giovedì

“ሐሰትና ስንቅ እያደር ይቀላል”

ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ 18.02.08

በአንድ በዴሞክራሲ በበለፀገና ባደገ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት የወደፊት ፕሮግራም ዝግጅት መሰረት በአገሪቱ በሚደረገዉ የፖለቲካ ምርጫ ለመካፈል ቅስቀሳ የማካሄድና አላማቸዉም ጭምር ምን እንደሆነ በትክክል ለመራጩ ሕዝብ የማሳወቅና የማስረዳት ግዴታ ሲኖርባቸዉ በአንፃሩ መብታቸዉም የተጠበቀ እንደሆነ ይታወቃል:: ይህንንም ስርአትና ደንብ የዴሞክራሲ ጨዋታ (il gioco delle regole della democrazia) በማለት ይጠሩታል::
በዚህ በጣሊያን አገርም እንደ አዉሮፓዉያን አቆጣጠር የፊታችን 13 እና 14 አፕሪል 2008 በሚደረገዉ የፖለቲካ ምርጫ ላይ ለመካፈል የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የዉጭ ሀገር ዜጋዉን በተመለከተ የማስፈራራት ዘመቻ፣ ቅስቀሳ፣ ፕሮፖጋንዳና ሽብርም ጭምር በመንዛት ላይ እንደሆኑ በገሃድ ይታያል::
ከዚህ ቀጥሎ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ዝርዝርና ፕሮግራማቸዉን በተለይም በጣሊያን አገር ነዋሪ ለሆኑት አንባቢያን ሊጠቅም ይችላል በማለት ባጭሩ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፣
ስኒስትራ አርኮባሌኖ (Sinistra Arcobaleno):
ባጠቃላይ በተግባር መተርጎም ቢችል የዉጭ አገር ዜጋዉን መብት ሙሉ በሙሉ ሊያስከብር የሚችል ፕሮግራም መስሎ ይታያል;
የዴሞክራትክ ፓርቲ (Partito Democratico):
እምግሬሽንን መቆጣጠር፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት የጊዜ ገደብ ይራዘም፣ መብትና ግዴታን ማሳወቅ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት ማስከበር፣ ጣሊያን አገር ለሚወለዱት ሁሉ የዜግነት መብት ማስከበር፣ ሕገወጥ ወይንም ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጎችን ማባረር;
እታሊያ ደይ ቫሎሪ (Italia dei Valori):
ወንጀልን ማጥፋት፣ ሕገወጥ ወይንም ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጎችን ወዲያዉኑ ማባረር; ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጋ ወደ አገሩ ተልኮ እስር ቤት ይቆያል;
ዩኒዮኔ ዲ ቸንትሮ (Unione di Centro); ወንጀልን ማጥፋት፣ የጣሊያን ዜጎችን ህይወት መንከባከብ፣ ለቁጥጥር ይሆን ዘንድ ለፖሊስ ተገቢዉን መሳሪያ ማቅረብ፣ እምግሬሽንን መቆጣጠር፣ ስራና መኖሪያ ቤት ያለዉ ታክስ በአግባቡ የከፈለ የዉጭ አገር ዜጋ የመኖር መብቱ ይከበራል;
ፖፖሎ ደላ ሊበርታ (Popolo della Libertà)
ወንጀልን ማጥፋት፣ ሕገወጥ ወይንም ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጎችን ወዲያዉኑ ማባረር; እንተርናሽናል ወንጀልን መቆጣጠር፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ለሌላቸዉ እንዳይሰጥ፣ ጊዜያዊ እስር ቤቶችን ቁጥር መጨመር፣ ስራና የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ተለያይተዉ አይታዩም በመሆኑም ስራ የሌለዉ የዉጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀቱ አይታደስም;
ላ ዴስትራ (La destra)
በጣሊያን አገር የሚገኝ ማንኛዉም የዉጭ አገር ዜጋ ወደ መጣበት ትዉልድ አገሩ ይመለስ፣ ወንጀልን ማጥፋት፣ ወንጀለኛ የዉጭ አገር ዜጋ ወደ አገሩ ተልኮ እስር ቤት ይቆያል፣ በደንብ መቆጣጠር ይቻል ዘንድ የዉጭ አገር ዜጋ ሁሉ አሻራ የመነሳት ግዴታ አለበት፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ለሌላቸዉ እንዳይሰጥ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳይፈቀድ;
ሌጋ ኖርድ (Lega Nord)
ስራና የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ተለያይተዉ አይታዩም፣ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ገንዘብ ማሳየት ያስፈልጋል ገንዘቡም እንዴት እንደተገኘ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፣ በዉጭ አገር ዜጋዉ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር መደረግ ይኖርበታል፣ በመንግስት የመኖሪያ ቤቶች ዉስጥ በሚኖሩት ቤቱ በትክክለኛ ህጋዊ መንገድ እንደተሰጣቸዉ አትብቆ መቆጣጠር፣ ማንኛዉም መንግስታዊ እርዳታ ለዉጭ አገር ዜጋ እንዳይፈቀድ እና የመሳሰሉትን ይጠቅሳል::
እንግዲህ ባጠቃላይ የፓርቲዎቹን ፕሮግራም ስንመለከት ከመጀመሪያዉ በስተቀር ሁሉም የጋራ ቀመራቸዉ የዉጭ አገር ዜጋዉ ሁሉ አደገኛ እንደሆነ በማስመሰል በህብረተሰቡ ላይ ፍርሃትን መዝራት ሆኖአል::
ዉሸትና ስንቅ እያደር ይቀላል እንደተባለዉ ከምርጫዉ በኋላ ሁሉም ይረሳና እንደነበረዉ ይቀጥላል ብቻ ለማየት ያብቃን::

Nessun commento: