጫማ ነው። ቶኪዮ በልዩ ልዩ ኅብረ-ቀለማትና በኦሊምፒክ ዓርማ አሸብርቃለች። የዓለም ሕዝብ በጉጉት ይጠብቀው የነበረው የኦሊምፒክ መዝጊያ ውድድርም እልህ Aስጨራሽና ወኔንና ጉልበትን የሚጠይቅ ነበር። ውድድሩ እንደተጀመረ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተወዳዳሪዎች አንዱን ከአንዱ በማይለይበት ሁናቴ ማፈትለክ ጀመሩ። ቢሆንም ከመጀመሪያው አንስቶ የመሪነቱን ቦታ አበበ ብቻውን ተያይዞታል። እናም ቃሉን አላጠፈም። ዳግም የኦሊምፒክ ክብረ-ወሰን በመስበር ድልን ተቀዳጀ። በሮም ከተማ የሰበረውን ሰዓት በ2፡12፡15 አሻሻለው። ዓለም ዳግመኛ ጉድ አለ!።
የማይደገመው ተደገመ፤ ተደግሞ የማያውቀው የማራቶን ድል ተደገመ። ለአቤም እንዲህ ሲባል ተቀኘለት፤
ሮምን በባዶዕግሩ፤ ቶኪዮን በጫማ
ድል አድርጓል አቤ በሁለቱም ከተማ
ይህ ድንቅ አትሌታችን ክብሩን ጠብቆ፤ ታሪኩን ደግሞ፤ የሐገሩንም ሰንደቅ-ዓላማ ከፍ ብላ እንድትውለበለብ አደረገ። በዓለም ዙሪያ የመነጋገሪያ ርእስ ሆነ። እስከዛሬም ድረስ ቢሆን የዓለም ሕዝብ አበበን ጠንቅቆ ያውቀዋል።...

«ከ 1960 ጀምሮ የኦሊምፒክ ማራቶን የአውሮጳውያንና የአሜሪካውያን የግል ሃብት መሆኑ አበቃ። ከኢትዮጵያ ደጋዎች የተወለደ አንድ ሰው የሮማን የንጋት ውጋጋን ስሜት ፈጠረ። ይህ ያልታወቀ ሰው አበበ ቢቂላ ይባላል። ባዶ እግሩን ይሮጣል። ከአራት ዓመት በኋላ፤ ግን ጫማ አጥልቆ በድጋሚ ቶኪዮ ያሸንፋል»

ለአፍሪቃ፤ ለጥቁር ሕዝቦችና ለኢትዮጵያም የስፖርት በር ከፋችና ምሣሌ በመሆን ጀግናው አበበ በቶኪዮ ዳግም ድል አድርጐ ወደ ሐገሩ ተመለሰ። ከፍተኛ የክብር አቀባባልም ተደረገለት። ለእናት ሐገሩ ባለውለታነቱና ለራሱም ላጐናፀፈው ክብር፤ የልፋቱን ዋጋ ከሐገሩ መንግሥት ለማግኘት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፊት ለሁለተኛ ጊዜ ቀርቦ የምክትል የመቶ አለቃነት ማእረግ ሹመት ተቀበለ። የማራቶን ጀግናነቱንም አረጋገጠ። ቀጣዩ ኦሊምፒክ ለአበበም ሆነ ለኢትዮጵያ በጣም አስፈለጊ ብቻም ሣይሆን ታሪካዊነቱም የላቀ እንደሚሆን ግንዛቤ እየያዘ መጣ። ቀጣዩ የኦሊምፒክ ውድድር ሊደረግ የታሰበው ከአራት ዓመታት በኋላ ሜክሲኮ ላይ ነው። ለአበበም ሆነ ለተከታዮቹ የሚታያቸው ራእይ ከውድድሩ በስተጀርባ ያለው ቁም ነገር ብቻ ነው። በተከታታይ ለሦስት ጊዜ ማሸነፍ ከቻሉ የማራቶን ንጉሥ የሚለው ክብር ማግኘት ነበር ለጥንካሬያቸው ተጨማሪ ግፊት። በነገራችን ላይ ለሦስት ጊዜ የኦሎምፒክ ማራቶንን በመከታተል ያሸነፈ እስከዛሬ የለም። ጀርመናዊው ሯጭ እንዲሁ እንደ አበበ ሁለት ኦሊምፒኮችን ብቻ ነበር በተከታታይ ያሸነፈው። እንደ ሕይወቴ ሩጫን እወዳለሁ። ሕይወቴም ሩጫ ናት (running is my life) ነበር ያለው። አበበ ብዙዎች አበበዎችን አፍርቷል። ብቻውን አይደለም። ማሞ ወልዴም ከኮሪያ ዘመቻ በድል ተመልሷል። ዋሚ ቢራቱ፤ ባሻ ፍቅሩ፤ በየነ አያኖም፤ የትነበርክ በለጠ፤ ሽብሩ ረጋሣ... እነዚህ ሁሉ ከአበበ የማይተናነሱ የዘመኑ ፈጣኖች ነበሩ። ቢሆንም የኢትዮጵያ ችግር «ምንጊዜም» አይጠፋምና በበጀት ምክንያት ሁሉም አይሄዱም። የምርጦች ምርጥ ይመረጣል። በ1968 የሜክሲኮ ኦሊምፒክ የምርጦች ምርጥ አበበና ማሞ በመሆን ተመረጡ። ጊዜው ሲደርስም ጉዞው ወደ ሜክሲኮ ሆነ፤ ከበዙ ሰዓት የዓየር በረራ በኋላ ሜክሲኮ ሲቲ ሲገቡ የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ጋዜጦች ርእሰ አንቀጽ ገፆችን አበበና ማሞ ሸፈኑት። ሁለቱም ምርጥ አትሌቶቻችን በአካልም በመንፈሰም ተዘጋጅተዋል። አበበ የኦሊምፒክ የማራቶን ንጉሥ ለመባል፤ ማሞም በበኩሉ የመጀመሪያ ውጤቱን ለማየት!። በሜክሲኮ ጥቂት ቀናት ቆይታቸውም ከአካባቢው ዓየር ጋር ለመተዋወቅ የልምምድ ፕሮግራምም ነበራቸው፤ በቀረው ትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ ልዩ ልዩ ታሪካዊና መዝናኛ ቦታዎችን በመጐብኘት አሣለፉ። አይደርስ አይቀር የውድድሩ ቀን ደረሰ። ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር በመሆን የማስነሻውን ጥይት ተኩስ ይጠባበቃሉ፤ ውድድሩ ከተጀመረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጀግኖቹን አበበንና ማሞን የሚፎካከራቸው ጠፋ፤ የዕለቱ ዓየር ጠባይም ፀሃያማና ተስማሚ ስለነበር ተራ በተራ የመሪነቱን ቦታ ይቀባበላሉ። የውድድሩን ሂደት የሚከታተለውና የሚያስተላልፈው የሜክሲኮ ሬዲዬም ያለምንም ማጋነን የሁለቱን Iትዮጵያውያን በተለይም ደግሞ የAበበን ታሪክ አስመልክቶ ነበር ልዩ ትኩረት የሰጠው። ማሞንም በሚመለከት ከአራት ቀናት በፊት በ10ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የመሆኑን ታሪክ በሰፊው ያትታል፤ ውድድሩን በየተራ ለብቻቸው ይቀባበሉ ስለነበር ማን ያሸንፍ ይሆን? የሚል ጥያቄ መነሣቱ አልቀረም። ይሁንና ሁለቱም አትሌቶቻችን ከባዱን ጐዳና ተያይዘውታል። የውድድሩን የመጀመሪያ 25 ኪሎ ሜትር አገባደውታል።

በመሀሉ ማሞ ባልገመተውና ባላሰበው ሰዓት በጆሮው ተምዘግዝጐ የገባውን የአበበን ቃላት ማመን አቃተው። እንደመደንገጥ ብሎ «ምን አልከኝ?» በማለት ጠየቀው። አበበም የማሞን መደናገጥ ስለተገነዘበ እንደ ማባበል ዓይነት አለና «አይዞህ ታሸንፋለህ፤ እኔ አልቻልኩም፤ የእግሬ ወለምታ በጣም ተሰምቶኛል፤ ሌላም የማላውቀው ስሜት እየተሰማኝ ነው። ስለዚህ አደራዬን ተቀበለኝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠብቀናል፤ እኔ ስላልቻልኩ አንተ ቀጥል፤ የኢትዮጵያ አምላክ ይከተልህ» ካለው በኋላ አስፋልት ዳር ወደቀ። እውነትም በጣም ታሟል። ወዲያውኑ አበበ ሜክሲኮ ሆስፒታል በአስቸኳይ ተወሰደ። ማራቶን ልእልቷ አቤን ከዳችው። እርግጥ ነው በዚህ ውድድር የተጠበቀው አበበ ቢቂላ ነበር። የአበበ ውድድሩን ማቋረጥ ብዙዎቹን በማስደንገጡ በስቴዲየሙ የተገኙ ኢትዮጵያውያኖች የአበበ ማቋረጥ እንደተሰማ ስቴዲየሙን ለቀው ማሞ ወልዴን ለማበረታታት ወደ አደባባይ ወጡ። በዚያን ወቅት የነበረውን ሁናቴ ታዋቂው ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ እንዲህ ገልፆት ነበር፤ «የአበበን መውጣት ስሰማ ማሞን ለማበረታታት የጮህኩት ጩኸት ድምፄን ለሦስት ቀናት ያህል ዘግቶት ነበር።» ማሞ ብቻውን ቀሪውን ኪሎ ሜትር እየመተረ፤ በከፍተኛ ሞራል በመገስገስ ያለተቀናቃኝ የሜክሲኮን ኦሎምፒክ አሸንፎ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆነ። ማሞ በዚህ የሜክሲኮ ውድድር የ10 ሺህ ኪሎ ሜትር ማጣሪያና ፍፃሜ ውድድርን ጨምሮ 62 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር በመሮጥ የAንድ የወርቅና የአንድ ነሐስ ባለቤት በመሆን ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ሣይሆን አይቀርም። አበበ ከሆስፒታል ወጥቶ ማሞን ባየ ጊዜ እጅግ ከመደሰቱም በላይ ስቅስቅ ብሎ ካንጀቱ አለቀሰ። «የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠብቀናል» ብሎት ስለነበር ማሞ ..ረውም። በሦስት ተከታታይ የማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆኗ ዓለምን ቢያስደንቅም የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስታው ከመጠን በላይ ሆኗል። የቡድኑ አባላት ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ እለትም አበበንና ማሞን ለመቀበል ሕዝቡ በነቂስ ነቅሎ ወጥቷል። እልልታው፤ ዘፈኑ፤ ዝማሬው፤ ጭፈራው የአዲስ አበባ ጐዳናዎችን ከማስጨነቁም ባላይ አዲስ አበባ ከመመሰቃቀሏ የተነሣ የሠርግና የደስታ አውድማ መስላለች። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በየአግጣጫው ይውለበለባል። የክብር ዘበኛው ባንድ ጀግኖቹን ለመቀበል በልዩና በሚያስደስት ቅንብር ያሣየው ትርኢት ድንቅ ነበር። እንዲህ ነው ጀግንነት! እንዲህ ነው ወንድነት! አበበና ማሞ አንድና ሁለት! በማለት እንዲህ ሲባል ተገጠመላቸው፤

ማራቶን ማራቶን ማራቶን ውዲቷ
አበበና ማሞ ሆነዋል ባለቤቷ
ማራቶን ጠብቀሽ አቤን ብትቆጪ
ሆኖም አልቀረልሽ የትም አታመልጪ
አበበ ቢወጣ በእግር ወለምታ
ማሞ ተተክቷል የሐገሩ መከታ
ሮምን በባዶ እግሩ ቶኪዮን በጫማ
ድል አድርጓል አቤ በሁለቱም ከተማ
ተባለላቸው፤ ተዘመረላቸው። ተጨፈረላቸውም።

አበበ አንደ ዛሬ የዘመኑ ሥልጣኔ ባልተስፋፋበት ጊዜ በባዶ እግሩም፤ በጫማም የኦሊምፒክ ውድድርን ብቻ ሣይሆን በተለያዩ ውድድሮች አሸንፏል። ከዋሚና ከማሞ ጋርም ብዙ የዓለም-አቀፍ ውድድሮች ላይ ተካፍለው አሸንፈዋል። በዚያን ጊዜ አበበ የገባበት ሰዓት ዛሬም ቢሆን በቀላል Aይገባም። አበበ ቁመቱ ሎጋ፤ የቀይ ዳማና መልከ-መልካም Iትዮጵያዊ ነበር። በመልኩና በቁመናው እንዲሁም ባስመዘገበው ውጤት በመላው ዓለም ትልቅ ስምና ክብር አግኝቷል።
ከዚህ ውድድር በኋላ የጀግናው ሕይወት እንዴት ነበር የሚል ጥያቄ አንባቢያን ሊሰነዝሩ ይችላሉ። አበበ የጀግንነት ክብር ማግኘቱ፤ ዝናና ታዋቂነት ማትረፉ፤ በአጠቃላይም ስሙ በሐገር ውስጥም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጐልቶ ይታወቅ እንጂ በሕይወት ዘመኑ በርካታ ፈተናዎች ውስጥ ገብቷል። ዝነኛ ሰው ብዙ ችግሮች አጋጥመውታል። ቅናት እና ፍቅር ዋነኛዎቹ ናቸው። አበበም ከሁለቱ ለማምለጥ አልቻለም። ጀግና ይወደዳል፤ ይፈቀራል፤ ይከበራል። በ1972 ዓ.ም. በጀርመን ሙኒክ ከተማ የተካሄደው የማራቶን ውድድር ለኢትዮጵያውያኖች መጨረሻ ድል ነበር። አበበ ቢቂላ በሙኒክ ከተማ የተገኘው እነዚያ የሚወናጨፉ እግሮቹን ጣጥፎ፤ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ (1) ሲሆን፤ በስታዲየሙ የተገኙ ተመልካቾች ከመቀመጫቸው ተነስተው በጭብጨባ ነበር ተቀበሉት። በዚሁ በሙኒክ ውድድር በAርባ ዓመት እድሜው የተሣተፈው ማሞ 2፡14፡31 በመግባት 3ኛ ወጥቶ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቃ።

(2)

በነገራችን ላይ በሙኒኩ ውድድር Iትዮጵያ በማራቶን ነሐስ ሜዳሌያ ከማግኘቷ ሌላ በ10ሺህ ኪሎ ሜትር በአትሌት ምሩፅ ይፍጠር አማካይነት ሁለተኛውን ነሐስ አግኝታለች። ግናው አበበ ቢቂላ በተሽከርካሪ ወንበር ላይም ሆኖ በድጋሚ የዓለም የቀስት ሻምፒዮን ሆኗል። በእግሩ ያጣውን የወርቅ ሜዳሊያ በዓይኖቹና በእጆቹ ለማግኘት ችሏል። በ1966 ዓ.ም. አቤ ለዘላለም ይለየን እንጂ። ሻምበሉ ምን ጊዜም ሕያው ነው። ስሙ ከመቃብር በላይ ነው። አበበ ዛሬም ለሚሊዮን ኢትዮጵያውንና ሌሎች አትሌቶች አርዓያና «Inspiration» ምንጭ በመሆን በርካታ አበበዎችን ተክቶልን አልፏል። የዚህ እውቅና ድንቅ አትሌታችን የክብር መታሰቢያ ሐውልት በባእድ ሐገር በቶኪዮ በክብር ከመቆሙም በላይ ልዩ እንክብካቤም እንደሚደረግለት አንባቢያን እንዲገነዘቡልኝ እሻለሁ። በሐገራችን ያለው የአበበ ሐውልት ጉዳይ ግን እጅግ አሣዛኝ ነው። አቶ አቤ ሴሎም በክብር ያሠሩለት ሐውልት ዛሬ ምን እንደሚመስል ለአንባቢያን እተዋለሁ። በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከ1972 ዓ.ም. በኋላ ለማራቶን ድል ባትታደልም በተሣተፈችባቸው ኦሊምፒኮች ሁሉ የሩጫን ድል Aላጣችም። በ10ሺህና በ5ሺህ ኪሎ ሜትር ውድድሮች ብርቱ አትሌቶች ድል አጐናፅፈውታል። ምሩፅ ይፍጠር፤ መሐመድ ከድርና ቶሎሣ ቆቱ በ10ሺህ፤ መሐመድ ከድር፤ ዮሐንስ፤ ምሩፅ ይፍጠርና እሸቱ ቱራ የቡድን ሥራ በመሥራት በ5ሺህ ኪሎ ሜትር ተከታትለው በመግባት ሞስኮ ላይ ታሪክ ሠርተዋል።

ኢትዮጵያ በ1992 ዓ.ም. በስፔን ባርሴሎና በተካሄደው ውድድር በደራርቱ ቱሉ በ10ሺህ፤ በፊጣ ባይሣና በአዲሱ አበበ 1የወርቅና 2 የነሐስ አግኝታለች።1996 ዓ.ም. በአትላንታ ኦሊምፒክ ኃይሌ ገ/ስላሴ፤ ጌጤና ፋጡማ ሮባ በድል አንበሽብሸውናል። ንጉሱ በንግሥት ተተካ። በአትላንታ። አበበ የባረከውን፤ ማሞ የደገመውን የማራቶን ድል Aትሌት ፋጡማ ሮባ አፀናችው። ኢትዮጵያ በወንዶች ብቻ ሣይሆን በሴቶች ማራቶን እንደገና ንግሥት ሆና ብቅ አለች። በአበበ ቢቂላ ፈር ቀዳጅነት ጥቁር ሕዝቦችን ያኮራው የማራቶን ድል በማሞ ወልዴ አርማ አንሺነት የፀደቀው የማራቶን ድል፤ ዛሬ ከማንም በላይ ለኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት ሁሉ ተናፋቂ ነው። በሚቀጥለው ተረኛ ባለታሪክ እስከምንገናኝ ድረስ ቸር ይግጠመን።

የግርጌ ማስታወሻ
በዘመኑ በIትዮጵያ ራዲዬ እንደተነገረው አበበ ሸኖ በምትባል አካባቢ መኪና ተገልብጦ አደጋ ደረሰበት የሚል ዜና ተሠራጨ። በእውነት አበበ የሚኪና አደጋ ነው የደረሰበት? እንዴት ሁለቱን ፈጣን እግሮቹን ብቻ Aደጋ ደረሰባቸው? ዓይኑ አልተነካ፤ እጁ ላይ ቁስል አልደረሰበት። ምንድነው ምስጢሩ? እስካሁን ድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአበበ አሟሟት ትክክለኛ መንስዔ በትክክል ካለመታወቁም ባለይ እንቆቅልሽም ሆኖ ይገኛል። የአሟሟቱ መንስዔ የተሣፈረባት ቮልስቫገን ሣትሆን «ልዩ እጅ» የነበረው ስለመሆኑ በጊዜው ልንሰማ ችለናል።
ሶራ ጃዌ
.
ሮም የኢትዮጵያ ደመኛ አገር የነበረችዋ የጣሊያን ዋና ከተማ ናት። በሮም፣ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ፣ በአዲስ አበባ የጣሊያን ባንዲራ በመተከሉና ኢትዮጵያ በጣሊያን እጅ በመውደቋ የድንፋታ ንግግር ለአገሬዉ ሕዝብ ያደረገበት ከተማ ናት። ከሃያ ስድስት አመታት በኋላ፣ እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ 1952 ዓ.ም ባንዲራችን መሬት ወድቆ ጮቤ በተረገጠባት ከተማ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ከፍ ብሎ ተዉለበለበ። በዚያን ቀን ታሪክ ተሰራ።


Nessun commento: