martedì

“የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል”


* ዶ/ር ዘለቀ እሬሶ*
... በአገራችን በኢትዮጵያ ገበያ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መተንተኑ በዚህ ወቅት አስፈላጊነቱ ጎልቶ ባይታየኝም እንዲያዉ ለማስታወስ ያህል ባጭሩ ገበያ ማለት ምርት አምራቹ ግለሰብ ወይንም ቡድን በተለይም የገጠሩ አርሶ አደር ክፍል ማንኛዉንም ያመረተዉን ጥሬ እቃ ለመሸጥ የሚያቀርብበት አማካይ ስፍራና ለኑሮዉ የሚያስፈልገዉን ለመግዛት የሚሄድበት ማእከላዊ ቦታ ነዉ:: ብቻ ባጠቃላይ እቃና ገንዘብ የመለዋወጫዉ ቦታ ገበያ በመባል ይጠራል:: በመሆኑም የተለያዩ የገበያ ስሞችን እንደነ ጉልት ገበያ፣ መርካቶ፣ እሁድ ገበያ፣ ቅዳሜ ገበያ፣ ሰኞ ገበያ፣ ማክሰኞ ገበያ ወዘተ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል::
... ከላይ እንደጀመርኩት ገበያ የእቃና የገንዘብ መለዋወጫ ቦታ ብቻ ሳይሆን የአገር ሽማግሌዎች የተጣሉ ግለሰቦችን በመጥራት የሚያስታርቁበት ስፍራም ነዉ:: በዚህ የገበያ ቀን ሌባዉንና አታላዩን ለመቆጣጠር ሲባል የጸጥታ አስከባሪዎች በገበያዉ ዉስጥ በመዞር አካባቢዉን ይቃኛሉ:: ይህም ለገበያዉ መልካም ፍጻሜ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል:: ህዝቡም በሰላም የሚፈልገዉን በመግዛትም ሆነ በመሸጥ የፈለገዉን አከናዉኖ ወደየቤቱ ይመለሳል::
... ማህበራዊ ኑሮን በተመለከተ ገበያ ጥቅሙ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ህብረተሰቡ ጥላቻን አስወግዶ ተፋቅሮ፣ ተሳስሮ፣ ተቻችሎ፣ ተረዳድቶና ተስማምቶ በአንድነት እንዲኖር በማድረግም ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል::
ታዲያ በዚህ በምንኖርበት አካባቢ ማለትም “በዉጭዉ አለም” የገበያ ሁኔታ መልኩና ይዘቱ በጣም ለየት ያለ ነዉ:: አንዳንድ እዚህ ነዋሪ የሆኑት የዉጭ ሀገር ዜጎችም የንግዱን አለም ተያይዘዉታል:: ቁጥራቸዉም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል:: የንግዱን ይዘትም በሁለት መልኩ ልናገናዝበዉ ይገባል:: በአንድ በኩል የሚያበረታታና እንደ ምሳሌ የሚወሰድ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ “የገበያ ግርግር ለሌባ ምቹ ነዉ” የሚለዉን የአያቶቻችንን አባባል የሚያስታዉሰን ይመስለኛል::
... እስቲ የመጀመሪያዉን ለመመልከት እንሞክር:: አንድ በዚህ አካባቢ ነዋሪ የሆነ የዉጭ ሀገር ዜጋ የሚኖርበትን ሀገር ቋንቋ፣ ባህልና የኑሮ ዘዴዉን ጠንቅቆ ከተረዳ ህጋዊ በሆነ መንገድ ሰርቶ ለመንግስት ደግሞ መክፈል የሚኖርበትን የስራ ግብር ከገበረና ከማንኛዉም ወንጀል ነጻ ከሆነ ግዴታዉን በሚገባ ተወጥቶአል ብሎ ማለት ይቻላል:: ይህም ከአንድ ጥሩ ነዉ ከሚባል ዜጋ የሚጠበቅ በጎ ስነምግባር ነዉ:: አብዛኛዉን ጊዜ የዉጭ ሀገር ዜጋ ይህን ግዴታዉን አጥብቆ መወጣት እንዳለበት ተደጋግሞ በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች እንደ ዉዳሴ ማሪያም ሲነገረዉ መብቱን በተመለከተ እንዲከበርለት በሚጠይቅበት ወቅት ግን መልሱ ሰምቶ እንዳልሰማ ይሆንና ግለሰቦችን ወደማይፈልጉት የወንጀል መንገድ ይመራቸዋል:: መብትና ግዴታ ተነጣጥለዉ የሚታዩ ሁለት ነገሮች መሆን የለባቸዉም::
... በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የግለሰቦች መብት አለመከበር ብዙ የሚያስከትላቸዉ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም:: የጸጥታ ችግር፣ የሌብነት፣ የማጭበርበር፣ የሽርሙጥና፣ የድራግ ሱስ ወዘተ ብቻ በአጠቃላይ “እንደምንም ገንዘብ ብቻ ላፍራ” የሚል መፈክር ተይዞ ይነሳና መጨረሻዉ ዉድቀት ከመሆንም ያልፍና ሰላማዊ ኑሮ ቀርቶ በምትኩ መፈራራትና ጥላቻ የመሳሰሉት ይነግሳሉ:: ብልጠትን፣ ማጭበርበርንና ዉሸትን መሰረት በማድረግ የሚሰራን ስራ እንደ ስራ ሊንቆጥረዉ አይገባም::
... በኢጣሊያን ሃገር ዉስጥ በግምት ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ የዉጭ ሐገር ዜጎች እንደሚኖሩ ይነገራል:: ይህ ቁጥር ብዙ መስሎ ቢታይም ከሌሎች የአዉሮፓ አገሮች ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ነዉ:: በተጨማሪ ለጊዜዉ ቁጥራቸዉ በትክክል የማይታወቅ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት የሌላቸዉ የድብቅ ስራ በመስራት ኑሮን ለመወጣት የሚታገሉም ጭምር እንዳሉ ነዉ::
... አንዳንድ የዜና ማሰራጫዎች አልፎ አልፎ የዉጭ ሃገር ዜጋን በተመለከተ ትክክለኛ ያልሆነ መልክት ያስተላልፋሉ:: የዉጭ ሃገር ዜጋንና ወንጀልን አጣምረዉ በማቅረብ የዉጭ ሃገር ዜጋዉን ሁሉ ወንጀለኛ አድርገዉ ያቀርባሉ:: በዚሁ የተሳሳተ መልክት የተነሳ በየመንገዱ “አሁንስ እነኚህ የዉጭ ሃገር ዜጎች በዙ ይዉጡልን” የሚሉትንና የመሳሰሉትን ዘረኛ ቃላት መስማቱ ጆሮዬ ዳባ ልበስ ሆኖአል:: ይህም እንግዳዉንና አስተናጋጁን አይጥና ድመት ሆነዉ የጎሪጥ እንዲተያዩ ያደርጋቸዋል::
... ለማጠቃለል ያህል በዚህ ብልጠትና እራስ ወዳድነት በበዛበት በተለይም ባሁኑ ወቅት የዉጭ ሀገር ዜጋዉ ከምን መጠንቀቅ አለበት:
... 1. በማሳወቅና በማስተማር ፋንታ “አንተ አታዉቅም፣ ቋንቋ አትችልም፣ እኔ እሰራልሀለሁ፣ እኔ አስብልሃለሁ” ከሚሉት የአፍ እርዳታ ሰጪዎች በሚገባ መጠንቀቅ;
... 2. በተቻለ መጠን ተደብቆ በጥቁር መስራትን ማስወገድና ለመንግስት አስፈላጊዉን የስራ ግብር በወቅቱ መክፈል;
... 3. በስራ የሚተዳደረዉ የዉጭ ሀገር ዜጋ እድሜ ገፍቶ ጡረታ እንዳለ በመረዳት አስፈላጊዉን የጡረታ ማስከበሪያ የታክስ ሁኔታ ከሚመለከተዉ መንግስታዊ አካል የራስን ሁኔታ መከታተል;
... 4. ትምህርትን በተመለከተ በመማር ላይ ያለዉ ትምህርቱ “ጊዜን ገዳይ ብቻ” እንዳይሆንበት ተጠንቅቆ ትምህርቱ እንዳበቃ ስራ ማግኘት የሚያስችለዉን የትምህርት አይነት መማር እንዳለበት ከሚያዉቁት ሰዎች ጠይቆ መረዳት;
... 5. ከዘረኝነት በሽታ፣ ከሃይማኖት የበላይነት፣ ከአጉል ፉክክር፣ ከማይጠቅም ምቀኝነት፣ ከማያሳድግ ሃሜትና አሉባልታ እና ከመሳሰሉት ኋላ ቀር አመለካከቶች በመራቅ ሰላማዊ ኑሮን ከሚያስፋፉ የህብረት ክፍሎች ጋር መተባበር;
... 6. ግዴታን ከተወጡ የግል መብትንም ለማስከበር መጣር::
በሚቀጥለዉ እስክንገናኝ መልካም ቆይታ


Nessun commento: