mercoledì

ጣሊያንና የዉጭ ዜጎችዋ


ከጠብ ወደ ፍቅር ወይንስ ከፍቅር ወደ ጠብ
ቃለ መጠይቅ

የተያያዝነዉ አዲስ ዓመት የሰላም፣ የደስታና የብልጽግና ይሁንልን በማለት እራሴን ላስተዋዉቅ።
አብረሃም ዘዉዴ እባላለሁ:: ከሁሉም በፊት በየዕለቱ ይህንን ድረገፅ የሚጎበኙት (በውጪ ሀገራት የሚኖሩት) ግለሰቦች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እና ይህች ድረገፅ የራስዋ ግብ ላይ ለመድረስ ስለተቃረበች አዘጋጅና ተባባሪዎች የሆንን በሙሉ ደስታ ተሰምቶናል። ለዚህም እኔም ከልብ አመሰግናለሁ::
ከዚህም በመቀጠል ለዚህ መድረክ ዝግጅት መሳካት ተባባሪ ከሆኑት አንዱ ከዶ/ር ዘለቀ እሬሶ ጋር በጣሊያን የዉጭ አገር ዜጎችን በተመለከተ አጠቃላይ ሁኔታ ያደረግሁትን ቃለ መጠይቅ (ጥያቄና መልስ) ባጭሩ ከዚህ በታች አቀርብላችኋለሁ::

ጥያቄ:- ... በቅርቡ አለም አቀፍ የስደተኞች ቀን (Immigration Day) በጣሊያንም አገርም ተከብሮ ነበር:: ይህን በተመለከተ በጣሊያን ለሚኖሩት ኢትዮጵያዉያንም ሆነ ከጣሊያን ዉጪ ለሚከታተሉን ሁሉ ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?

ዶ/ር ዘለቀ:- ... ይህን ጥያቄ በብዙ መልኩ መመለስ ይቻላል:: ለምሳሌ የጣሊያን ፕሬዝደንት የተከበሩት ጆርጆ ናፖሊታኖ በዚሁ ጉዳይ ላይ ሰሞኑን እንዲህ ብለዉ ነበር: በጣሊያን ነዋሪዉ የዉጭ አገር ዜጋ ለኢኮኖሚያችንና ለባህላችን እድገት መሰረት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፣ ልዩነታችን የብልጽግናችን መሰረት ነዉ:: በታሪክ እንደሚታወቀዉ ሁሉ እኛ ጣሊያኖች በመሰደድ የመጀመሪያዎች ነበርን ዛሬ ግን የዉጭ አገር ዜጎች ስራ ለመፈለግ በራችንን በሚያንኳዋኩበት ባሁኑ ወቅት የማስተናገድ ችሎታችንም ያን ያህል ከፍተኛ መሆን አለበት:: ሁሉም የዉጭ አገር ዜጋ እንደወንጀለኛ መቆጠርና መታየት የለበትም:: በህጋዊ መንገድ ሰርቶ የሚኖር፣ ህጋችንን የሚያከብር የዉጭ አገር ዜጋ ሁሉ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ያሉት ተስፋ የሚሰጥ ይመስለኛል::

ጥያቄ:- ... ባለፈዉ 21/12/2006 የጣሊያን ፓርላማ የ 2007 የአመት በጀቱን አጽድቋል:: በዚህ ህግ ዉስጥ የዉጭ አገር ዜጋን የሚመለከቱ ጉዳዮች ወይም አንቀጾች ካሉ በተለይ በጣሊያን ለሚኖሩ አንባቢያን ሊጠቅም ስለሚችል ባጭሩ ቢገልጹልን?

ዶ/ር ዘለቀ:- ... አንዳንድ ጥቃቅን ጉዳዮች አሉበት ለምሳሌ የዉጭ አገር ዜጋን የስራና የመኖሪያ ችግር ለማቃለል ተብሎ የተወሰነ ያህል በጀት ተመድቧል፣ በቤት አገልጋይነት የዉጭ አገር ዜጋን ቀጥሮ የሚያሰራ ማንኛዉም አሰሪ ግለሰብ የግብር ቅነሳ ይደረግለታል፣ አዲስ ኮምፕዩተር ለሚገዛ ወይንም ያለዉን ለሚቀይር የዋጋ ቅናሽ ይደረግለታል፣ የያዘዉን አሮገ የቤት መኪና በአዲስ ለሚቀይር ድጎማ ይሰጠዋል፣ የግል ድርጅት ለማቋቋም ለሚፈልጉ አማካሪ ድርጅቶችን ይመድባል የሚሉትና የመሳሰሉት ይገኙበታል:: በወረቀት ላይ ያሰፈሩት ተግባራዊ እንዲሆን ተስፋ አደርጋለሁ አንዳንዴ ህጎች ይጸድቁና ተግባራዊ ሳይሆኑ ይቀራሉና ተከታትሎ ዉጤቱንም ማረጋገጥ ያስፈለጋል::

ጥያቄ:- ... ለመሆኑ በጣሊያን ፓርላማ ዉስጥ የዉጭ አገር ዜጎች አሉ? ካሉ ቁጥራቸዉስ ምን ያህል ነዉ?

ዶ/ር ዘለቀ:- ... በጣሊያን ፓርላማ ዉስጥ በመጨረሻዉ ምርጫ የተመረጡት በትዉልድ የዉጭ አገር ዜጋ በዜግነት ጣሊያናዊ የሆኑት ተመራጮች ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ ነዉ:: ባልሳሳት አራት ወይም አምስት ቢሆኑ ነዉ:: ይህ የሚያሳየን በጣሊያን የዉጭ አገር ዜጋዉ በፖለቲካ የተጠናከረና የተደራጀ አለመሆኑን ነዉ:: ምንም በፓርላማ ባይመረጡም በየክፍለሃገሮችና በየማዘጋጃ ቤቶች ያስተዳደር ምርጫ በመካፈል የሚመረጡት በትዉልድ የዉጭ አገር ዜጎች ቁጥር ግን እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል፣ ይህም ያበረታታል ብዬ አምናለሁ::

ጥያቄ:- ... በጣሊያን አገር በግምት ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ የዉጭ አገር ዜጎች እንደሚኖሩ እንሰማለን በፖለቲካና በማህበራዊ ኑሮዉ ሙሉ በሙሉ የተካፈሉት ጥቂቶች ናቸዉ ምክንያቱ ምን ይመስልዎታል?

ዶ/ር ዘለቀ:- ... በመጀመሪያ ባንድ አገር የፖለቲካና ማህበራዊ ኑሮ ሙሉ በሙሉ ለመካፈል የዚያን አገር ቋንቋ፣ ባህል፣ የኑሮ ዘዴ፣ እና የመሳሰሉትን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል:: አንዳንድ ጊዜ ግለሰቦች ከጣሊያን ዉጪ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ በመፈለግ ጣሊያንን እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ አድርገዉ ስለሚወስዱ ቋንቋውን ለማጥናትም ሆነ አልፎ ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ብዙም የዉስጥ ፍላጎት አይኖራቸዉም፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ኑሮዉ ተካፋይነታቸዉም እየቀነሰ ይመጣል:: አንዳንድ ጊዜ የቁጥር መብዛት ብቻዉን በቂ ሊሆን አይችልም:: በሌላ በኩል ደግሞ ከጣሊያን የመንግስታዊ አካል በኩል ለብዙ ጊዜ የዉጭ አገር ዜጎች ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠዉ ቆይቷል፣ ችግሮች ከመከሰታቸዉ በፊት ፕሮግራም አይወጣም ይህ ደግሞ ለቁጥጥር አመቺ አይሆንም እንክርዳዱን ከስንዴዉ ለመለየትም ያዳግታል::

ጥያቄ:- ... የጣሊያን ጋዜጠኞች ብዙ ጊዜ ስለዉጭ አገር ዜጋ ወንጀል ብቻ ሲጽፉ እናያለን የዉጭ አገር ዜጋዉ ሁሉ ወንጀለኛ ነዉ ማለት ነዉ ወይንስ ይህ ጉዳይ እንዴት ነዉ?

ዶ/ር ዘለቀ:- ... አዎን ጋዜጦች ለምዶባቸዉ ነዉ መሰለኝ የዉጭ አገር ዜጋዉን ሁሉ ከወንጀል ጋር ያዛምዱታል፣ ይህ በኔ ግምት የፕሮፌሽኒስት ወይም የባለ ሙያ ጋዜጠኛ ስራ አይደለም ምክንያቱም እየቆየ ሲሄድ ከፍቅር ይልቅ ወደ ጠብ ያመራል:: እዚህ ላይ አንድ የማስታዉሰዉ ነገር አለ ባለፈዉ ጊዜ አንድ የሴኔጋል ተወላጅ ለረፍት ባህር ሄዶ ከሌሎች ጋር ዋና በመዋኘት ላይ እንዳሉ አንድ ጣሊያናዊ ህጻን ይሰምጥና የሰመጠዉን ልጅ አድናለሁ ብሎ ገብቶ ሰምጦ ሞተ:: ድርጊቱ በተፈጸመበት ወቅት ይህን ያህል አልተወራም ነበር:: እንደዚህ አይነት ተግባር ቢታይም ለህብረተሰቡ በተገቢዉ መንገድ አይቀርብለትም:: ይህ ብቻ አይደለም በጣሊያን ሰሜናዊ ክፍል ለፍተዉ የግል ድርጅቶች በመክፈት የዘር፣ የሃይማኖት፣ የጎሳ፣ የቀለም ልዩነት ሳይሉ ጣሊያኖችንም ጭምር ቀጥረዉ የሚያሰሩ በትዉልድ የዉጭ አገር ዜጎች በብዛት እንዳሉ መዘንጋት የለብንም:: ይህ ደግሞ ከጠብ ወደ ፍቅር ሊያመራ የሚችል ትክክለኛ መንገድ ነዉ::

ጥያቄ:- ... በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

ዶ/ር ዘለቀ:- ... በሺህ በሚቆጠሩ በተለያዩ ምክንያቶች ከትዉልድ አገራችን ዉጭ የምንኖር ኢትዮጵያዉያን ሁሉ “አንድነት ሃይል” መሆኑን ሳንዘነጋ በጋራ ችግሮች ላይ እኛን ከመሰሉት ሌሎች የዉጭ አገር ዜጎች ጋር መቀራረብና መነጋገር ይኖርብናል:: እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያዉቀዉን ለሌላዉ ለማያውቀዉ ወገኑ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት አዉቆ ተገቢዉን ቢያንስ የሞራል እርዳታን መለገስ ይኖርበታል:: የማናዉቀዉን ጉዳይ ከሚያዉቁት ጠይቆ ከመረዳት ወደ ኋላ አለማለት፣ ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሃሳብ ለሃሳብ መለዋወጥ:: ...



Nessun commento: